ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው የሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ያለ ሕዝበ ውሳኔ ምላሽ ዘገየ በሚል በራስ ጊዜ ክልል መመስረትና መስርተናል ብሎ ማወጅ እንደማይቻል የሕግ ምሑራን ይገልጻሉ። በዚህ መልኩ ለመሄድ ማሰብም የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ለጠያቂውም ሆነ ለአገር የማይጠቅም፤ ይልቁንም ጉዳቱ ያመዘነ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
አቶ ውብሸት ሙላት፣ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች በማናቸውም ጊዜ ክልል የመመሥረት መብታቸው ዋስትና አግኝቷል። በአንቀጽ 47/2 «በማናቸውም ጊዜ» የሚለው ቃልም የመብቱን ገደብ የለሽነት ያሳያል። በአንቀጽ 46(2) መሠረት ደግሞ ለክልል ምስረታ የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ከግምት መግባት እንዳለባቸው ያሳያል።
አሁን የሚነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ደግሞ በሕዝብ የሚነሱ እንደመሆኑ ከፈቃደኝነት ጋር የሚያያዙ ናቸው። ጥያቄው የሚቀርበውም ጥያቄውን ላነሳው ሕዝብ ምክር ቤት ነው። ለምሳሌ፣ የሲዳማ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ የሚያቀርበው ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት ነው። ጥያቄውም በምክር ቤት የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ድጋፍ ካገኘ፤ በአዋጅ ቁጥር 251/1993 መሠረት የብሔሩ ምክር ቤት በጽሑፍ ወደክልል ምክር ቤት ጥያቄውን ያቀርባል።
የሕግና ሰብዓዊ መብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙልዬ ወለላ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የክልል ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3/ሀ- ሠ የተዘረዘሩ ነገሮችን ሲሟሉ፤ የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት ሲጠይቅ ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ነው ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን አካሄዶ በአብላጫ ድምጽ ተቀባይነት ሲያገኝና ክልሉ ሥልጣኑን ሲያስረክብ ክልልነቱ የሚረጋገጠው።
ዋናው ጉዳይም ይሄ እንዴት ይፈጸማል የሚለው ነው። የሕዝበ ውሳኔ ምርጫውን እንዲያካሂድ ለምርጫ ቦርድ በሕግ ከመሰጠቱ ጋር ተያይዞም፣ ምርጫው በቦርዱ ይሄን እንዲመራ መደረጉ ተቋሙ ለዚህ ተግባር በተገቢው እውቀት፣ ልምድና ቁሳቁስ የተደራጀ ከመሆኑ ባለፈ በገለልተኛ አካል እንዲከናወንና ከተጽዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲጓዝ የሚያደርገው ይሆናል።
አቶ ውብሸትም ይሄንኑ ያጠናክራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ድምጸ-ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት። ይሁን እንጂ፣ በአዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት የምርጫ ቦርድ ከሚያስፈጽማቸው አምስት ምርጫዎች አንዱ የሆነውና የሕዝብን ፍላጎት ለመለካት ተግባር ላይ የሚውለው ሕዝበ ውሳኔን የሚያዘጋጀው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ሳይደረግ ቢቀር ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱ በዝምታ አልፎታል።
ሆኖም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ የክልሉ ምክር ቤት ካላዘጋጀ፣ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ መጠየቅን እንደመፍትሔ መውሰድ ይቻላል። ከዚህ ውጪ ግን በተናጠል ወይም ጥያቄውን ያቀረበው ብሔር፣ ሕዝበ ውሳኔው ሳይከናወን ክልል መመሥረትና ክልል መሥርተናል ብሎ ማወጅ የሚቻልበት አካሄድ የለም። ይሄንን አካሄድ ሕጋዊ የሚያደርግ ሥርዓትም በሕገ መንግሥቱ ላይ የለም።
ይሄን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ ሙልዬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግ፣ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ ሌሎች አካላት ጥያቄያቸውን ማቅረብ የሚችሉት፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውም ተግባራዊ የሚሆነው፤ ሰላምና ጸጥታ ብሎም ምቹ ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው። ሰላምና ጸጥታ ባልተረጋገጡበት ሁኔታ ደግሞ ነፃ፣ ገለልተኛና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም።
ሕዝበ ውሳኔ ውጤታማ የሚሆነውም ሰላምና መረጋጋት ኖሮ የምርጫ ኮሮጆ በነፃና ገለልተኝነት ተጠብቆ፤ ሕዝቡ መብቱ ተከብሮና ምርጫ ጣቢያ ላይ ተገኝቶ መምረጥ ሲችል ነው። ለዚህ ደግሞ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ተሟልተው ሊገኙ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ፣ ከምርጫ በፊት የምርጫ ጣቢያዎችን መለየት፤ ሕዝቡ ቅስቀሳ ተደርጎለትና ትምህርትም ተሰጥቶ ማን፣ መቼና እንዴት መምረጥ እንዳለበት ማስገንዘብ፤ ለምርጫውም ምን ምን ሁኔታዎችን መማሟላት እንደሚገባ ማሳወቅን የመሳሰሉ ተግባራት መከናወን አለባቸው።
በምርጫ ወቅትም ታዛቢዎች በሰዓቱ በቦታው ተገኝተውና መራጮችም በሰላም ወጥተው ምርጫው በታቀደለት መልኩ እንዲከናወን የሚያስችል ድባብ መፈጠር አለበት። ከምርጫ በኋላም የድምጽ ቆጠራና ውጤት በትክክል ለሕዝብ የሚገለጽበት አግባብ በተጠናከረ መልኩ ሊከናወን ይገባል።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን አንድም ጊዜ ሲኖር፤ ሁለትም ሰላም ሲሰፍን፤ ሦስተኛም፣ ይሄን የሚያስፈጽም ጠንካራ ተቋም ሲፈጠር ነው። እነዚህ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ውጤታማ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ አስቸጋሪና ሊታሰብ የማይችል ነው።
አቶ ሙልዬ እንደሚሉት፤ በዚህ ሂደት ደግሞ የጥያቄ ምላሽ ሊራዘም ወይም ሊያጥር ይችላል። ሆኖም ጥያቄው ሊራዘም የቻለው በምን ምክንያት ነው (ሆን ተብሎ ላለመመለስ ነው ወይስ በአገር ላይ ባለ ተጨባጭ ችግር ምክንያት ነው) የሚለውን በልኩ መመዘን ይገባል። ባለው ሁኔታ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ገና በአዲስ አመራሮች እየተደራጀና ሕጎቹም እየተሻሻሉ፤ ተቋማዊ አደረጃጀቱም በግልጽ ያልታወቀ፤ ሠራተኞቹንም በደንብ ያላደራጀ ነው።
ከዚህ ባለፈ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታም ተጨባጭ ችግር አለ። ከሰላምና አለመረጋጋቱ በመፈናቀሎች የታጀበበት፤ ከግለሰብ እስከ አመራሮች ሲገደሉ የታየበት ነው። እናም በምክንያታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ መቅደም ያለበት «እነዚህን ማረጋጋትና ወደ ሥርዓት ማምጣት እንዲቀድም መስራት ወይስ ሕዝበ ውሳኔ ካላደረጋችሁ ብሎ ሌላ ችግር መፍጠር ነው» የሚለውን መመለስ ይገባል።
ሕገ መንግሥቱ ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል አለ እንጂ፤ አንድ ዓመት ካለፈ በራሱ ጊዜ ክልል ይሆናል የሚል አላስቀመጠም፤ እንደዚያ የሚልም የለም። በመሆኑም አንድ አካል በሚያነሳው የክልል ልሁን ጥያቄ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላትና እነዛን ተከትሎም መሄድ ይጠበቅበታል።
በራስ ጊዜ ተነስቶ እንዲህ ካላደረጋችሁኝ እንዲህ እሆናለሁ ወይም አደርጋለሁ የሚባልበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ስለሌለም፤ ጥያቄው በሕጉ መሠረት እንዲሄድ ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው።
አቶ ውብሸት እንደሚሉት፤ በሽግግሩ ወቅት አሥራ አራት ክልሎች ነበሩ። ከሽግግሩ በኋላ ግን ዘጠኝ ክልሎችና አንድ የከተማ መስተዳድር ሆነ። ኋላም አንድ የከተማ መስተዳድር ተጨመረ። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ብሔሮች ክልል ለመመሥረት ፈልገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የነበረው የሲዳማ የክልል ጥያቄ ግን ገፍቶ ዛሬ ላይ ገሃድ ወጥቷል።
አቶ ሙልዬ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በዚህ መልኩ ይህ ካልሆነ እንዲህ አደርጋለሁ የሚል አስተሳሰብ ሲኖርና ወደዚሁ ተግባር ከተገባ መንግሥት ሥርዓት ለማስከበር መግባቱ የማይቀር ነው። ወደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ መግባቱ ደግሞ ለጠያቂው አካልም ሆነ ለአገር፤ በአጠቃላይ ለሕዝቡ ጠቀሜታ የለውም። ይልቁንም ጉዳቱ የከፋ ይሆናል።
በመሆኑም ወደፊት እንዲህ ዓይነት ነገሮች በየትኛውም አካባቢ መቆም አለባቸው። ሕግን ተከትሎ ለጥያቄ ምላሽ ማግኘት እንጂ እንዲህ ካላደረጋችሁኝ እንዲህ እሆናለሁ የሚል ነገር አይሰራም። በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ሕጎች አይደገፍም።
ሕዝቡ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብርለት፣ ሰላምና መረጋጋትን እንዲያሰፍንለት እየጠየቀ ባለበት፤ ምርጫ ቦርድም ዝግጅት እያደረኩ ነው በሚልበት ጊዜ ላይ፤ ከሕግ ባፈነገጠ መልኩ ከሚደረግ ተግባር ተቆጥቦ ቀድሞ ሰላሙን ማረጋጋት፤ ቦርዱንም ማጠናከርና ያለምንም ተጽዕኖ ነፃ ሆኖ ምርጫው የሚካሄድበትን ዕድል መፍጠር ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011
ወንድወሰን ሽመልስ