ተመድ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

አዲስ አበባ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርሃ-ግብር (ዩ ኤን ዲ ፒ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት የባለሙያዎች ፎረም ዛሬ ተካሂዷል።

የፎረሙ ሰብሳቢ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፤ ፎረሙ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ልማትን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለምታዘጋጃቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተለይም የቴክኒክ፣ የፋይናንስና ሌሎች የዘርፉን ዓለም አቀፍ ልምዶች በማምጣት በትብብር ለመሥራት ዕድል እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብራቸውንና የፋይናንስ ድጋፋቸውን በዘላቂነት እንዲያጠናክሩ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት። በቀጣይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በብሔራዊ ደረጃ ለምትተገብረው ዕቅድ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለመሸፈን የልማት አጋሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ዕቅዱን ለመተግበር ለአሥር ዓመት 316 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ 253 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የሚገኝ በመሆኑ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የፎረሙ ጸሐፊ የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርሃ-ግብር (ዩ ኤን ዲ ፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራና ሌሎች ዕቅዶች የምታከናውነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።

ዩ ኤን ዲ ፒ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል አረንጓዴ ልማትን ለመገንባት የያዘችውን ዕቅድ እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማስተባበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት በሚከናወኑ የባለሙያዎች ፎረሙ፤ በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የመንግሥት ተቋማት በአንድነት የሚሠሩበት ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 የተቋቋመ ሲሆን፤ በየሦስት ወሩ በመገናኘት በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትግበራ ላይ ውይይት በማድረግ የአፈጻጸም አቅም የሚያጠናክር ነው።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You