በአዲስ አበባ ከተማ በየቀኑ የሚስተዋለው የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይነገራል፡፡ የምርት አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎችም በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ የአትክልት ምርቶች እንኳን ሳይቀር ባልተገባ ሁኔታ ዋጋን ከፍና ዝቅ በማድረግ ውጫዊ ምክንያት ሲያስተጋቡ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች በአዲስ አበባ ከተማ የአትክልት ዋጋ ምን እንደሚመስል በኮተቤ 02 የገበያ ማዕከል፣ በሾላ ገበያና በተለያዩ የሰንበት መገበያያዎች ተዘዋውረው ቃኝተዋል፡፡
በኮተቤ 02 የገበያ ማዕከል የአትክልት ነጋዴው አለባቸው ፋንታው እንደሚናገሩት፤ የገበያ ሁኔታው ከጊዜ ወደጊዜ በመጨመር ላይ ይገኛል፤ በተለይም በዓላት ሲደርሱ የዋጋ ጭማሪው እየተለመደ መጥቷል፡፡ የጭማሪው ምክንያት ወቅቱ የበዓል ሰሞን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፍላጎት በመጨመሩና የአቅርቦት እጥረት በመስተዋሉ መሆኑን ነጋዴው ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ አለባቸው ገለጻ፤ የገበያው ሰንሰለት በመራዘሙ በመሃል የሚገኙ ደላሎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምርቱ እዚህ ከደረሰ በኋላ የወዛደርና ሌሎች ልዩ ልዩ ወጪዎች አሉ፡፡ እንዲሁም የአትክልት ምርቶች በባህሪያቸው የሚበላሹ በመሆናቸው ያንንም ለማካካስ ነጋዴው የዋጋ ጭማሪ ያደርጋል፡፡
ነገር ግን ካለፈው ይልቅ የተወሰኑ መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውን የሚያነሱት አቶ አለባቸው፤ ባለፉት ቀናት የሽንኩርት ዋጋ እስከ 140 ብር የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ከ90 ብር እስከ 120 ብር፣ ቲማቲም ከ60 ብር እስከ 70 ብር፣ እንዲሁም ድንች በአማካይ 25 ብር እየተሸጠ ይገኛል ይላሉ፡፡
ችግሩን ለመፍታት በተለይም በሀገሪቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የነጻ ገበያ ሥርዓት በመሆኑ አቅርቦትን በመጨመር ከፍላጎት ጋር ማጣጣም እንዲሁም የግብይት ሰንሰለቱን ማሳጠር እና ሰላም ማስፈንም ለነገ የማይባል መሆኑን አቶ አለባቸው ያነሳሉ፡፡
በኮተቤ 02 የገበያ ማዕከል ሲሸምቱ ያገኘናቸው አቶ በላይ ቸሩ እንደሚገልጹት፤ በገበያዎች ላይ እየታየ የሚገኘውን ድንገተኛና ጊዜውን ያልጠበቀ የዋጋ ጭማሪ የሚቆጣጠረው አካል በማጣቱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ሕይወታቸውን በአግባቡ መምራት አቅቷቸዋል፡፡
ለቤት አስቤዛ የሚሆኑ የሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንችና ሌሎች የአትክልት አይነቶችን ለመሸመት ወደገበያ መምጣታቸውን በመግለጽ፤ በገበያው ላይ ነጋዴዎች የሚጠሩት ዋጋ ያሰቡትን ያህል ሊያስሸምታቸው እንዳልቻለ አቶ በላይ ይጠቁማሉ፡፡
የመስከረም ወር የበዓል ወቅት በመሆኑ በሁሉም ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ አሳሳቢ ሆኗል የሚሉት አቶ በላይ፤ መንግሥት ሰላምን ለማስፈንና የዜጎችን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ አተኩሮ መሥራት አለበት ባይ ናቸው፡፡
በሾላ ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ማርታ አለማየሁ የአትክልት ገበያው ውድ የሚባል ነው ይላሉ፡፡ ሽንኩርት በ 130 ብር፣ ድንች በ28 ብር፣ ቀይ ስር በኪሎ 50 ብር መሸመታቸውን ገልጸው፤ የሽንኩርት ዋጋ ከዓመት በዓሉ ጨምሮ መመልከታቸው ይገልጻሉ፡፡ ለአዲስ ዓመት ጥራት ያለው ቀይ ሽንኩርት 120 ገዝቼ ነበር ያሉት ወይዘሮዋ፣ 15 ቀን ባልሞላ ጊዜ የ 10 ብር ጭማሪ መታዘባቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
ከበዓል በኋላ ጭማሪ የታየው ሽንኩርት ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ምርቶች ላይ ነው የሚሉት ወይዘሮ ማርታ፤ ቲማቲም በኪሎ 90 ብር እንዲሁም ጥቁር ጎመን ከዚህ ቀደም በመደብ 20 ብር ይሸጥ የነበረው 30 ብር በመሆኑ ሳይገዙ መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡
በሾላ ገበያ የአትክልት ምርት በመሸጥ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሱአድ አብዱል በበኩላቸው፤ ሽንኩርት ከ120 ብር እስከ 135 ብር፣ ቲማቲም 90 ብር፣ ድንች 28 ብር፣ ቀይስር 50 ብር፣ ካሮት 75 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 350 ብር እየሸጥኩ ነው ይላሉ፡፡
ሽንኩርትም ሆነ ሌሎች የአትክልት ምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ያነሱ ሲሆን፤ ለዚህ ደሞ ምክንያቱ ከሚያመጡበት ቦታ የምርቶቹ ዋጋ መጨመሩ አንዲሁም የትራንስፖርትና መሰል ወጪዎች መደማመር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ወይዘሮ ሱአድ፤ ምርቶቹን የሚረከቡት በከተማዋ ካለ የአትክልት ተራ መሆኑን እና የዋጋ መወደድ እንጂ በማንኛውም ምርት ላይ እጥረት አለመኖሩን ጠቁመው፤ ችግሮቹን መፍታት ከተቻለ ዋጋው ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ያመላክታሉ፡፡
ኢፕድ ባደረገው ምልከታ በሰንበትና በመደበኛ ገበያዎች መካከል የዋጋ ልዩነቶች እንደሚስተዋሉ መገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህም ከቋሚ ገበያዎች አንፃር የጥራት ሁኔታው እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ላይ እስከ 40 ብር፣ በቲማትም እስከ 20 ብር፣ በነጭ ሽንኩርት እስከ 80 ብር የሚደርስ የዋጋ ልዩነት ይስተዋላል፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ እና መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም