አዲስ አበባ:- ወቅቱ ክረምት መሆኑን ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ከመከላከል አኳያ ኅብረተሰቡ ከተማዋን ለጎርፍ ከሚዳርጉ ተግባራት እንዲቆጠብ ተጠየቀ።
የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራርኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ተቆፋፍረው ክፍት የተተዉ ጉድጓዶች፣ የውሃ መውረጃ ቦዮች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ወንዞች ላይ ተረፈ ምርቶችንና ቆሻሻዎችን መጣል ለጎርፍ አደጋ መከሰትና መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚያደርግ ኅብረተሰቡ ከዚህ ድርጊት በመቆጠብና አካባቢን በማፅዳት አደጋን ለመከላከል፤ ከተከሰተም ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ የበኩሉን ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል።
በአሁኑ ሰዓት በአስሩም ክፍለ ከተሞች ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች በጥናት ተለይተው ታውቀዋል ያሉት አቶ ሰለሞን መስሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ ለመከላከል አስፈላጊው ጥረት ሁሉ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።
የከተማዋ መልካምድራዊ አቀማመጥ፣ የመንገዶች አገነባብ፣ በርካታ ነዋሪዎች በወንዝ ዳር መኖራቸው፣ በከባድ ዝናብ ወንዞች መሙላት፣ የጎርፍ መከላከያ ግንብ አለመኖር፣ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች፣ በፕላን አለመመራት እና የመሳሰሉት ለአደጋ ክስተት ምክንያት ናቸው የሚሉት አቶ ሰለሞን በዚህ የክረምት ወቅት በከተማዋ በአጠቃላይ 20ሺህ 955 አባወራዎች፣ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና 990 ተቋማት ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማሳሰቢያ የክረምት ወቅት ቅዝቃዜን ለመከላከልና ምግብ ለማብሰል ከሰልን በቤት ውስጥ በምንጠቀምበት ጊዜ በርና መስኮት በመክፈት በቂ የአየር ምልልስ እንዲኖር በማድረግ፣ በመጨረሻም ከሰሉን በውሃ በማጥፋት ሊደርስ የሚችልን ሰብአዊ አደጋም ሆነ የንብረት መውደምን ልንከላከል ይገባል።
በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሳይታሰብ የሚከሰትና የኅብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስተጓጉል፣ በሰው፣ በንብረትና አካባቢ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት፣ እልቂትና ተፅእኖ ሊያስከትሉ የሚችሉ አደጋዎችን መከላከልና የጋራ ደህንነትን መጠበቅ የአንድ መስሪያ ቤት ኃላፊነት ብቻ አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሩ ችግሩ እንዳይከሰት ከተከሰተም የመቆጣጠርና ሊደርስ የሚችለውን አደጋ የመቀነስ ተግባር ከግለሰብ ጀምሮ የሁሉም የከተማዋ ነዋሪና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሆኑንም ተናግረዋል።
ከቀላል እስከ ከባድ አደጋዎች እየደረሰባት ያለችው አዲስ አበባ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የወደፊት የእድገት አቅጣጫዋ ላይ ሁሉ አደጋ እየደቀኑ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ሰለሞን ከምን ጊዜውም በላይ እያንዳንዱ ነዋሪና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011
ግርማ መንግሥቴ