በዓላቶቻችንን በሕይወታችን ገልጠን እንኑርባቸው

መስከረም ሽቅርቅር፣ ኩንስንስና ደማቅ ወር ነው። አዲስ መንፈስ ብርታት ጉልበት የሚያጋባ ኃይለኛ ወር ነው። ሜዳው ጋራ ሸንተረሩ በአደይ አበባ የሚደምቅበት፤ ክረምቱ ወጥቶ ዝናብ የሚቀንስበት፤ ወንዞች ጎለው ዘመድ ከባዳ የሚገናኝበት፤ እሸት የሚያሸትበት ተስፋ የሚጎመራበት ምትሐታዊ ወር ነው።

የዘመን አቆጣጠራችንን ከተፈጥሮ ጋር የሞሸረ ወር ነው። በእነዚህና በአያሌ ምክንያቶች መስከረምን እወደዋለሁ። በእንቁጣጣሽ 2017ን በአደይ ተቀብለን መስቀል ላይ ደርሰናል። በጋሞ-መስቀላ፣ በወላይታ- ጊፋታ፣ በሐድያ-ያሆዴን እያከበርን ነው። እሬቻም መጣሁ መጣሁ እያለን ነው።

እነዚህን በዓላት ጨምሮ ጥምቀትን፣ ገናን፣ ትንሳኤን፣ ኢድ አልፈጥርን ሆነ መውሊድን እና ሌሎች በዓላትን በአደባባይ በውጭ እናከብራቸዋለን እንጂ በቤታችን በውስጣችን አናከብራቸውም ብዬ አምናለሁ። በእውነት በሕይወታችን አንገልጣቸውም አንኖራቸውም። በዚህ የተነሳ ሙሉዕ አይሆኑልኝም። ሸንግለናቸው አታለናቸው ሸውደናቸው፣ አሹፈን ባቸው ተጠቃቅሰንባቸው፣ ተላልፈን፣ ወዘተረፈ የምናሳልፋቸው ስለሆነ ጥፋተኝነት ይሰማኛል።

ለነገሩ እራሳችንን ነው የምንሸውደውና የምና ታልለው። እንደ ሕዝብም እንደ ሀገርም ይህ ጥፋተኝነት ተሰምቶን እነዚህን የፍቅር የሠላም የይቅር ባይነት የትሑትነት የመስጠትና ራስን ዝቅ የማድረግ በዓላት በሕይወታችን ገልጠን ካልኖርናቸው ዓመት በመጣ በሄደ ቁጥር ብናከብራቸው ምን ትርጉም አለው። ስላቅና ምጸት ካልሆነ በስተቀር። እናም ዛሬም በድጋሚ እንኑራቸው በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እንግለጣቸው እላለሁ። በዚህ አንድምታ ነው እንግዲህ እሬቻን በወካይነት የማነሳው።

እንኳን ለሁሉም በዓላት አደረሰን አደረሳችሁ! አሜን። ከዚህ በቀደመ መጣጥፌ ሦስቱ አብርሃማዊ ዕምነቶች ማለትም ክርስትና፣ እስልምና እና የአይሁድ ዕምነቶችን ከእነ በጎ ባሕላቸው በተለይ ልሒቃን ወይም ጉልሀን ነን በምንል ዕቡያን ባለመገለጣቸው፣ በየዕለት ተዕለት ሕይወታችን ባለመታየታቸው፣ በተግባር ስላልኖርናቸው፣ ከዘመናዊው ትምህርት ጋር መሳ ለመሳ ስላላስኬድናቸው እንዲሁም ከምዕራብም ሆነ ከምሥራቅ እንዳሉ በገለበጥናቸው ርዕዮተ ዓለሞች ስለደፈቅናቸው ሀገራችንን ዛሬ ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ ተዳርጋለች።

ለዚህ ደግሞ ልሒቃን ተብዬዎች በአንድም በሌላ መልኩ ተጠያቂ ነን። በዛሬ መጣጥፌም ልሒቃንን በእርግጥ እሬቻን እንኖረዋለን በሕይወታችን እንተረጉመዋለን ስል እጠይቃለሁ። መቼም አፋችንን ሞልተን እንዴታ አንልም። ሀገራችን የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው የአደባባይ ሐቅ ነውና ።

በተፈጥሮዬ ጨለምተኛ የሚሉት አይነት ሰው አይደለሁም። ሆኖም ባሕላዊ ወረቶቻችንን መኖር በተግባር መግለጥ ካልጀመርን መጭው ጊዜ ከዚህ የከፋ እንደሚሆን እነግራችኋለሁ። ለዚህ ነው ቆም ብለን ከእያንዳንዳችን ዕምነትና ባህል አኳያ ራሳችንን ያለ ርኅራኄ መገምገምና መቤዠት የሚያስፈልገን። ለቀብድ ያህል ይሄን ካልሁ ወደ ገደለው።

ዓለም አቀፉ የእርቅ፣ የሠላም፣ የግልግልና የሽምግልና ረቡኒ (መምህር) ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ “የሠላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች” በሚለው ማለፊያ መጽሐፋቸው የሠላም የእርቅ አድማሶች በማለት በመጀመሪያ ሰው ከራሱ ጋር ከዚያ ከጎረቤቱ፤ ከማኅበረሰቡ ጋር በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር እርቅ፤ ሠላም ማውረድ እንዳለበት ይተነትናሉ። ሰሞኑን የሚከበረው የእሬቻ በዓል ሰው በመጀመሪያ ከራሱ ጋር በመቀጠል ከጎረቤቱ ከዚያም ከተፈጥሮ ጋር የሚታረቅበት ማዕድ ነው።

እሬቻ ሠላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት የሚፈፀምበት በመሆኑ አብሮነትን ስለሚያበረታታ አሰባሳቢ ነው። ጥልን ቂምን ጥላቻን እያራገፈ መልካም መልካሙን ማለትም ሠላምን ዕርቅን የሚያጠናክር ስለሆነ በውስጠ ታዋቂ ሠላምን ይዟል። የኦሮሞ ባሕልና ታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊ ኦቦ ድርቢ ደምሴ እሬቻ ማለት ኦሮሞ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ፈጣሪን የሚያመስግንበት ክዋኔ ሲሆን በሐይቅ፣ በወንዝ፣ በምንጭ ወይም በውሃ ዳርና በተራራ ብቻ የተወሰነ ግን አይደለም ይላሉ።

ልጅ ሲወለድ፣ አዲስ ቤት ሲሠራ፣ ሙሽራ ሲወጣ፣ በዘር ወቅትም፣ ወዘተረፈ እሬቻ ይደረጋል በማለት ከማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ምን ያህል የተቆራኘ እንደሆነ ያስረዳሉ። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኦቦ ሙሉጌታ ደበበ (ፒ ኤች ዲ) በሌላ በኩል እሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ አንጓ ነው ይላሉ። በማሳያነት ከሚጠቀሱት ዓበይት ምክንያቶች ቀዳሚው የሥርዓቱ ክዋኔ በቃሉና በአባ መልካ አጋፋሪነት መመራቱ ነው በማለት በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

እሬቻ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚከወንና የመጀመሪያው በበልግ በተራራ ላይ አምላክን የሚያመሰግንበትና ዝናብ የሚለማመንበት ሲሆን ቱሉ እሬቻ ይሰኛል። ኦቦ ድርቢ ቱሉ እሬቻ መሬት አፏን ከፍታ የበልግ ዝናብን የምትጠብቅበት ወቅት ስለሆነ ፈጣሪን ዝናብ የሚለማመኑበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ። ለምለም ሳርና አበባ ተይዞ በሐይቅ፣ በወንዝ፣ በምንጭ ዳር የሚከበረው የምስጋና በዓል ደግሞ መልካ እሬቻ በመባል እንደሚታወቅ ኦቦ ሙሉጌታ ያብራራሉ።

ፈጣሪ ዝናብ ስለሰጠ ከክረምት ወደ ብራ ስለ አሸጋገረ የሚመሰገንበት እንዲሁም አዝመራው ደርሶ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዲገባ የሚለመንበት መሆኑን አክለው ይገልጻሉ። በፕሮፌሰር የሠላም አድማስ እይታ መሠረት እሬቻ ሦስቱንም የሠላም አለባውያን በአንድነት የያዘ የእርቅ፣ የሠላም ገበታ ነው ማለት ይቻላል። ጥያቄው እየኖርናቸው ነው ወይ!? የሚለው ነው። ለማንኛውም ሦስቱን የሠላም አድማሶች ከእሬቻ እሴቶች አንጻር አንድ በአንድ እናመሳክር፦

1ኛ . ከራስ ጋር ሠላም ፤

ዓለም አቀፍ አሸማጋይ እና የሠላም አባት ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ከፍ ብሎ በጠቀስሁት መጽሐፋቸው ገጽ–102 ላይ “ውስጣዊና መንፈሳዊ ሠላም ከራስ ጋር ሠላም ማውረድ፣ መታረቅ ነው። ከፈጣሪ ጋር ሠላም ከማውረድ ጋር ትስስር አለው። ውስጣዊ ሠላም ከሌሎች ጋር ለሚመሠረት ሠላም ወሳኝ ነው። ውስጣዊ ሠላም ያለው ሰው ምን ያህል ከሌሎች ጋር በሠላም እንደሚኖር እና ሠላም እንደሚያካፍል ይታወቃል። ውስጣዊ ሠላም ያላቸው ሰዎች አስታራቂና ሠላም ገንቢም ናቸው። ሠላማቸው ወደሌሎች ይፈሳል። ከራሱ ጋር የታረቀና ውስጣዊ ሠላም ያለው ሰው የሕይወትን መስተጋብር የተገነዘበ ስለሆነ ከማኅበረሰቡና ከተፈጥሮ ጋርም ሠላምና እርቅን ያወረደ ነው። ከራስ ጋር የሚፈጠር ሠላም ለሠላም አድማሶች መነሻም ውጤትም ነው። …”

እሬቻ ከመደረጉ በፊት ከራሱ ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር የተቀያየመ የተጋጨ ካለ እንዲወጣ ሽማግሌዎች በኦሮሞኛ “እውነትን ከአምላክ ፆታን ከምድር መደበቅ አይቻልም። በውሻም ሆነ በልጅ ምክንያት የተጋጨ ካለ ከፈጣሪ ጋር እንዳያቀያይመን ይውጣ” በማለት እንደሚያግባቡ ይህን ሳያደርጉ ቢቀሩ ደግሞ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደሚያስወቅሳቸው ኦቦ ድርቢ ያስረዳሉ። የሀገር ሽማግሌዎች ቢያንስ በመጋቢትና በመስከረም በዓመት ሁለት ጊዜ እርቅ የማውረድ የመሸምገል አጋጣሚ እንዳላቸው ይገልጻሉ። ሰሞኑን የሚከበረው መልካ እሬቻም ሆነ በወርሐ መጋቢት የሚከበረው ቱሉ እሬቻ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከራስ ጋር መታረቅ ሠላም ማውረድ ማኅበራዊ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና በዓሉ ቤትን ራስን በእርቅ የማፅዳት፤ የጥል ግድግዳን የማፍረስና ፋይል ዘግቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሻገሪያ ድልድይ መሆኑን ኦቦ ሙሉጌታ አክለው ያብራራሉ።

2ኛ . ማኅበራዊ ሠላም፤

ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ ስለ ሁለተኛው የሠላም አድማስ ገጽ– 103 ላይ “ማኅበራዊ ሠላም ከራስ ጋርና ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረግ ሠላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ይህ ማለት ግን ማኅበራዊ ሠላም ከሌለ ውስጣዊ ሠላም አይኖርም ወደሚል መደምደሚያ አያደርስም። ሆኖም ብጥብጥና ሁከት ባለበት ውስጣዊ ሠላምን ማስፈንንም ሆነ ማስቀጠልን ፈታኝ አያደርገውም ማለት አይደለም። ሌላው ማኅበራዊ ሠላም ከተፈጥሮ ጋር ከሚደረገው ሠላም ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን መገንዘብ ነው። ግጭትና ጦርነት በተደጋጋሚ የተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ስለሚጎዳ ደኑም ስለሚጨፈጨፍ አካባቢው ይራቆታል። በዚህም ሥነ ምሕዳሩ ስለሚዛባ የከባቢ አየር ለውጥን ያስከትላል። ለዚህ ነው የማኅበራዊ ሠላም መኖር ለፍጥረትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና ተደርጎ የሚወሰደው። “ፕሮፌሰር እንደሚሉት ከራስ ጋር የሚፈጠር ውስጣዊ ሠላም ከጎረቤትና ከማኅበረሰብ ጋር የሚደረግ እርቅ መሠረት ነው። በእሬቻ ለመታደም ከራስ ጋር መታረቅ ማኅበራዊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከራሱ ጋር ሠላም ያለው ደግሞ ከጎረቤቱ ጋር የመጋጨት አጋጣሚው ዝቅተኛ ነው።

ሆኖም ከጎረቤቱ ጋር ወይም ከሌላ ሰው ጋር ግጭት ቢፈጠር የሀገር ሽማግሌዎች በቱሉ ወይም በመልካ እሬቻ የማስታረቅ መልካም አጋጣሚም ኃላፊነትም ስላለባቸው ማኅበራዊ ሠላምን ከመታወክ ይታደጉታል። ለዚህ ነው የሥነ ማኅበረሰብ አጥኚዎች መጀመሪያ ከራስ በመቀጠል ከጎረቤት ጋር የሚፈጠር ሠላም ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረስ ሠላም መደላድል እንደሆነ የሚያስረዱት። ታላቁ መጽሐፍስ “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።” አይደል የሚለው! ?

3ኛ . የተፈጥሮ ሠላም፤

ፕሮፌሰር በገጽ–104 ላይ “የተፈጥሮ ሠላም ከማኅበራዊ እና ከውስጣዊ ሠላም ጋር ጥብቅ ትስስር አለው። ከተፈጥሮ ጋር ሠላም፣ እርቅ ማውረድ አካላችን ከታነፀበት ምድር ጋርም መታረቅ ነው። ከተፈጥሮ፣ ከዩኒቨርስ ሥርዓትና ኃይል ጋር መንሰላሰል የውስጣዊ ሠላም ምንጭ ነው። …የተፈጥሮ ፍቅርና እንክብካቤ ለማኅበራዊ ሠላም መስፈን የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

“እሬቻ ከሁለቱ የሠላም አድማሶች ይልቅ ከተፈጥሮ ጋር ለሚደረግ እርቅ ያደላል ቢባል ማጋነን አይሆንም። በቱሉ እሬቻ ፈጣሪውን ለበልግ እርሻ፣ ለከብቶች ግጦሽና ለውሃ ዝናብ የሚለምንበት መሆኑ መልካ እሬቻው ደግሞ ፈጣሪው ዝናብ ስለሰጠው፣ ከክረምት ወደ ብራ ስላሸጋገረው የሚያመሰግንበት በሌላ በኩል ያልተሰበሰበውን እህል በአደራ የሚሰጥበት የአምላክን ጥበቃ የሚለማመንበት መሆኑ በተለይ ለምለም ሳርና አበባ ይዞ ውሃ ዳር ፈጣሪ የሚመሰገንበት መሆኑ ከተፈጥሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ያሳያል።

ይሁንና እሬቻ ደረጃው፣ ስፋቱ፣ ጥልቀቱ በየሠላም አድማሱ የተለያየ ቢሆንም ሰው ከራሱ፣ ከጎረቤቱ በመጨረሻም ከተፈጥሮ ጋር በአንድ የእርቅ፣ የሠላም፣ የመቀባበል፣ ወዘተ . ማዕድ ቀርቦ የሚቋደስበት ስለመሆኑ አያጠያይቅም።

ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ”…በተለያዩ ማኅበረሰቦች ሀገር ግንባታ Nation Building በመሐላቸው ያለውን ልዩነት አጥብቦ ግድግዳዎችን አፍርሶ የጋራ ማንነት መገንባት ነው። …” ይላሉ። የሀገር በቀል እውቀቶችና የባሕል ተመራማሪው አቶ አብዱልፈታህ አብደላ ይሄን የፕሮፌሰር ሀሳብ ይጋራሉ።

በዓሉ በአዲስ አበባ ሌሎችን የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሳተፈ አግባብ መከበሩ ለሀገረ ግንባታ መሠረት ጥሏል ማለት ይቻላል ሲሉ ዘላቂ ፋይዳውን ያመላክታሉ። የጋራ የሆኑ እሴቶችን ባሕሎችን እያጎለበትን እያሳደገን በሄድን ቁጥር መተዋወቅ፤ መከባበር፤ መቀባበል ስለሚጨምር እኔነት በእኛነት እየተተካ ስለሚሄድ ለሀገርም ሆነ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እርሾ እንደሚሆን ተመራማሪው ያስረዳሉ።

ዛሬ ከምንገኝበት መንታ መንገድ ላይ የደረስነው ባሕሎቻችንን እሴቶቻችንን ለሀገረ መንግሥትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ባለማዋላችን ነው ሲሉ አቶ አብዱልፈታህ ይሞግታሉ። ኦቦ ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓሎቻችን፣ እሬቻ፣ ሻደይ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጨምበላላ፣ ጊፋታ፣ ወዘተረፈ አንድ የሚያደርጉን ባሕሎች በበዙ ቁጥር ኢትዮጵያዊነታችን ይጠናከራል። ከተገኘንበት ብሔር ይልቅ ኢትዮጵያዊነታችን እየገዘፈ ይሄዳል። እየተዋሓድን፣ እየተቀባበልን፣ እየተከባበርን በሄድን ቁጥር እየተዋደድን እንሄዳለን አንድነታችንም በዚያው ልክ ይጎለብታል ሲሉ ይጠቁማሉ።

እንደ መውጫ

መስቀልንም ሆነ እሬቻም ወይም ጊፋታ፣ መስቀላዮም ሆነ ፍቼ ጨምበላላ አሸንዳ ሻደይም ሆነ ሶለል፣ ወዘተረፈ ሲከበሩ በተቻለ መጠን ከፖለቲካዊ አንድምታ ጋር ላለማቆራኘት ጥረት ሊደረግ ይገባል። በተወጠረች ፖለቲካዊ ገመድ በጥበብ በማስተዋል መጓዝ ግድ ይለናል። እሴቶቻችን ባሕሎቻችን በራሳቸው ሙሉ፣ ጮኸው የሚናገሩ፣ ከሩቅ እንደ ቀስተ ዳመና ደምቀው የሚታዩ ስለሆኑ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ማጋጌጪያ አያሻቸውም። ቱባ መሆናቸው በራሱ ሙሉዕ አድርጓቸዋልና። አቶ አብዱልፈታህ እሬቻ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ይዞልን የሚመለሰው ምስጋናን፣ ይቅርታን፣ ሠላምንና አንድነትን እንጂ ሌላ አጀንዳን ሊሆን አይገባም ይላሉ።

ሆኖም የክልል ሰንደቅ ዓላማ እና የፓርቲ ዓርማ በማንገብ ፖለቲካዊ ቡልኮ መደረቡ ተገቢ አይደለም። ይህ ከእሬቻም ሆነ ከሌሎች በዓላት እሴቶች ጋር የሚጣረስ ከመሆኑ ባሻገር አቃፊነቱ ላይ ጥያቄ፣ ብዥታ፣ ግርታ ሊያስነሳ ይችላል። ከባሕላዊ፣ እሴታዊ አንድምታው ይልቅ ፖለቲካዊ ቱማታው ላይ ጊዜያዊ ነጥብ ለማስመዝገብ የሚደረግ መሽሎክሎክ ፊት ሊነሳ ይገባል።

ከሀገራዊ፣ ከቀጣናዊ፣ ከአሕጉራዊና ከዓለም አቀፋዊ ስትራቴጂና ሕልማችን አንጻር አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖረው ሃይማኖትንና በዓላትን ለአማኙና ለተከታዩ መተው ሊበረታታ ይገባል። በነገራችን ላይ ሃይማኖትንና ባሕልን ከፖለቲካ ጋር የማጣቀስ አባዜያችን ትናንት የተጀመረ አይደለም። የዋለ ያደረ አባዜ እንጂ። ይህ ቅርሻ በዜጎች መካከል መጠራጠርን፣ ልዩነትን የሚያነብር ስለሆነ ሰከን ብሎ ማሰብ ይገባል። ለብሽሽቅ፣ ለእልህ ፖለቲካ በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ ማድረግም ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ላልገነባች ሀገርና ሕዝብ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት Po­litical Correctness የልብ ትርታዋ ሊሆን በተገባ። ሆኖም በገዥው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍ ወለምታ፣ ግራ ቀኙን ካለማመዛዘን፣ የመራጭን constituncy ቀልብ ለመግዛት፣ “የአንቂን” Activist ቡራኬ ለማግኘት የሚፈፀሙ ፖለቲካዊ ስህተቶች ሀገርን ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉዋት ኖረዋል።

አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ለጭብጨባ ተሟጋች ነን ባዮች ለሰብስክራይብና ለላይክ ሲሉ በስሜት ከመጋለብ ዛሬም ራሳቸውን በልጓም፣ በልባብ ሊገቱ ይገባል። ቢዘገይም አልረፈደም። ወደ መነጋገሪያው ቀርቦ አንደበትን ከመክፈት በፊት ሁለት ሦስቴ ማሰብና ከስሜታዊነት መታቀብ ያስፈልጋል። ገና ብዙ ያልተሻገርናቸው ሸለቆዎች፣ ገደሎች አሉብንና በእንቅርት ላይ … እንዳይሆን አበክረን ልንጠነቀቅ ይገባል ።

ከጊዜያዊ ድል ዘላቂውን የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ማስቀድም ትልቁን የተስፋ ስዕል አሻግሮ ማየት ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ እሬቻንም ሆነ መስቀልን በዓመት አንድ ጊዜ በአደባባይ ማክበር ብቻ ሳይሆን በዕለት ተዕለት ኑሯችን እንተርጉማቸው። እንኑራቸው። በልካቸው እንገኝ። ልካቸው ሠላም፣ እርቅ ፣ ይቅርታ፣ መቀባበል፣ መግባባት፣ አብሮነት፣ አንድነትና ሰው ሆኖ መገኘት ነውና።

ፈጣሪ የከርሞ ሰው ይበለን ! ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም  (ሞሼ ዳያን ) fenot1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You