የኢሬቻው ድምቀት

የበዓላት ወቅት ሲደርስ የበዓሉን ድባብ ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል የባህል አልባሳት ተጠቃሽ ናቸው። ድሮ ድሮ የባህል አልባሳት በብዙዎች ዘንድ የማይመቹ ተደርገው የሚታሰቡ የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፋሽን ኢንዱስትሪው የባህል አልባሳትን በተለያየ ስልት እየሸመነ ሰዎች በዓላትን ሳይጠብቁ ጭምር እንደየምርጫቸው በባህላቸው እንዲያጌጡ እያደረገ ይገኛል።

በተለያዩ ስልቶች የተዋቡ የባህል አልባሳት ከሚስተዋሉባቸው በዓሎች አንዱ ኢሬቻ ሲሆን በዚህ በዓል ላይ ከህጻናት ጀምሮ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የባህል አልባሳት ተውበው ይስተዋላሉ።

እነዚህ አልባሳት በዓላቱን ከማድመቅ ባለፈም የአንድን ማህበረሰብ ማንነት በማጉላትና በማስተዋወቅ ፣ ኢኮኖሚውን በማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኢሬቻ በዓል መቃረብን አስመልክቶ የባህል አልባሳት ገበያው ምን ይመስላል ሲል የኦሮሞ ባህል አልባሳት ዲዛይነሮችንና ሸማቾችን አነጋግሯል።

የሎቲ ፋሽን ባለቤትና የፋሽን ዲዛይነር መርሲሜ ኩምሳ እንደምትለው የኦሮሞ ባህል አልባሳት ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን ለመሸጥ በዓመቱ የሚጠብቁት ትልቁ በዓል ኢሬቻ ነው። ከዚህ አንጻር ከሌሎች በዓላት በበለጠ ብዙ ትዕዛዞችን የሚቀበሉበትና ትልቅ ሽያጭ የሚኖርበት ወቅት ነው ትላለች።

ኢሬቻ በየዓመቱ አዳዲስ የፋሽን ስልቶች የሚታዩበት በዓል እየሆነ መጥቷል የምትለው መሪሲሜ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አልባሳቱ ባህላዊ እሴታቸውን በጠበቀ መልኩ በተለያየ ስልት የሚሠሩ በመሆናቸው ልብሱን የሚፈልግ ሰው እየጨመረ መምጣቱን ታነሳለች።

ዲዛይነሯ የሁሉም የኦሮሞ አካባቢ አልባሳትን የምትሠራ ሲሆን የአልባሳቱ ዋጋም እንደየዲዛይኑ ይለያያል። ለአብነትም በሎቲ ፋሽን የወለጋ የባህል ልብስ በሶስት ሺ ብር እየተሸጠ ሲሆን በጥልፍ ሲሠራ ደግሞ አስከ ሰላሳ ሺ የሚደርስ ዋጋ እንደሚኖራቸው ትገልጻለች።

በኢሬቻ ከአልባሳት በተጨማሪ የተለያዩ የኦሮሞ ማህበረሰብን ማንነት የሚገልጹ እንደ ቦራቲ ፣ሀደ ስንቄ ቆሪ የሚባሉ በእጅ የሚያዙ ጌጣጌጦችን እያቀረበች መሆኑ ትገልጻለች።

አልባሳት የአንድን ማህበረሰብ ባህልና ቋንቋ ከማሳደግ አንጻር የሚኖረው ሚና ትልቅ መሆኑን የምታነሳው መሪሲሜ፤ በኢሬቻ በዓላት የሚስተዋሉ የተለያዩ አልባሳትም የየአካባቢውን ባህል እያስተዋወቁና የሌላ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች እንኳን ስለ ማህበረሰቡ የተወሰነ እውቀት እንዲጨብጡ እያደረገ ይገኛል ትላለች።

ሌላኛዋ ለኢፕድ ሃሳቧን ያጋራችው የባህል አልባሳት ዲዛይነር አስናቁ መርሻ የባህል አልባሳት የአንድን ማህበረሰብ ባህል አጉልቶ የማሳየት አቅም ያለው ነው ትላለች። ለአብነትም የኦዳ ዛፍ እንዲሁም ጥቁር ነጭና ቀይ ጥለት ያለው ልብስ የኦሮሞ ማህበረሰብ መገለጫ ሆኖ በህብረተቡ ዘንድ እንዲቀረጽ የሆነው ከምንም ነገር በላይ ሰዎች ለብሰውት በሚንቀሳቀሱ የባህል አልባሳት አማካኝነት ነው ትላለች።

ወ/ሮ አስናቁ የባህል አልባሳት ባህሉን ከማስተዋቅ በተጨማሪ ለብዙዎች የሥራ እድል እየፈጠራና ብዙዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስተዳድሩ በማድረግ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ሚና እንዳለውም ታነሳለች።

ዲዛይነሯ ከኢሬቻ መድረስ ጋር ተያይዞ በዙ ሰዎች በፈልጉት ዲዛይን አልባሳት እንዲሠራላቸው ወደ ሱቋ ጎራ ማለት መጀመራቸውን የገለጸች ሲሆን ከምትቀበለው ትእዛዝ በተጨማሪም ይፈለጋሉ ተብለው የሚታሰቡ አልባሳትን እየሠራች ለገበያ እያወጣች ትገኛለች።

ዲዛይነሯ አልባሳቱ ላይ ከአምናው የኢሬቻ በዓል ጋር ሲነጻጸር ብዙም የሚባል የዋጋ ልዩነት የለም ያለች ሲሆን ሸማቾች ወደ ሱቋ ሲመጡም ከ1500 እስከ ስምንት ሺ ብር ባለው ዋጋ የሚፈልጉትን አይነት የባህል ልብስ መግዛት እንደሚችሉ ትገልጻለች።

በባህል አልባሳት መሸጫ መደብር ውስጥ ለኢሬቻ በዓል የምትለብሰውን ቀሚስ ስታዝ ያገኘናት ወጣት ሴና የማነ እንደምትለው በየአመቱ የኢሬቻን በዓል ስታከብር የባህል አልባሳትን ለብሳ እንደሆነ ገልጻለች።

አምና የወለጋ አካባቢ ቀሚስን ለብሳ ማክበሯን የምታስታውስ ሲሆን ዘንድሮ ከጓደኞቿ ጋር አንድ አይነት በጥልፍ የተሠራ የአርሲ ቀሚስ ለብሰው ለመውጣት በመነጋገራቸው ለዚህም የሚያሰሩትን ቀሚስ መርጣ ትእዛዝ መስጠቷን ገልጻለች።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You