– መንግሥት የዋጋ ግሽበት ለመከላከል አቅርቦት እንዲኖር ይሠራል
አዲስ አበባ፡- ለ2012 በጀት አመት ከፀደቀው 386 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር የወጪ በጀት ውስጥ፣ለፌዴራል መንግስት የመደበኛ ወጪ109 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 130 ነጥብ 71 ቢሊዮን ብር፣ለክልሎች ድጋፍ 140 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ስድስት ቢሊዮን ብር ሆኖ ተደልድሏል፡፡
በ2012 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ረቂቅ በጀቱም በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡
የገቢ፣በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል መንግስት የ2012 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ ትናንት ለምክር ቤቱ ያቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብን መርምሮ ረቂቅ የበጀት አዋጁ እንዲፀድቅ ባስደረገበት ጊዜ እንደተገለፀው፤ ከአጠቃላይ የፌዴራል መንግስት መደበኛና ካፒታል ወጪ 63 ነጥብ 3 በመቶው ለትምህርት፣ ለመንገድ፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤናና ለከተማ ልማት ተደልድሏል፡፡በመሆኑም በጀቱ በዘላቂ ልማት፣በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን፣ በድህነት ተኮር ክፍላተ ኢኮኖሚና በመሰረተ ልማት አውታሮች ማስፋፋት ተግባራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የተመደበ በጀት ነው፡፡
የካፒታል ወጪዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ለተያዙ ነባር ፕሮጀክቶች ለማሳካት ቅድሚያ በመስጠትና በውጭ ፋይናንስ የሚደገፉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችም የመንግስት ድርሻን ታሳቢ ተደርጎ የተደለደለ ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዳመለከተው፤የ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት የ2011 በጀት ዓመት የወጪ አፈፃፀም ሂደትን በመገምገም የፊስካል ፖሊሲ ዓላማን መሰረት በማድረግ የመንግስት የፋይናስ አቅም ያገናዘበ ነው፡፡ እንዲሁም ራስን የመቻል አቅጣጫን የተከተለ፣የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ድህነት ተኮር ለሆኑ ተግባራት ትኩረትም የሰጠ ነው፡፡
በተጨማሪም የፕሮግራም በጀት አሰራርን የተከተለ፣ለክልል መንግስታትና ለካፒታል በጀት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣በ2012 በጀት ዓመት ለሚተገበሩ ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ቁልፍ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አቅጣጫዎችና ዓላማዎች ማሳካት የሚያስችል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር ህግና ደንብን አክብሮ በመስራት ረገድ በተደጋጋሚ ጉድለት እንዳለ በቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ይህ ግን በ2012 በጀት ዓመት ላይ እንዳይደገም የክትትልና ቁጥጥር ስራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡
በዕለቱ በጀቱን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የዋጋ ግሽበት እንዳይባባስ ምን አይነት ጥንቃቄና እርምጃ ይወሰዳል?ፕሮጀክቶች በጀት ከተመደበላቸው በኋላ ፈጥነው ወደስራ ያለመግባትና ከገቡም በኋላ መጓተት እንዲሁም በተያዘላቸው በጀት ያለመጠናቀቅ ሁኔታ የሚታይባቸው ሲሆን በዚህም ውስን የሆነው ሀብት ስለሚባክን ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በጀታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ቢብራራ?ቀደም ብለው የተጀመሩ መንገዶች እስካሁን ያልተጠናቀቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ቅሬታን እየፈጠሩ ነውና ምን ታስቧል?የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለጥያቄዎቹ መልስ ሲሰጡ እንዳብራሩት፤ዋናው የግሽበት መንስኤ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለው አለመጣጣም ነው፡፡ግሽበት ማለት የመግዛት አቅም ውስንነት ነው፡፡ሰው በአቅሙ ልክ መግዛት እና የዕለት ተዕለት ኑሮውን መግፋት እንዲችል አቅርቦት ላይ መስራት ያስፈልጋል፤ በዚህ ላይ መንግስት አቅርቦት እንዲኖር እየሰራ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም በዘርፉ ያሉ ፖሊሲዎች ግሽበትን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ኢኮኖሚው መሸከም ከሚችለው በላይ የሆነ ገንዘብ በገበያ ውስጥ እንዳይዘዋወር የመቆጣጠር አቅም የሚያስችል ፖሊሲ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት መጠነኛ የሆነ መሻሻል ያለ ሲሆን፣ይህም በቀጣይ የሚጠናከር ይሆናል፡፡
በተጨማሪም የሚፈለገው ምርት በገበያው ላይ እያለ ነጋዴው ግን እጥረት እንዳለ በማድረግ ግሽበት እንዲፈጠር የሚያደርገውን መቆጣጠርም ያስፈልጋል፡፡ በመብራት በኩል የሚፈጠረውንም ችግር በመፍታት እንዲሁም ሎጂስቲኩንና የንግድ ስርዓቱንም በማዘመን ችግሩን ለመፍታት መንግስት የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡
የሀብት ብክነትን በተመለከተ ሲናገሩ፣አገሪቱ ያላት ሀብት ውስን መሆኑን አስታውሰው፤ሁሉም አካል ቢሆን ሌብነትን መጠየፍና መዋጋት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡በተለይ የመንግስትንና የሕዝብን አደራ ወስደው የሚሰርቁ ሰዎች እንዳሉ አመልክተው፤እነዚህን መቆጣጠር የግድ እንደሚል ገልፀዋል፡፡አክለውም መቆጠብንና ወጪ መቀነስ መለመድ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ፕሮጀክቶችን ያለመለገም መስራት ቢቻል አገሪቱ ትልቅ ደረጃ ላይ የምትደረስ መሆኗን ጠቅሰው፤ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፕሮጀክቶችን እንደ ልጅ ተከታትለው ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
በደቡብ ክልል ሀድያ አካባቢና ከወላይታ ሶዶ-ታጫ-ጭዳ-ጅማ መንገድን በተመለከተ የተነሳው አግባብነት ያለው ጥያቄ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ዐብይ፣ ዘንድሮ ከፍተኛ በጀት ከተያዘላቸው ተግባራት መካከል አንዱ መንገድ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ከክልሉ ጋር በመነጋገር አዋጭ በሆነ ልክ መንገዱ እየተሰራ እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡
በዕለቱ ያነጋገርናቸው የምክር ቤት አባላት አቶ ናስር ካንሶ እና አቶ ብርሃኑ አበበ በየበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በጀታቸውን በአግባቡና በቁጠባ እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡በገቢ ማሰባሰቡም በኩል ድርሻቸው ጉልህ በመሆኑ ካለፈው ይልቅ ጠንክረው ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በአንደኛ አስቸኳይ ስብሰባው የ2012 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀትን አዋጅ ቁጥር 63/2011 አድርጎ አፅድቆታል፡፡
አዲስዘመን ሰኔ 2/2011
አስቴር ኤልያስ