አዲስ አበባ፡-
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳርና አዲስ አበባ የመንግሥትና የጦር አመራሮች ላይ በተፈጸመው ግድያ ተሳታፊ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ተጨማሪ ሰዎችና ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረኃይል ገለጸ። መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ኅብረተሰቡም ይሄንኑ አውቆ ከተለያዩ አደናጋሪ መልዕክቶች ራሱን እንዲጠበቅ አሳስቧል።
ግብረኃይሉ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በተደረገው የምርመራ ሂደትም ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በባህርዳር ከተማ 223 በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ከተጠርጣሪዎቹ 59 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ ሌሎች የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ወንጀል ፈጻሚዎቹ የጠነሰሱትን ሴራ የሚመሩባቸው የተለያዩ የሥልጠና ማንዋሎችና የደህንነት አደረጃጀት መዋቅሮችም ተይዘዋል።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ 60 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራና የማጣራት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ግብረኃይሉ አስታውቋል። ግብረኃይሉ ባደረገው ብርቱ ክትትልም ለሽብር እና ለተደራጀ ዝርፊያ ሊውሉ የተዘጋጁ ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪያዎችና መሰል ጥይቶች እንዲሁም ለፈንጂ ማቀጣጠያ የሚያገለግሉ ቁሶች እና 84 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። በተያያዘም 10 ተጠርጣሪዎች የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ ሲያዘዋውሩና ለወንጀል ድርጊት ሊጠቀሙ ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ክትትልና ፍተሻ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አስታውቋል።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ 60 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራና የማጣራት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ግብረኃይሉ አስታውቋል። ግብረኃይሉ ባደረገው ብርቱ ክትትልም ለሽብር እና ለተደራጀ ዝርፊያ ሊውሉ የተዘጋጁ ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪያዎችና መሰል ጥይቶች እንዲሁም ለፈንጂ ማቀጣጠያ የሚያገለግሉ ቁሶች እና 84 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። በተያያዘም 10 ተጠርጣሪዎች የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ ሲያዘዋውሩና ለወንጀል ድርጊት ሊጠቀሙ ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ክትትልና ፍተሻ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አስታውቋል።
ከፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረኃይል የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ እንዲሁም በአዲስ አበባ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ በተፈጸመ አሰቃቂ ወንጀል ከፍተኛ የክልል የሥራ ኃላፊዎች እና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ሕይወት እንዳለፈ፤ እንዲሁም ሌሎች የጸጥታ አባላት እንደሞቱና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ከፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረኃይል በተሰጠ መግለጫ ማሳወቃችን ይታወሳል።
በወቅቱ የተጠነሰሰው ሴራ በአማራ ክልል ሕዝብ እንዲሁም በክልሉና በፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት የከሸፈ ሲሆን፤ ወንጀል ፈጻሚዎቹንም ለሕግ ለማቅረብ ለተፈጸመው ወንጀል የምርመራ ቡድን በማቋቋም የተጠናከረ የክትትልና የምርመራ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ግብረኃይሉ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በአማራ ክልል 212፣ በአዲስ አበባ ከተማ 43 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በቀጣይም የደረሰበትን ውጤት ለኅብረተሰቡ በተከታታይ እንደሚያሳውቅ መግለጹ ይታወሳል። በዚህ መሠረት ከባህርዳር ከተማ እስከ አዲስ አበባ በተዘረጋው ትስስር የተፈጸመውን ውስብስብ የወንጀል ሂደት በተመለከተ በክትትልና በማጣራት ያገኛቸውን ውጤቶች ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።
እስካሁን በተደረገው የምርመራ ሂደትም ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በባህርዳር ከተማ 223 በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከልም የክልሉ የልዩ ኃይል ፖሊስ አመራርና አባላት፣ የክልሉ የፀጥታ መዋቅርን የሚመሩ ከፍተኛ ኃላፊዎችና አባላት እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች መካተታቸው በተካሄደው ምርመራ ታውቋል።
ከዚህ በፊት ከተገለጸው በተጨማሪ ግብረኃይሉ ባደረገው ክትትልና ምርመራ ከተጠርጣሪዎቹ 59 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ ሌሎች የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም በርካታ ጥይቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ወንጀል ፈጻሚዎቹ የጠነሰሱትን ሴራ የሚመሩባቸው የተለያዩ የሥልጠና ማንዋሎችና የደህንነት አደረጃጀት መዋቅሮችም ተይዘዋል።
በተደረገው ምርመራና የማጣራት ሂደት በመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳትፈዋል ተብለው የተያዙት ተጠርጣሪዎች ድርጊቱን ካቀነባበረውና ሲመራው ከነበረው ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንደነበራቸው በምርመራ ሂደት ተረጋግጧል።
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ቀድሞም ቢሆን በሕገ ወጥ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና እራሱን ለመደበቅ በማሰብ የራሱ መኖሪያ ቤት እያለው፤ በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የቤት ቁጥር 288 በሆነው በአቶ ወዳጆ ማሞ ባለቤትነት ተመዝግቦ በሚታወቀው መኖሪያ ቤት 17ኛው የቤቱ ነዋሪ በመምሰል የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ በማውጣት የተለያዩ ወንጀል ፈጻሚ ቡድኖችን ሲያደራጅ እንደነበረ በምርመራ ለማረጋገጥ ተችሏል።
በተያያዘ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ የሚገኘው የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ የግል መኖሪያ ቤታቸው ሲበረበር አንድ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ አንድ ራቫ ፎር ተሽከርካሪ፣ የተለያዩ ሰነዶች እንዲሁም በቀጣይ የሚጣራ ሆኖ የከበሩ ማዕድናት የተቀመጡበት የባንክ ደብተር በማስረጃነት ተይዟል።
በተጨማሪም ሃምሳ አለቃ ፈቃዱ ሃብታሙ የተባለ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አሰልጣኝና የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው የቅርብ ሰው ከጀነራሉ ባለቤት ከወይዘሮ ደስታ አሰፋ ግርማይ ጋር በተጠቀሰው መኖሪያ ቤት ተሸሽጎ መያዙንና ሁሉቱም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጣራ እንደሚገኝ ግብረኃይሉ ያስታውቃል።
በዚሁ በቡራዩ ከተማ በለኩ ከታ ቀበሌ በብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ስም የተመዘገበ ሌላ መኖሪያ ቤትና በአዲስ አበባም በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ሃያት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በስሙ ተመዝግቦ በተገኘው ባለ 3 መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም ውስጥ የተለያዩ ሰነዶችና ክላሽንኮቭ መሣሪያ ተገኝቷል። በተጨማሪም በሰበታ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አንድ ማካሮቭ ሽጉጥ ከበርካታ ጥይቶችና በአዲስ አበባ ከተማ የፈጠረውን የአደረጃጀት ትስስር በአስረጂነት ከሚጠቅሱ ሰነዶች ጋር በግብረኃይሉ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በጀነራል አሳምነው ጽጌና በቁጥጥር ስር በዋሉ ሌሎች አመራሮች ተሞክሮ ለከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት የደህንነትና የውትድርና ሥልጠና የወሰዱ ግለሰቦች መኖራቸውም ታውቋል። እነዚህ ሥልጠና የወሰዱ ግለሰቦች በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ግድያና የተደራጀ ዘረፋ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ብሎም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ለማጋጨት ተልዕኮ እንደተቀበሉ ለማወቅ ተችሏል።
በተለይ በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎችና በአዲስ አበባ ከተማ ረብሻና ሁከት በመፍጠር ሕዝቡን ለማሸበር እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ መረጃ በመሰብሰብ የግድያ ወንጀል ለመፈጸም መሰማራታቸውም በምርመራ ተረጋግጧል። በሌላ በኩል ተጠርጣሪዎቹ ለወንጀል ድርጊታቸው ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብና ቁሳቁስ የማሰባሰብ ሥራ ላይ እንደተሰማሩ ግብረኃይሉ ባደረገው የማጣራት ሂደት አረጋግጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያ ጋርና ከባህርዳሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ 60 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የምርመራና የማጣራት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም ግብረኃይሉ ባደረገው ብርቱ ክትትል ለሽብር እና ለተደራጀ ዝርፊያ ሊውሉ የተዘጋጁ ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪያዎችና መሰል ጥይቶች እንዲሁም ለፈንጂ ማቀጣጠያ የሚያገለግሉ ቁሶች እና 84 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሏል። በተያያዘም 10 ተጠርጣሪዎች የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ ሲያዘዋውሩና ለወንጀል ድርጊት ሊጠቀሙ ሲንቀሳቀሱ በተደረገ ክትትልና ፍተሻ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረኃይሉ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እያሳወቀ፤ የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ በፍጹም ለድርድር እንደማይቀርብ ያስገነዝባል።
ኅብረተሰቡም በተለይም ደግሞ የአማራ ክልል ሕዝብና የፀጥታ ኃይሉ ሰላሙን በማስጠበቅ እንዲሁም ተጠርጣሪዎችን ለሕግ በማቅረብ ላበረከተው ከፍተኛ ሚና ግብረኃይሉ ምስጋና እያቀረበ፤ ማንኛውም ስጋት ተወግዶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲቀጥል በሚከናወነው ተግባር አሁንም ኅብረተሰቡ እንደወትሮው የተለመደ ትብብሩን እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ የጋራ ግብረኃይሉ ማሳሰብ ይወዳል።
መንግሥት በቀጣይነትም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ የተሟላ ቁመና እንዳለው እየገለጸ፣ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም የሽብር እንቅስቃሴ ለአፍታም ቢሆን እንደማይታገስ ግብረኃይሉ በድጋሚ ያረጋግጣል።
ኅብረተሰቡም ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ሆን ተብለው ከሚሰራጩ የሃሰት መረጃዎችና አሉባልታዎች እንዲጠነቀቅ ግብረኃይሉ እየገለጸ፤ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ ከተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶቹ ጋር በተያያዘ ተከታታይ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ይፋ እንደሚያደርግ ያሳውቃል።
የሀገር መከላከያ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ የሰጡት መግለጫ
አዲስ አበባ
ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011
ወንድወሰን ሽመልስ