የሰላም ስብራቱ ወጌሻ

በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደሚገልጹት፤ ብሔራዊ ምክክር በሥርዓተ መንግሥት እና በሀገራዊ ተቋማት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንደገና መገንቢያ መንገድ ነው። በግጭት የተለያዩ ማኅበረሰቦችን እንደገና ማሰባሰቢያ አጀንዳ እና አዲስ ማኅበራዊ ውል ማሠሪያ ገመድም ነው።

ሀገራት ውስጣዊ መሰንጠቅ እና የመበተን አደጋ ሲጋረጥባቸው የሚሻገሩበት ድልድይ፤ አለመረጋጋት እና የግጭት አዙሪት ሲንጣቸውም ከውድቀት መውጫ ምርኩዛቸው ነው። ሥርዓተ መንግሥት መገንባት ላልቻሉ ሀገራት ደግሞ ሕዝባቸውን በጋራ የታሪክ መሠረት፣ በዛሬ እኩልነትና በነገ ተስፋ ማሰባሰቢያ ነጋሪት ሆኖ ያገለግላል።

የሥርዓተ መንግሥት ግንባታቸውን በቅጡ ያልጨረሱ፣ በግጭት እና በኢኮኖሚ ውድቀት አዙሪት ውስጥ ለሚማቅቁ ኢትዮጵያን ለመሰሉ ሀገሮች ውይይቶቹ የሚመልሷቸው በርካታ ዝርዝር ጉዳዮች ስለሚኖሩ ሀገራዊ ውይይት (National Dialogue) ጥቅሙ ብዙ ነው ባይ ናቸው።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክከር ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲውል ምን አይነት አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ?

ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ “መግባባት ፖለቲካዊ ዕኩልነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን” በሚል ርዕስ በ2015 ዓ.ም አሻሽለው ባሳተሙት መጽሐፋቸው፤ ለሀገራችንና ለወገኖቻችን የሚበጅ ሃሳብ ማመንጨትና በሥራ ላይ ማዋል የሚቻለው በመነጋገር ነው ይላሉ።

ትልቅነት የሚመጣው በሃሳብ የምንለያይ ወገኖች በበጎ ፈቃድና በቆራጥነት ግንባር ለግንባር ተገናኝተን ለመነጋገር ስንችል ነው ያሉት ፕሮፌሰር አድማሱ፤ የሚያስፈልገን ሀገራችን የሁላችንም መሆኗን ተገንዝበን ችግሮቻችንን ለማሸነፍ በፈቃደኝነትና በቆራጥነት በጋራ መታገል ስንችል ነው ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠለጠነ፣ ሰላም ወዳድና ጨዋ መሆኑን ደግመን ደጋግመን ሰምተናል፤ አይተናልም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከዚህ ሕዝብ የወጡ የተለያዩ ዓላማዎችን ይዘው በፖለቲካ ቡድንነት የተደራጁ ወገኖቻችን በቅን ልቦና ከታገሉና ካታገሉ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን የፖለቲካ ሥርዓት ለማምጣት ብቃት ይኖራቸዋል። ለሀገርና ለሕዝብ የሚያገለግል፣ ለአሁኑም ሆነ ለሚቀጥሉት ትውልድ የሚበጅ ሥርዓት መሠረት በመጣል ታሪክ መሥራት ይችላሉ ነው የሚሉት።

ጸሐፊው እንደሚገልጹት፤ የግል ወይም የቡድን ጥላቻና ጠብ በሀገር ጉዳይ ውስጥ ቦታ የላቸውም። ይበጃል ያሉትን የተለያየ ሃሳብ ይዘው በሀገር ጉዳይ ላይ የሚነጋገሩ ሰዎች በሀገር ጉዳይ የሚተባበሩ፣ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ በሥራ ላይ ለማዋል የሚፈለገውን ሥልጣን ለማግኘት የሚፎካከሩ እንጂ ጠላቶች መሆን አይገባቸውም። የሥልጣን ተፎካካሪዎች ዓላማ የተሻለ ሁኔታ ለማምጣት፣ ሃሳብ ለሃሳብ መፋጨት፣ እንጂ መጠፋፋት አይደለም። ዓላማቸው ሃሳባቸውን ለሕዝብ አቅርበው በሕዝብ ዳኝነት መሠረት በሰላም ሁሉም እንደ ድርሻቸው ሥልጣንን መጋራት መሆን አለበት።

የሕዝብ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ይህንን እውን ለማድረግ ቅን መንፈስ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። መነጋገርን ትተው የመጠፋፋትን መንገድ ከገፉበት አደጋው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ሲሉም ያሳስባሉ።

የሃሳቦች መለያያት በራሱ ክፉ ነገር ሳይሆን ለሀገር እድገት የሚበጁ ሃሳቦችን ለማፍለቅ መነሻ (ጥንስስ) መሆኑ ሊታወቅ ይገባል የሚሉት ፕሮፌሰር አድማሱ፤ ሃሳቦችን እርስ በርሳቸው በማፋጨት፣ ብሎም በማቀራረብ፣ በጋራ ለጋራ የሚሆኑ አማራጭ ሃሳቦች በመፍጠር ወገንን ማገልገል እንደሚቻል ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና አብሮ የመኖር ባህላችንን ስንቅ አድርገን፣ የመግባባት ዴሞክራሲን መንገድ አቅጣጫ ይዘን ከተጓዝን እኛም ሰላም እናገኛለን፣ መጪዎቹም ትውልዶች ይኮሩብናል ሲሉም ከሀገራዊ ምክክሩ ብዙ ማትረፍ እንደሚቻል ጽፈዋል።

የፖለቲካ ተመራማሪው ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ከአንድ ቀን ጦርነት የአስር ዓመት ውይይት የሚል ታዋቂ አባባል አለ። እኛም እስካሁን በጦርነቶችና በግጭቶች ብዙ ነገሮች ሞክረናል። እስካሁን እንዳየነው ወደ ጦርነትና ግጭት የሚያመሩ ሰዎች መነሻና መድረሻቸውን የማያውቁና ግልጽ ፕሮግራም የሌላቸው ናቸው” ይላሉ።

በጣም የተደበላለቁ ነገሮች አሉ። ሁሉም ተንስቶ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልበት በእውቀት የማንመራበት፤ አዋቂዎቻችንን ሽማግሌዎቻችንን የማናዳምጥበት ደረጃ ላይ ደርሰናል የሚሉት ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር)፤ ይሄ ሁኔታ ሄዶ ሄዶ ይረግባል። ሲረግብና ስንደማመጥ ወደ ማዕከል እንመጣለን። ፍጹማዊ አንድነቱም ፍጹማዊ ልዩነቱም ይቀራል። ልዩነት ቢኖረንም ከውይይትና ከምክክር አያልፍም ወደሚል እምነት እንሻገራለን ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያስቀመጣቸው አጀንዳዎች ሲዘረጉና ወደ ውይይት ሲገባ ልዩነቶቻችን ብዙ እንዳልሆኑ ሁሉም ሰው እንደሚረዳ የሚጠቁሙት የፖለቲካ ተመራማሪው፤ እኛ እንደ ምሁር ብዙ መድረኮችን መርተን አወያይተናል፤ መጨረሻ ላይ አለመነጋገርና አለመወያየታችን እንጂ ልዩነታችን ጠባብ አንድነታችን ደግሞ የሚገዝፍ መሆኑን ተረድተን እንወጣለን ነው የሚሉት።

መግባባት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ ሰንደቅ ዓላማ፣ ሕገመንግሥት፣ የመሬት ይዞታ፣ የክልል አከላለል እና ሌሎችም ጠንከር ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ አመላክተው፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በሀገራዊ ምክክሩ ለውይይት ቀርበው በውይይት የሚፈቱት በዚሁ መንገድ እንዲፈቱ፤ ወደ ሪፈረንደም የሚሄዱ ጉዳዮችም በሕዝብ ድምጽ መቋጫ እንደሚያገኙ ይገልጻሉ።

ብዙ ዓመት ብንወያይ ችግሮቻችንን እየፈታን በጋራም ሆነ በግል በሰዎች እና ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እየቀነስን ሀገረ መንግሥት እየገነባን የምንሄድበትን ዕድል እንፈጥራለን እንጂ የምናጣው ነገር አይኖርም ሲሉም ያክላሉ።

የተከበሩ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራ የማያልቅ ተግባር ነው። በትውልዶች ቅብብሎሽ እየተሳካ የሚሄድ፤ ከዘመን ወደ ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ ትውልዶች በደረሱበት ደረጃና ዘመኑ በሚጠይቀው ሁኔታ ማዕከል ሀገራቸውን እየገነቡ የሚቀጥሉበት ነው። በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ አለመግባባት እንዲፈጠር በማድረግ በየጊዜው ሀገራችንን ለትርምስ፣ ለግጭት እና ለጦርነት እየዳረጉ የመጡ ጉዳዮችን ቁጭ ብለን ለመነጋገር የጀመርነው ጉዞ የሀገረ መንግሥት ግንባታን የሚያሳልጥ ነው ይላሉ።

የረጅም ዘመን ታሪክ ያለን እና በዓለም ላይ በሥልጣኔያችን የምንታወቅ ግንባር ቀደም ሀገር ሆነን አንዳንድ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በቀላሉ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንን ጭምር የሚፈታተን ደረጃ የሚደርስበት አንዱና ዋና ምክንያት የጋራ መግባባት ላይ ያልደረስንባቸው በርካታ ነገሮች በመኖራቸው መሆኑንም ይገልጻሉ።

አንዱ የማንግባባበት ጉዳይ ያለፈው ታሪካችን መሆኑን በአብነትነት አንስተው፤ በሀገራችን ታሪክ የሚጻፍበትም ሆነ የሚተረክበት መንገድ ሀገር በሚገነባ አቅጣጫ ሳይሆን ሀገርን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በሚከት መንገድ ነው። ከታሪካችን ጋር ተያይዞ ትናንት በሆነ ጉዳይ መጨቃጨቅ ትተን ከትናንት ትምህርት ወስደን ዛሬን የተሻለ ለማድረግ እና ነገን በትክክለኛ አቅጣጫ ለመጓዝ መግባባት ላይ መድረስ የምንችለው ቁጭ ብለን መነጋገር ስንችል ነው ይላሉ።

የልዩነት ሃሳቦቻችንን ወደ መድረክ አምጥተን ተነጋግረንባቸው መግባባት ካቃተን ሕዝብ ይወስንባቸዋል፤ ሀገር የሚገነባው በዚህ አቅጣጫ ነው የሚሉት ፖለቲከኛው፤ ዛሬ የሚያጨቃጭቁንን፣ የሚያዋጉንን፣ የሚጋጩንን፣ የሚያባሉንን እና እንዳንተማመን የሚያደርጉንን ጉዳዮች በመነጋገር፣ በመወያየት እና በመመካከር በማረም መግባባት ላይ መድረስ ከቻልን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት በሚያስችል አቅጣጫ መጓዝ እንችላለን በማለት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪካችን ሲታይ የጦርነትና የግጭት ብቻ ሳይሆን አኩሪ የሆነ ሥልጣኔ፣ አብሮነት፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና በረጅሙ ታሪካችን ያካበትነው የጋራ ማንነት ያለን ማህበረሰቦች ስለሆንን አለመግባባቶቻችንን በሠለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት አንድነታችንን ማጽናት አለብን ሲሉም ይመክራሉ።

ችግር ውስጥ የገቡ ሀገራት ቁጭ ብለው ተነጋግረው ስህተቶቻቸውን አርመው ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈ ትክክለኛ አቅጣጫ ተከትለው ዜጎች በእኩልነት ኮርተው የሚኖሩበት ሀገር መፍጠር መቻላቸውን አውስተው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የሚዲያ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ምሁራን፣ አሰላሳዮች እና ጸሀፊዎች ብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You