የወጣቶች ተሳትፎ በአደባባይ በዓላት

በሀገራችን በአደባባይ በርከት ያለ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ ተሰብስበው በሕብረት ከሚያከብሯቸው ሀይማኖታዊ እና ባሕላዊ የታሪክ ዳራ ያላቸው በዓላት የአዲስ ዓመትን ተከትለው በዚህ የመስከረም ወር ላይ ይከበራሉ። የመስቀል ደመራ በዓል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ የሚከበር አንደኛው በዓል ሲሆን ሀይማኖታዊ ዳራውን ተከትሎ በየዓመቱ በጉጉት እና በድምቀት ይከበራል።

ባሕላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ ደግሞ የመስቀል በዓል በደቡቡ የሀገራችን ክፍል የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን ወላጆች በናፍቆት በተለያየ ቦታ ያሉ ልጆቻቸውን የሚጠብቁበት ልጆችም ለዓመት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ለቤተሰቦቻቸው ስጦታ ይዘው ከያሉበት በዓሉን አስታከው የሚሰባሰቡበት ነው። በመስከረም ወር በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው ሌላኛው በዓል እንዲሁ የኢሬቻ በዓል ነው። ባሕላዊ ትውፊት በጠበቀ መልኩ የበዓሉ ተሳታፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ያከብሩታል። የመስቀል ደመራ በዓል እና የኢሬቻ በዓል ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቤታቸው ወጥተው በአደባባይ የሚያከብሯቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ጎብኚዎችን ጭምር ወደ ሀገራችን እንዲመጡ የሚጋብዙም ጭምር ናቸው ።

በዚህ በዓል ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ሚና ምን መምሰል ይገባዋል ፣ በዓሉን እንደከዚህ ቀደም ታሪኩን እና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ ይጠናቀቅ ዘንድ ወጣቶች የሚያደርጉትን ዝግጅት በተመለከተ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሀፊ ከሆነው ወጣት ይሁነኝ መሀመድ ጋር ቆይታ አድርገናል። ማህበሩ ከተመሰረተ 26 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ ‹‹ሀገራችን ካሏት ሀይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ ትውፊት ያለው አንዱ በዓል የመስቀል ደመራ በዓል ሲሆን የኢሬቻ በዓልም እንዲሁ ሌላኛው ነው። እነዚህን በዓላት እንደ ሀገር እና እንደ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን በዩኔስኮ የተመዘገቡ ጭምር በመሆናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት ያገኙ ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው።›› እነዚህን በዓላት ታዲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ ያደረጋቸው የራሳቸው የሆነ መለያ ያላቸው በመሆኑ በትልቅ ትኩረት እና ከፍታ ይዘታቸውን እንደጠበቁ እንዲከበሩ ማድረግ የሁሉም ማኅበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ዋና ጸሀፊው ወጣት ይሁነኝ ገልፇል ።

በእነዚህ በዓላት ላይ ወጣቶች የሚያከብሩበት መንገድ ትኩረትን የሚስብ ሲሆን በበዓሉ እለት ወጣቶች የሚኖራቸው ሚና ከፍ ያለ እንደሚሆንም አክለው ገልጸዋል። ‹‹ወጣቶች የትላንት ታሪክን ወደ ዛሬ የሚያሻግሩ፣ የዛሬን ደግሞ መሰረት ሆነው ጠብቀው አቆይተው ለነገው ትውልድ የሚያስተላልፉ ናቸው።›› በመሆኑም በዚህ ሂደት ወጣቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ማኅበሩ ማኅበራዊ ጉዳይ ብሎ ባስቀመጠው ክፍል ሀገራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ባለፈ ወቅታዊ ኩነቶች ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

 

በ2017 ዓ.ም ተከብሮ በዋለው የደመራ ስነ-ስርዓት እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል በድምቀት ተከብሮ እንዲውል ከእለቱ አስቀድሞ እና በበዓሉ እለት የሚያስተባብሩ በርካታ ወጣቶችን ማኅበሩ ማደራጀቱን ወጣት ይሁነኝ ይገልጻል። ‹‹ለመስቀል የደመራ በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ የሚከበርበትን ቦታ ከማጽዳት እና ለበዓሉ እለት ዝግጁ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ወጣት የሚሳተፍበት ነው። የመስቀል ደመራ በዓል በርካታ ቁጥር ያለው ምዕመን የሚሳተፍበት እንደመሆኑ ከሚመለከታቸው የመንግስት የሰላምና ጸጥታ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የጸጥታ ስጋት ሳይኖር እንዲከበር እናደርጋለን።›› በዚህም በዓሉ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የእምነቱ ተከታዮች ወደ አደባባይ በመውጣት የሚያከብሩት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማም በመስቀል አደባባይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች እና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች ባሉበት ይከበራል። ማኅበሩ በእለቱ በዓሉን ለማክበርና ለማድመቅ ወደቦታው ከሚሰባሰቡ የተለያዩ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት የእምነት ተቋማት፣ የተለያዩ ደብሮች የሚመጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሀይማኖት አባቶች ጋር የበዓሉ አከባበር ምን መመስል ይገባዋል የሚለውን ውይይት አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ከተመሰረተ 26 ዓመት ማስቆጠሩን የገለጸው ዋና ጸሀፊው ከማኅበሩ ውጪ ያሉ ወጣቶችን ጭምር ባሳተፈ መልኩ ውይይት በማድረግ በዓሉ ተከብሮ እንዲያልፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ‹‹ በመስቀል አደባባይ ከሚከበረው በዓል እንዳለ ሆኖ በየአከባቢው ትልቅ ቁጥር ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በጋራ ሆነው ያከብራሉ። በየአከባቢው በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ የሚሳተፉ ወጣቶቻችንን ደልድለናል።›› የአከባቢውን ሰላምና ጸጥታ የሚያናጉ በየአከባቢያቸው እንደ ወጣት ይሁነኝ ገለጻ ይህንን የመስቀል ደመራ በዓል እና ኢሬቻ የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ጊዜ ወጣቶች የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ በተጠበቀ መልኩ እንዲከበር ከበዓሉ ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ሚናቸውም ከፍ ያለ ይሆናል በማለት ገልጸው፤ ይህ እንቅስቃሴም ሆነ የወጣቶች ተሳትፎ ግን የመንግስትን ሚና በመተካት ሳይሆን ነገር ግን ሰላምና ጸጥታ በተረጋገጠባት ከተማ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በቀጣይ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን፣ ማኅበራዊ ተሳትፏቸው እና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው የሚያሳድጉበት ነው።

ደመራ በሚደመርባቸው አካባቢዎች ከኤሌክትሪክ ቦታዎች ተቀጣጣይ ነገሮች የራቀ እንዲሆን አደጋ እንዳይፈጠር እንዲሁም ከአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን ይሰራሉ ።

ሌላኛው ከዚህ በኋላ በቅርብ ቀናት ውስጥ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ነው። ‹‹የኢሬቻ በዓል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን አዲስ አበባ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው። በመሆኑም የኢሬቻ በዓል የሚከናነወንበትን ቦታ በማጽዳት ለበዓሉ ዝግጁ እንዲሆን የማድረግ ስራዎችን እንሰራለን።›› ያለው ወጣት ይሁነኝ የበዓሉ ተሳታፊዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ አጎራባች በዓሉን ለመታደም የሚመጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶች ወደ ከተማዋ የሚመጡበት በመሆኑ ማኅበሩ በሚያሰማራቸው ወጣቶች በዓሉን ለመታደም ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች ሳይቸገሩ ወደሚከበርበት ቦታ እንዲደርሱ የማመላከት ፣ በዓሉ የሚከበርበትን ዓውድና ዐላማ በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ከሸገር ከተማ አስተዳደር ፣ ከኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ እንዲያልፍ እየሰሩ መሆናቸውን አክሏል።

እነዚህ ሁለት በዓላት በዩኔስኮ የተመዘገቡ መሆናቸው ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች በዓሉን ለመመልከት ለመታደም ወደ ሀገር የሚገቡበት በመሆኑ እንግዶችን ተቀብሎ ከማስተናገድ አንጻር ምን ስራዎች በማኅበሩ በኩል ይሰራል ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ዋና ጸሀፊው ይህን ምላሽ ሰጥተዋል። ‹‹ በዓላትን ለመታደም ወደ ሀገራችን የሚመጡ እንግዶችን ባሰቡት መልኩ በዓሉን እንዲያከብሩ እና ማየት የሚፈልጉትን አከባበር እንዲያዩ ማድረግ ዋነኛው ስራ ነው ፤ ምክንቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘገብ ያደረገው የበዓሉ አከባበር ስለሆነ ከዛ በመቀጠል፣ ንብረታቸው ባልሆኑ አካላት እንዳይወሰድ የማድረግ ስራ እንሰራለን ፡ በኢሬቻ በዓል የተለያዩ ኅብረተሰቦች ከክልል ስለሚመጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ከሚሰጡ ሆቴሎች፣ የንግድ ማዕከላት ጋር ካለፈው ዓመት ልምድ በመነሳት እና የነበሩ ክፍተቶችን በማስተካከል እንዲስተናገዱ በማድረግ እኛም ደግሞ መተላለፊያ ቦታዎች ላይ በመገኘት ቦታዎችን በመጠቆም፣ በክብረ በዓሉ ላይ የራሳችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ››

የኢሬቻ በዓል በዓሉን በሚያከብሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለዓመታት እየተከበረ እና ዛሬ የደረሰ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አግኝቷል። ከዚህ ቀደም ባለፉት ዓመታት የነበረው አከባበር በተሳካ ሁኔታ ተከብሮ ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮ ዓመትም ለዚህ በዓል በድምቀት መከበርም ከሚሰሩ የመንግስት አካላት ጋር ማኅበሩ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሀፊ ይሁነኝ መሀመድ ገልጸዋል።

ሀገራችን በአሁን ሰዓት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ጥያቄዎች የውስጥም ሆኑ የውጭ ከሚመጡ ችግሮችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች ያለው የማህበሩ ዋና ጸሀፊ እንዚህን ችግሮች ለመፍታት እንደ መስቀል ደመራ በዓል እና ኢሬቻ በዓላት የሚፈለጥሩልንን እድሎች በመጠቀም አንድነታችንን፣ ሕብረብሄራዊነታችንን፣ ውስጣዊ ሰላማችንን መጠበቅ እንችላለን ያሉ ሲሆን ‹‹እነዚህን በዓላት እና ሁነቶች በመጠቀም ያልተገቡ ተግባራትን የሚፈጸሙ ክፍሎች መጠቀሚያ የሚያደርጉት የወጣቱን ክፍል በመሆኑ ወጣቶች ይህንን ተረድተው ለራሳቸው በመቆም እና መሰል ድርጊቶችን በመከላከል ራሱን እና አካባቢውን በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በመወጣት እነዚህን እና ሌሎች ሀይማኖታዊም ሆኑ ባኅላዊ ትውፊት ያላቸውን በዓላት በሰላምና በድምቀት ማክበር እና አንድነታችንን ማጠንከር እንችላለን ። ›› በማለት አዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሀፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን  መስከረም 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You