አዲስ አበባ:- እየተካሄደ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ወደ ጠንካራ የመተሳሰብ እና መረዳዳት ባህል እየተቀየረ መሆኑ ተነገረ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙህዲን ናስር አህመዲን ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል በቅስቀሳ፣ ጉትጎታና ግፊት ሲከናወን የነበረው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት
አሁን ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ወጣቱ ማንንም በአስተባባሪነት ሳይፈልግ እራሱ ተነጋግሮ፣ አቅዶና ተደራጅቶ ወደ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው እየገባ ይገኛል።
እንደ ኃላፊው አነጋገር የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ወጣቱ በራሱ ተነሳሽነት ከዳር እዳር መንቀሳቀሱና እስከዛሬ የነበረውን የጊዜ ሰሌዳ ማሻሻሉ ነው። እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ከሐምሌ ወር ሲጀምር የነበረው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘንድሮ ወደ ኋላ ተስቦ ከሰኔ ወር እንዲጀምር የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የሆነበት አቢይ ምክንያት የታቀዱ ሥራዎች በዝናብ ምክንያት እንዳይቋረጡ ታስቦ መሆኑን አቶ ሙህዲን ተናግረዋል።
በ2001 ዓ.ም በተደራጀ መልኩ የተጀመረው ይህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሙህዲን ለተሳታፊዎች የሚሰጠው ሥነ-ልቦናዊ እርካታ፣ ልምድ ከመለዋወጥ፣ ከመተሳሰብ፣ አብሮነትን ከማዳበርና ከማህበራዊ መስተጋብር አኳያ የሚፈጥረው ዕድል፣ እንዲሁም ለሚደረግለት ሰው የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ይገልፃሉ።
በዚህ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚዎች ናቸው የሚሉት የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በተለይ አቅመ ደካሞችና ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻች በዚህኛው ዙር ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን፤ ከዚህ ባለፈም «ድንበር ተሻጋሪ» (ከአንድ ክልል ወይም ከተማ ወደ ሌላ ሄዶ የመስራት) ተግባር መኖሩንም አስረድተዋል።
በአምስት የሥራ ዘርፎች የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዛሬ አስራ ሦስት ደርሷል የሚሉት አቶ ሙህዲን ናስር አህመዲን በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት አንዱና ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት እንቅስቃሴው በመላ አገሪቱ ሊካሄድ እንዳልቻለም አቶ ሙህዲን ናስር ጠቁመዋል። ዘንድሮ ግን በተፈጠረው የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ፣ እስከ ወረዳና ቀበሌ ባለው መዋቅር አማካኝነት አገልግሎቱ በመላ አገሪቱ እየተካሄደ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችም እንዲሳተፉ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ እየተከናወነ የሚገኘው የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰኔ 14 እና 15 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በአዳማ ከተማ በይፋ የተጀመረ ሲሆን በአደረጃጀትና ከአደረጃጀት ውጪ፤ በአጠቃላይ 12.7 ሚሊዮን ወጣቶች እየተሳተፉበት እንደሚገኙ፤ የመዝጊያ ሥነ- ሥርዓቱም መስከረም መግቢያ ላይ እንደሚዘጋጅና የተከናወኑ ሥራዎች ሪፖርት እንደሚደመጥ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011
ግርማ መንግሥቴ