አዲስ አበባ፡- ሰኔ 15 ቀን 2011 በአማራ ክልል በተሞከረ መፈንቅለ መንግሥት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመው ጥቃት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን /አዴፓ/ን ለማፍረስ ያለመ መሆኑን የአዴፓ ሊቀመንበር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡ በአሁኑ ወቅትም የአማራ ክልል መንግሥታዊ መዋቅሮችና የአዴፓ አደረጃጀት መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ትናንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ጥቃቱ የክልሉን መንግሥት የማፍረስና ስልጣንን በአቋራጭ የመያዝ ሙከራ ነበር፡፡
ጥቃቱን የፈፀመው ቡድን በባህር ዳር ዙሪያ የሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎችን እንዲሁም የክልሉን ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት፣ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን እና የአዴፓን ፅህፈት ቤትን ለመቆጣጠር ሞክሮ አንደነበርም አቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡
ድርጊቱ ከመፈፀሙ ከቀናት በፊት በባህር ዳር በነበረው ህዝባዊ ውይይት በአመራሮች ዘንድ የተለየ አቋም እንዳልነበር አስታውሰው፤በወቅቱ የክልሉ ህዝብ ከሰላምና ፀጥታ አኳያ ለሚያነሳው ጥያቄ የተሠራው ሥራ በተገመገመበት ወቅት የአቋም ልዩነት አለመኖሩን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ የጥቃት ድርጊቱ ስልጣንን በመፈለግ የተፈፀመ ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሊቀመንበሩ፣በአሁኑ ወቅትም የአማራ ክልል መንግሥታዊ መዋቅሮችና የአዴፓ አደረጃጀት መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ፣ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ በክልሉ የፀጥታ አካላት ብቻ እየተከናወነ መሆኑ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን በክልሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሰበብ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ግለሰቦች እንዳልታሰሩም ጠቁመዋል፡፡
ምርመራው ህግና ስርዓትን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አቶ ደመቀ ጠቅሰው፤ ይህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚደረጉ ጥረቶች በጥንቃቄ መካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ የማቅረቡ ሥራም ህግን የተከተለና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ያከበረ መሆን ይኖርበታል።
ወደህግ የማቅረቡ ሂደት ከበቀል የፀዳ እንዲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ለጥርጣሬ የሚያበቁ ጭብጦችን በአስተውሎት መመልከትና አንድ ተጠርጣሪ በህግ ጥላ ስር እንዲውል ሲደረግ የሚመለከተው አካል እያወቀ መሆን ይኖርበታል፡፡
በአገራዊ ለውጡ አካሄድ ላይ ቅሬታ ያለውም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የተለየ ሀሳብ ይዘው የሚታገሉ ዜጎችን ወደ ወንጀል ድርጊቱ ከማጠጋጋት መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ድርጊቱን ከብሄርና አጠቃላይ ከአማራ ህዝብ ጋር በማያያዝ እየተደረገ ያለው ጥረት መሰረተ ቢስ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የሌላ ፓርቲ አባልም ይሁን ሌላ አካል በድርጊቱ የተሳተፈ ከሆነ በዚህ ላይ መደራደር እንደማይገባና ህግ መከበር እንደ ሚኖርበትም ገልፀዋል።
እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቀት አዴፓ ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት እየሠራ ሲሆን፣ የክልሉ ህዝብ ግለሰቦች በሚፈጥሩት አጀንዳ ሊጠለፍ አይገባውም።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩትን ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።
ጥቃቱን ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በባህርዳር 213 በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በመሳተፍ የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም የክልሉ ልዩ ሃይል አመራር አባላት ፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር የሚመሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች እንደሚገኙበት ከትናንት በስቲያ ምሽት የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር