የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ሒሳብ ሠራተኛዋ ወይዘሮ ትርንጎ ጌጡ ኮሚሽኑ በከፈተው የህፃናት ማቆያ ልጃቸውን ማዋል ከጀመሩ ወደ ሦስት ወር ሆኗቸዋል፡፡ አገልግሎቱም 5ርካታቸውን ይናገራል፤ ከሥራ ከማርፈድም ሆነ መቅረት እንዲሁም ይደርስባቸው ከነበረው ድካም ታድጓቸዋል ፡፡
ልጃቸውን ይዘው ወደሥራ ቦታ ሲመጡ ትራስፓርትም መመቻቸቱን ይገልጻሉ። አገልግሎቱ የቤት ሠራተኛ አጥተው የሚንገላቱትን እናቶች መታደጉን፣ ልጆቻቸውንም በቅርብ መከታተል እንዲችሉ አስተዋጽኦ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡
የኮሚሽኑ የሪከርድና ማህደር ሠራተኛ ወይዘሮ ሸዋዬ ዓለሙ በእናትነታቸው ሳቢያ ከሥራ ሳይቀሩ ልጃቸውን በመስሪያ ቤቱ የህፃናት ማቆያ አስቀምጠው በሰዓቱ ጡት እያጠቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ‹‹ልጄን ቤት ትቼ ብመጣ ተረጋግቼ አልሠራም፤ በልጄ ምክንያት አርፍጄ ስመጣም እሳቀቅ ነበር›› ይላሉ።
የኮሚሽኑ የህፃናት ማቆያ ሞግዚት ወይዘሪት ትዕግስት ዮሃንስ ህጻናቱን በሰአቱ እንደሚመግቧቸውና እናቶችም እየመጡ እንደሚያጠቡ ይገልጻሉ፡፡ የተሟላ መጫወቻም እንዳለም ጠቅሰው፣ እናቶቻቸውን እንደማያስታውሱም ይናገራሉ። የሰባትና ስምንት ወር ህፃናት ካልሆኑ በስተቀር የተቀሩት ገና ወደ ማቆያው ሲገቡ እንደሚደሰቱ ያብራራሉ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የጽህፈት ሥራ ባለሙያዋ ወይዘሮ ወይንሸት አበበ የህፃናት ማቆያ በመሥሪያ ቤታቸው በመከፈቱ በጣም ተደስተዋል፡፡ ይህም ተግባር ህጻን ከእናቱ ጋር እንዲውል የማድረግ ያህል መሆኑንም ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ እናቶች በየሰዓቱ ልጆቻቸውን ማየትና ማጥባት ይችላሉ፡፡ ከቤት ሠራተኛ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግርም ይቀርፋል። ስራንም በአግባቡ ለመስራት ያግዛል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም በዚህ ትልቅ ባለውለታ መሆን ችሏል።
እንደ ወይዘሮ ወይንሸት ገለጻ፤ ለህጻናት ማቆያው አራት ሞግዚቶች ተቀጥረዋል። ወላጆች ምግብ ያመጣሉ፣መኝታና መጫወቻ በመሥሪያ ቤቱ ተሟልቷል። አንድ ነርስ የተመደበች ሲሆን፣ ህጻናቱ የጤና ችግር ሲጋጥማቸውም የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ተደርጎ ወደ ጤና ተቋም ለህክምና ይወሰዳሉ።
‹‹ከጸሀፊ ደመወዝ ላይ ለቤት ሠራተኛ ከ1ሺ500 እስከ 2ሺ ብር ከፍዬ ሠራተኛ መቅጠር አልችልም፡፡›› የሚሉት ወይዘሮ ወይንሸት፣ የህፃናት ማቆያው ባይከፈት ሥራቸውን ትተው ቤት ሊቀሩ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት፡፡
ቤት መዋል ደግሞ ገቢም እንደሚያሳጣ ጠቅሰው፤ ሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ይሄንን ተከትለው የህፃናት ማቆያ ቢከፍቱ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ። እናት ከልጇ ጋር ስትውል መንፈሷ እንደሚታደስም ያስረዳሉ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት፤ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወይዘሮ የሻረግ ነጋሽ፣ ‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን የጀመረው ሴት ሠራተኞች ሥራቸውን ተደላድለው እየሰሩ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው›› ይላሉ፡፡
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ አገልግሎቱ ከተጀመረ ሦስት ወር ይሆነዋል፡፡ ህፃናት ለማምጣትና ለማቆየት የተመዘገቡት 48 ቢሆኑም፤ ወደ 16 ያህል ህፃናት በማቆያው እየተገለገሉ ናቸው፡፡ በአገልግሎቱ አቅራቢው ለሚገኝ አንድ ተጠሪ መሥሪያ ቤትም አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡
አራስ ህፃናትን ቤት ጥለው በጠዋት የሚገቡ የጽዳት ሠራተኞች እንዳሉም ጠቅሰው፤ እነዚህ እናቶች ከማለዳው 12 ሰዓት ልጆቻቸውን ይዘው እንደሚመጡና ልጆቹን ሞግዚቶች በፈረቃ ቀድመው እየገቡ እንዲቀበሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ይጠቅሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ለህፃናት ማቆያው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋም የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት 64ሺ532ብር የሚያወጣ የልጆች የመጫወቻ ቁሳቁስ እገዛ አድርጓል። የኢትዮዽያ ሴቶች ጤና ማኅበር ‹‹አጋርነት ለለውጥ›› ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር አጠቃላይ ደረጃውን የጠበቀ ግብአት በማሟላት ሞግዚቶችን ከመቅጠር ጀምሮ በገንዘብ ሲተመን ወደ 300ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል። ትምህርት ሚኒስቴርም ከ250ሺ ብር በላይ ለቁሳቁስ ግዥ አውጥቷል።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ታደሰ እንደሚሉት፤ የህፃናት ማቆያ አገልግሎት ለመጀመር ትልቅ ተግዳሮት አጋጥሞ ነበር፡፡ ተቋሙ በኪራይ ቤት ያለና በርካታ ሠራተኞች ያሉት እንደመሆኑ ለህፃናት ማቆያ እንዲሆን የሚያደርገው ክፍል አልነበረውም።
አንድ ሚኒስትር ሲጠቀሙበት የነበረ በጣም ትልቅ ክፍል ለህፃናት ማቆያው አገልግሎት እንዲውል በመወሰኑ ችግሩ ተፈትቷል። በዚህ በኩል አመራሩ ያሳለፈው ውሳኔ ሊደነቅ ይገባል፡፡ ወደ ሥራ ከተገባም ሁለት ወር ይሆናል፡፡
በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48 ንዑስ አንቀፅ 6 ላይ ‹‹ማንኛውም የፌዴራል መንግሥት ተቋም ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ልጆቻቸውን ጡት የሚያጠቡበትና በቅርበት ክትትል የሚያደርጉበት የህፃናት ማቆያ ማዘጋጀት አለበት›› በሚል ደንግጓል።
‹‹ይሄን መሠረት በማድረግ የፌዴራል ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የአፈፃፀምና የአሠራር መመሪያውን የማውጣት ሥልጣን በአንቀፅ 68 ንዑሰ አንቀፅ 6 ላይ ተሰጥቶታል። በዛ መሠረት ዝርዝር መመሪያ አውጥቶ ሁሉም የፌዴራል መንግስት ተቋማት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ በዚህ መሰረት ይህን መተግበር ጀምረነዋል›› ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹መጋዘን የነበሩ ፍሪጅ፣ ቴሌቪዥን ዓይነት ዕቃዎች ለህፃናት ማቆያው ክፍል ወስደን የሌሉ ዕቃዎች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ ግዢ ፈፅመናል፡፡›› የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ በዋናነት ሥራውን ለመጀመር የአመራር ቁርጠኝነት ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ይገልጻሉ፡፡ በአገልግሎቱ መጀመር የተቋሙ ሠራተኞች ከብዙ ወጪ መዳናቸውንና በኢኮኖሚም እንደተደገፉ አድርገው እንደሚያስቡት ይገልጻሉ።
ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ መስሪያ ቤቱን የለቀቁ እናቶች እንዳሉም ጠቅሰው፤ እነዚህ እናቶች የትዳር ጓደኛ ወይም የሌላ አካል የኢኮኖሚ ጥገኛ ለመሆን የተገደዱበት እንዳለም ይገልጻሉ። ከ51 በላይ የፌዴራል ተቋማት እነርሱ ያላቸውን ተሞክሮ መጋራታቸውን ያብራራሉ።
በዋናነት ይህን አገልግሎት ለመጀመር ድጋፍ የሚያደርገው የፌዴራል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ነው። ከ170 በላይ የፌዴራል ተቋማት ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የህፃናት ማቆያ የሚጠይቀው የሥራ መደቦች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ረዳት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ማሞ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ መከፈት የእናቶችንና የህፃናትን መብት ከመጠበቅ አኳያ ፋይዳ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ መስሪያ ቤቱ ለአገልግሎቱ ሦስት ሠራተኛ መቀጠሩንም ጠቅሰው፤ የህፃናት ማቆያውን ለማዘጋጀትና ቁሳቁስ ለማመቻቸት ወደ 300ሺ ብር ወጪ መሆኑን ይገልጻሉ። አገልግሎቱ ከተጀመረ ወደ አንድ ዓመት እንደሆነውና በመሃል ለሦስት ወራት ያህል ለዕድሳት ተቋርጦ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት የ2012 በጀት ዓመት በጀት የፀደቀ ሲሆን፣ በወቅቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የሴቶች ተጠቃሚነትን የሚመለከት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ከሚችሉ ተግባራት መካከል አንዱ በቅርቡ በየሴክተር መስሪያ ቤቶች እየተቋቋሙ ያሉ የሕፃናት ማቆያዎች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ካሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል አሥሩ የሚመሩት በሴቶች ቢሆንም፤ ይህንን ማቆያ በማቋቋሙ ረገድ ግን ትጋት እንዳልታየባቸው አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ