አዲስ አበባ፡- ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር በትብብር ይሰራል፡፡›› ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አስታወቁ፡፡
የዘንድሮው ዓመት የሀጂ እና ኡምራ ጉዞ በረራ በመጪው ዓርብ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በመተባባር የዘንድሮውን የሀጂ እና ኡምራ ጉዞ በተመለከተ በትናንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ላይ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደተናገሩት፤ አየር መንገዱ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ምዕመን ጋር ከምን ጊዜውም በላይ እንደ አንድ ቡድን ሆኖ በመስራት የዘንድሮውን የሀጂ እና ኡምራ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለረጅም ጊዜያት ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነት አለው፡፡›› ያሉት አቶ ተወልደ፤ የ2011 ዓ.ም ሀጂ ጉዞን ስኬታማ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ተወልደ ማብራሪያ፤ ከእስልምና ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በርከት ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቅዱስ ቦታዎች አላት፤ አየር መንገዱም ጥንታዊ በሆኑት እንደ አልነጃሺ እና ሀረር የመሳሰሉት ስፍራዎች ለማስጎብኘት እንዲሁም ለምክር ቤቱ ተጨማሪ ገቢን ማስገኘት እና ለሀገሪቱ እውቅና መስጠት የሚችሉ የማስፋፋት ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
አየር መንገዱ ከ30 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉ የመስተንግዶ አባላትን ማዘጋጀቱን የገለፁት ዋና ሥራ ስፈፃሚው፣ ከጅዳ እስከ መካና መዲና ለምዕመናኑ በቂ መረጃ በመስጠት እንዲሁም በቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በርከት ያለ የፀሎት ቦታዎችን ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ የሀጂ ጉዞ ሀገሪቱና የእስላማዊ ምክር ቤት በለውጥ ጎዳና ላይ ባሉበት ወቅት መሆኑ ደስተኛ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ መንፈሳዊ ጉዞውም የተቃናና ከችግሮች የፀዳ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት አባል ዶክተር አንዋር ሙስጠፋ በበኩላቸው፤ የሐጂ ኮሚቴ መዋቀሩን በመግለፅ ኮሚቴው ሀገር ውስጥና በሳዑዲ ዓረቢያ በመናበብ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የተወሰኑ የቡድን አባላት ሳዑዲ ዓረቢያ መላካቸውንም ተናግረዋል፡፡
‹‹ከዚህ በፊት ካለመናበብና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ይፈጠር የነበረውን ችግር ተደጋጋሚ ስብሰባዎችን በማድረግና ችግሮችን ነቅሰን በማውጣት ለመፍትሄ ሰርተናል፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2011
ዳግማዊት ግርማ