አዲስ አበባ፡– በልደታ ክፍለ ከተማ ኮካ ኮላ ፋብሪካ አጠገብ ለአራት ዓመታት ግንባታው ሲከናወን የቆየውና 200 ሚሊዮን ብር የፈጀው አሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
በጤና አገልግሎት ዙሪያ ለሚሳተፉ የግል ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሆስፒታሉ ከትናንት በስቲያ በተመረቀበት ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን የግሉ ባለሃብት በከተሞች አካባቢ እየተከናወኑ ባሉ የጤና አገልግሎት ዘርፎች በመሳተፍ ከመንግሥት እኩል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሁለተኛና ከፍተኛ ደረጃ የጤና አገልግሎት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ህንፃው ተገንብቶና መሳሪያው ተሟልቶ አግልግሎቱን በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል አዳጋች እንደሆነ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ አገልግሎቱ እንዲሰፋ የግል ባለሀብቱን መንግሥት እንደሚደግፍና እንደሚያበረታታ አመልክተዋል፡፡
‹‹በአግልግሎቱ መሳተፍ የሚፈልጉ የግል ባለሃብቶችን በተለያዩ መንገዶች ጤና ሚኒስቴር ይደግፋል፡፡›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም የመንግሥት ቢሮክራሲዎችን በማሳጠር፣ ብድር እንዲያገኙ በማስቻልና ከመሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከከተሞች ከንቲባዎች ጋር በመነጋገር ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ከውጪ ባለሃብቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚፈልጉ የግል ባለሃብቶች በሽርክና የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲመቻችና ከመንግሥት ጋር አጋርነት በመፍጠር እንዲሰሩ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ሚኒስትሩ አክለው ጠቁመዋል፡፡
የአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር መሃመድ ሽኩር እንደገለፁት፤ ሆስፒታሉ ላለፉት ሰባት ዓመታት በኪራይ ቤት ሲሰጥ የነበረውን የህክምና አግልግሎት በተቀላጠፈና በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል በመፈለጉ ዘመናዊ አጠቃላይ ሆስፒታል በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ 80 የመኝታ አልጋ የያዘው ሆስፒታሉ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በህክምናው ዘርፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችንም ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ ነው፡፡ ይህም በዋነኛነት ለዜጎች የተሻለ የህክምና አገልግሎት መስጠት ያስችላል፡፡
ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ሲደራጅም ለህክምና ወደ ውጪ ሀገር በመጓዝ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን መንገላታትና ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የጎረቤት ሀገራት ታካሚዎች ወደሀገሪቱ በመምጣት ሊታከሙበት በሚችል መልኩ መደራጀቱን አመልክተዋል፡፡
ሆስፒታሉ ለ200 ዜጎች የሥራ አድል ፈጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2011
አስናቀ ፀጋዬ