• 151 ነጋዴዎች ደግሞ በተለያየ ምክንያት ውል አልፈረሙም፤
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ ቤቶች ላይ ያደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ ከ95 በመቶ በላይ ተከራይ ነጋዴዎች ውል ገብተው ክፍያ መጀመራቸው፤ 151 ነጋዴዎች ግን በተለያየ ምክንያት ውል አለመፈረማቸው ተገለጸ፡፡ የማሻሻያ እርምጃውም ኮርፖሬሽኑ የተሰጠውን ቤት የመገንባት ተግባር ዕውን ለማድረግ የፋይናንስ አቅም በመፍጠር እንዳገዘውም ተጠቁሟል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክብሮም ገብረመድህን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የዋጋ ማሻሻያውን ተከትሎ ከተከራይ ነጋዴዎች ጋር ያለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ሰፊ ውይይት ተደርጎ ግንዛቤ ማስያዝ በመቻሉ አሁን ላይ ከ95 በመቶ በላይ ተከራዮች ውል ፈርመው የመጀመሪያ ክፍያ ፈጽመዋል፡፡
151 ነጋዴዎች ደግሞ በተለያየ ምክንያት ውል ያልፈጸሙ ሲሆን፤ ተከራይ የመንግሥት ተቋማትም በወቅቱ ለዚያ የሚሆን በጀት ስላልተያዘላቸው በቀጣይ በጀት ዓመት ለመክፈል የሚያስችላቸውን የመተማመኛ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ ኮርፖሬሽኑ ያደረገውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ ተከራዮች በተቀመጠው ደንብ መሠረት ውል እንዲፈጽሙና ክፍያም እንዲያከናውኑ መልዕክት ተላልፏል፡ ፡ በሂደቱ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታትም ኮርፖሬሽኑ ተገቢነት ባላቸው ጥያቄዎች ላይ ማስተካከያና ማሻሻያ አድርጓል፡፡
ከእነዚህ መካከል የክፍያ ሂደት ማሻሻያ ተጠቃሽ ሲሆን፤ የማሻሻያ እርምጃዎችን የማይቀበሉ ነጋዴዎች ቢኖሩ ግን ኮርፖሬሽኑ በሕጉ መሠረት ቤቱን ተረክቦ ለጨረታ እንደሚያቀርብም ገልጾ ነበር፡፡
በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም ከ95 በመቶ በላይ ተከራዮች ውል ፈርመው ክፍያ የጀመሩ ሲሆን፤ በዙር የሚፈጸሙ ቀሪ ክፍያዎችም በተቀመጠው አሠራርና በተገባው ውል መሠረት የሚፈጸሙ ይሆናል፡፡ በቀጣይ ክፍያዎች ላይ ያለመቀበልና የእንቢተኝነት አዝማሚያዎች የሚስተዋሉ ከሆነ ውልና የአሠራር ሕጉን ተከትሎ ኮርፖሬሽኑ እርምጃ የሚወስድ ይሆናል፡፡
አቶ ክብሮም እንዳሉት፤ ውል ፈርመው ክፍያ የጀመሩ ነጋዴዎች የመኖራቸውን ያክል በዚህ ሥርዓት ውስጥ መግባት ከነበረባቸው ነጋዴዎች ውስጥ 151 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ውል አልፈጸሙም፤ ክፍያም አልጀመሩም፡፡
ከእነዚህ መካከል በአገር ውስጥ የሌሉ፣ ቅሬታ አቅርበው ይፈታልናል በማለት የሚጠባበቁ፣ እንዲሁም ከሕግ አሠራር ጋር በተያያዘ ምክንያት ውል ያልፈጸሙ የሚገኙበት ሲኖሩ፤ ጥቂቶች ደግሞ በእንቢተኝነት የዘለቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጋር በተያያዘ ያለው ሂደትም በተቀመጠው የሕግ አሠራር መሠረት መፍትሄ የሚሰጠው ሲሆን፤ ይሄው ለየቅርንጫፎች ተላልፏል፡፡
እንደ አቶ ክብሮም ገለጻ፤ በዚህ መልኩ የዋጋ ማሻሻያ መደረጉ የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ አቅም የሚያሳድግ ሲሆን፤ ይሄም ኮርፖሬሽኑ የተሰጠውን ቤት የመገንባት አዲስ ኃላፊነት እውን የማድረግ ጉዞውን አግዞታል፡፡
በዚህ የገቢ አቅም በመነሳትም ለሌሎች ነጋዴዎች የንግድ ቤትም ሆነ ለመንግሥት ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ እስከ አስር ፎቅ ያላቸው ሕንፃዎችን ወደመገንባት ገብቷል፡፡
አሁን ላይም በአራት ሳይቶች የአራት ሕንፃዎችን ግንባታ የጀመረ ሲሆን፤ እነዚህ ሕንፃዎችም እስከ አራተኛ ፎቅ ለንግድ፤ ከዚያ በላይ ያሉት ደግሞ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011
ወንድወሰን ሽመልስ