አዲስ አበባ፡- የተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ረቂቅ ፖሊሲ አገራዊ ለውጡን፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም በውጭ ያሉ ዜጎችን መብትና ደህንነታቸው ማስጠበቅን፣ የባህር ኃይልን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ ረቂቅ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መነሻው አሁንም የአገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። በውጭ ያሉ ዜጎችን መብት፣ ደህንነታቸውንና ጥቅማ ቸውን ማስጠበቅ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑ በትና የሚሳተፉበትን አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የተሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዋና ትኩረቱ ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ክልላዊ ትስስር መሆኑን አመልክተው በቅርብ ጊዜ የዓለም አጀንዳ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥንም የሚያካትት ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከ100ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እያላት ወደብ አልባ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት ያሉ አምባሳደሩ የተሻሻለው ፖሊሲም ከጎረቤት አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት መሠረት አድርጎ የባህር ኃይልን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የእያንዳንዱን አገር ግንኙነት በተመለከተም ራሱን የቻለ ሌላ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲሻሻል ከተደረጉባቸው ምክንያቶች መካከል አላስፈላጊ ዝርዝር ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑ፣ አገሪቱ በቀጣናው፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ሚና እየተቀየረ መምጣቱና በውስጡ መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች ባለማካተቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ክለሳ ቡድን አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ካሳሁን እንደገለጹት፣ በአገራችን፣ በአካባቢያችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ያለውን ፖሊሲ ይዞ መቀጠል አዋጭ አይደለም ብለዋል፡፡
በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ደቡብ ሱዳን ስላልነበረች ስለ ደቡብ ሱዳን የሚለው ነገር የለም፡፡ፖሊሲው በኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበረው ነገር በጣም አሉታዊ ነበር፣በሥልጣን ያለው መንግሥት ከሥልጣን እስካልተወገደ ድረስ ትብብሩ ችግር ይገጥመዋል ብሎ የደመደመ ነበር፡፡ በአንጻሩ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ የሚባል የመቀራረብ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡አዲሱ ፖሊሲ እነዚህን ሁሉ ወቅታዊ ሁኔታን ከግምት አስገብቶ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ለዳያስፖራው ብዙም ትኩረት የሰጠ አልነበረም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አዲስ የተሻሻለው ፖሊሲ ለዳያስፖራው ትኩረት ሰጥቷል፤ ከኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በተጨማሪም ለባህል፣ ለሕዝብ ለሕዝብ፣ለታሪካዊ ግንኙነትና ሌሎች ዲፕሎማሲዎችን ጭምር አካቶ የያዘ በመሆኑ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አድማስ የሚያሰፋ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ወራትም ምሁራን ረቂቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማሻሻያውን በጥልቀት መመርመራቸውም ተገልጿል። ረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኮ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። እስካሁን ድረስ የሚመለከታቸው አካላት በተሻሻለው ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት እንዳደረጉበት ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
ጌትነት ምህረቴ