‹‹መመሪያውን የወሰነው አካል በአግባቡ መፈጸም ይኖርበታል›› -አቶ ክፍሌ ሰይፈ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስራ አስኪያጅ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያን አውጥቶ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። መመሪያው እንዲወጣ ምክንያት የሆነው የክለቦች የዝውውርና ክፍያ ስርዓቱ ግልፅ ያልሆነና ብዙ ማጭበርበሮች ያሉበት መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ያስታውሳሉ፡፡

የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ወደ ትግባራ ከገባ በኋላ ለማስፈጸም ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለተግባራዊነቱ እየሰራ ነው። ይሁን እንጂ ከተጫዋቾች ዝውውርና ከክፍያ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ አሁንም መመሪያው እየተከበረ እንደማይገኝ ቅሬታዎች ይሰማሉ። ተጫዋቾች በዝውውር መስኮቱ አንዱ ክለብ ያቀረበላቸውን የተሻለ ክፍያ በመተው ትንሽ ክፍያ ላቀረበ ክለብ ሲፈርሙ መታየታቸው ደግሞ በመመሪያው ተግባራዊነት ላይ ጥርጣሬን ያሳደረ አንዱ ምክንያት ነው።

መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክፍሌ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች የክፍያ ስርዓት ግልጽ ያልሆነ ማጭበርበር የሚበዛበት በመሆኑ ከክለቦች በመጣ ጥያቄ መሰረት ጥናት ተደርጎ አዲስ መመሪያ ወደ ትግበራ መገባቱን ያስታውሳሉ። መመሪያውን የሚያስፈጽመው አካል ገለልተኛ መሆን ስለሚኖርበት ከተለያዩ ክፍሎች የተወጣጡ ሰዎችን ያቀፈ አጣሪ ኮሚቴ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ ከስነ-ምግባርና ፀረሙስና፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከደህንነት እና ከጠበቆች ማህበር ተዋቅሮ ስራ መጀመሩን ይጠቁማሉ። ኮሚቴው ደንብና መመሪያውን በማንበብ እራሱ የሚመራበትን የስነ ምግባር መመሪያንም ደንብ ማዘጋጀትም ተችሏል፡፡

ኮሚቴው የተጫዋቾች ዝውውር በክለቦች ምን እንደሚመስል ከ19ኙም ክለቦች መረጃ እንዲሰበሰብ ጠይቆ መረጃዎች ለጽህፈት ቤቱ እየደረሱ መሆናቸውንም ስራ አስኪያጅ ይናገራሉ። እየቀረቡ በሚገኙ መረጃዎች መሰረት አንድ ተጫዋች ከአንድ ክለብ ጋር የተነጋገረውን ከፍተኛ የደመወዝ ክፍያ በመቀነስ ለሌላ ክለብ በፌዴሬሽን ውል ላይ የ150 ሺ ብር ልዩነት ያላቸው ውሎችን ሲፈፅም እየታየ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ክፍሌ፣ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ውል ከፈፀሙ ክለቦች ጋር መረጃ በስልክ፣ በኢሜል፣ በአካልና በሌሎች መንገዶች ጥቆማ እንዲሰጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በቅርቡ ይፋ በሆነው የጥቆማ ስርዓት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከዚህ ጋር የተገናኙ መረጃዎችን ማቀበል ይችላል። በዚህም ጠቋሚው አካል ከፍተኛ የሆነ ገንዘብን የሚያገኝበት ይሆናል። ለጠቋሚው የሚሰጠው መጠን ከተጭበረበረው ገንዘብ ላይ 50 ፐርሰንቱ እንደሚሰጥ ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። በቦርድ ከፀደቀ በኋላ ለኅብረተሰቡ ይፋ ሆኖ በሚመጣው የጥቆማ ስርዓት መሰረት አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል። ክለቦች ውል እንዴት አዋዋሉ የሚለው አጣሪ ኮሚቴው ሂሳብ መዝገባቸውን በመመርመር እና በተለያዩ ስልቶች በማጣራት ላይ ሲሆን ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጽሞ የሚገኝ ክለብ በመመሪያና በደንቡ መሰረት ውሳኔ ይተላለፍበታል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር መመሪያውን የወሰኑ ክለቦችና አካላት በአግባቡ መፈጸም እንዳለባቸው የሚናገሩት አቶ ክፍሌ፣ ከ16ቱ ክለቦች መመሪያውን ጥሰዋል ተብለው ጥቆማ የተጠቆመባቸው ሶስት ክለቦች ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል። መመሪያውን ጥሰው የተገኙ ክለቦች ዋንጫ ቢያነሱ እንኳን በምርመራ ከተረጋገጠ ጊዜው ቢያልፍም ዋንጫውን ተቀምተው ከሊጉ እስከ መውረድ ድረስ ቅጣት ሊተላለፍባቸው ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁሉም በተስማማው መጠን ሰላማዊ የእግር ኳስ መድረክ እንዲኖር የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል። ክለቦች ሁልጊዜ ተስማምተው የሚያወጡትን ደንቦች መመርያዎች በአግባቡ መፈጸም እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

መመሪያው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወጣቶች ቦታ እንዲያገኙ ይጋብዛል የሚሉት አቶ ክፍሌ፣ አዲስ እንደመሆኑ ግን የመንገጫገጭ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ቢገልፁም አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ ይናገራሉ። ክለቦች የራሳቸው መለያ ኖራቸው አትራፊ እንዲሆኑ ብዙ ስልጠናዎች መሰጠቱን የሚያስታውሱት አቶ ክፍሌ ይህንን ለመተግበር ክለቦች የተደራጁበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ።

እንደ አቶ ክፍሌ ገለፃ፣ ክለቦች ከመንግስትና ከከተማ አስተዳደር ሙሉ ሀብት ስለሚያገኙ ሕዝባዊ እና የገበያ እቅድን መያዝ አይፈልጉም። የከተማ አስተዳደር ክለቦች ቀስበቀስ ከድጎማ ወጥተው የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩና ትርፋማ እንዲሆኑ መስራት ይኖርበታል። የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከችግር ለማላቀቅ ረጅም ጊዜ የሚያስፈልገው እና ክለቦች የ10 ዓመትና ከዛ በላይ እቅድ ይዞ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ክለቦች በዓመት ለአንድ ተጫዋች ምን ያህል እንክፈል እንጂ እንዴት ገበያ ተኮር መሆን እንዳለባቸው ግንዛቤ መያዝ አለባቸው፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You