•ምሩቃኑ ለአገራቸው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አርበኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ
•ተማሪዎችን ብቁ ማድረግ የሚቻለው ከታች ጀምሮ ሲሰራ ነው
አዲስ አበባ፡- ተመራቂዎች በተግባርና በንድፈ ሃሳብ ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ለአገራቸው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት አርበኛ ሆነው መሥራት እንደሚገባቸው ተነገረ።ተማሪዎች ከኩረጃ ነፃ በሆነ መልኩ በሁለንተናዊ መንገድ ብቁ ማድረግ የሚቻለው ከታች ጀምሮ በትምህርት ጥራት ላይ መስራት ሲቻል መሆኑን የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ ።
ወቅቱ አገርን የመጠበቅና ለሰላም ዘብ መቆምን የሚጠይቅ በመሆኑ ተመራቂዎች ከማህበራዊ ሚዲያ የጥፋት ተልዕኮ ራሳቸውን ጠብቀው ለሀገር ሰላምና ልማት መስራት እንዳለባቸው የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ማሳሰቡን ሪፖርተራችን ራስወርቅ ሙሉጌታ ዘግቧል።
ዩኒቨርሲቲው ትናንት ተማሪዎቹን ባስመ ረቀበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሀነመስቀል ጠና እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያዎች እያደረሱት ያለው ጥፋት ለሀገር አንድነትና ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ተመራቂዎች አድራሻው የማይታወቀው ማህበ ራዊ ሚዲያ እየፈጠረ ያለውን ችግር በጥልቀት በመረዳት ሁሉንም ነገር በመመርመር ለሰላም፣ ለይቅርታና ለአንድነት መሥራት አለባቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግሮች ሲፈጠሩ የዩኒቨ ርሲቲው ተማሪዎች ከአመራሩና ከመምህራን ጋር ችግሩን ለመድፈን የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚህም በኋላ ተማሪዎች በተመረቁበት ዘርፍ ወደ ሥራ ሲገቡ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን በማሰብ ከማህበረሰቡ ጋር በአብሮነት ለሰላምና ለልማት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ በበኩላቸው፤ «ተማሪዎች እንደ ከተማም ሆነ እንደ ሀገር ያሉትን የሰላምና የልማት ችግሮች ለመቅረፍ በህብረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል» ብለዋል። ይህንን ለማጠናከርም በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ይሰራል። የተጀመ ረውን እንቅስቃሴም ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደ ሚሆን ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክ ትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደመወዝ አድማሱ እንደገለጹት፤ዩኒቨርሲቲው ሥራውን ከጀ መረ ለስልሳኛ ጊዜ ሜትሮፖሊታን ከሆነ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ
በመደበኛ፤ በማታ፤ በክረምትና በርቀት እያስተማረ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 3 ሺ 282 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡
ሪፖርተራችን አጎናፍር ገዛኸኝ እንደዘገበው ጂማ ዩኒቨርሲቲ 28 ደቡብ ሱዳናውያንን ጨምሮ 2ሺ423 ተማሪዎችን በማስመረቅ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ተቀላቅሏል። በምርቃው ሥነሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ደቡብ ሱዳናውያንን አስተምሮ በማስመረቅ ዓለምአቀፍ ተቋማትን ተቀላቅሏል።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት የሶማሌያ፣ የቤኒን፣ የናይጄሪያ፣ የሞሮኮ፣ የጋና እና ደቡብ ሱዳን ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ዓለምአቀፋዊ የትምህርት ተቋምነቱን እያጠናከረ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በ270 የትምህርት ፕሮግ ራሞች፤ በመደበኛና በኢ-መደበኛ 47 ሺ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ሲሆን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዙር በአጠቃላይ 7ሺ 791 ተማሪዎችን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ባለው የትምህርት ደረጃ ማስመረቁን ገልጸዋል።
የሁለተኛ ዙር ተመራቂዎች በጤና፣ የሕግና ቴክኖ ሎጂ ትምህርት መስክ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ጀማል፤ በተግባርና በንድፈ ሃሳብ እውቀት መቅሰማቸውን አንስተው ማኅበረሰባቸውን በኃላፊነት እንደሚያገለግሉ እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው ራሱን እያሳደገ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሪፈራል ሆስፒታልን ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ዘመናዊ መሣሪያዎች ተገጥመውለታል፤ የታካሚዎች የህክምና ታሪክም በዲጂታል ቴክኖሎጂ መያዝ መጀመሩንም አንስተዋል።
ከሆስፒታሉ በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን ለማዘመን የእቅድና ሪፖርት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት በኦንላይን መቀያየርና አሠራሩም ከወረቀት ነፃ መሆኑንና ተጀምረው የነበሩ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ የተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ መደረጉን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው ብቁ አመራሮች እንዲመጡ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተመርጧል። የመማር ማስተማር ሂደቱም ሰላማዊ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መሠራቱንም ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ተመራቂዎች ተወካይ ተማሪ ሲሶ ርዛን ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምስጋናውን አቅርቦ የጅማ ማህበረሰብ በአምስት ዓመት የትምህርት ወቅት የሰጣችሁን ፍቅር ከልባችን አይወጣም ብሏል። የደቡብ ሱዳናውያን ተማሪዎች የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጥረት ውጤት ነው ያለው ተማሪው፤ እኛ መማራችን ለሁሉም ጥቅም አለው፤ ወደ አገራችን ስንመለስ የኢትዮጵያና የጂማ ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር እንሆናለን ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ለአንዲት አገር እድገትና ብልጽግና በአንድነት መንፈስ እንዲሠሩ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድርና የበዓሉ የክብር እንግዳ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ሪፖርተራችን ዳግም ከበደ ነው ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በ2011ዓ.ም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 8ሺ 612 ተማሪዎችን ባስመረቀበት ወቅት፤ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አወል አርባ እንደገለጹት፤ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ለውጥና አመለካከት በብቃት ተላብሰው ያጋጠማቸውን ችግሮች ተቋቁመው ራሳቸውን እንዲሁም አገራቸውን ለማልማት መነሳት ይኖርባቸዋል። ለዚህም በኢትዮጵያዊነትና በአንድነት መንፈስ ለአንዲት ኢትዮጵያ ብልጽግና መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
«ያለችን አገር አንዲት ኢትዮጵያ ናት» ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተመራቂዎች ታሪክ ሠሪ ትውልድ እንደሚሆኑ እንደማይጠራጠሩ ገልጸዋል። ከዚህ በተቃራኒው መቆም ወይም ከሌላ መጠበቅ ለውድቀት መመቻቸት መሆኑንም በመልዕክታቸው ላይ አንስተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወርቅ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ጊዜያዊ ችግር ሳይፈትናቸው ብርታትን ምርኩዝ በማድረግ ለዚህ የምርቃት ቀን መብቃታቸውን አስታውሰው፤ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ለማኅበረሰቡ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው አሳስበ ዋል።
ከአርሲ ዞን አጠቁ ወረዳ የመጣውና የእንስሳት እርባታና ሥርዓተ ትምህርት ክፍል የወርቅ ተሸላሚ የሆነው ብሩክ ነገደ እንደተናገረው፤ በዩኒቨርሲቲው የነበረው ቆይታ መልካም እንደነበር አስታውሶ፤ የቀሰመውን እውቀት በመጠቀም ከዘረኝነት በጸዳ መልኩ አገሩን ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል።
በተመሳሳይ ዜና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድኅረ ምረቃ ያሰለጠናቸውን 5ሺ461 ተማሪዎችን አስመርቋል። ተመራቂዎቹ ኩረጃ፣ የጥናት ጽሑፎችን ቀድቶ ማቅረብና የቡድን ሥራዎችን ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ መተው በትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ተጽእኖ በመገን ዘብ ማስቆም ይገባል ማለታቸውን የዘገበው ዘላለም ግዛው ነው።
ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው 5ሺ461 ተማሪዎች መካከል 1ሺ806 ሴቶች ናቸው። አስር ኤርትራውያን፣ ስምንት ሶማሊዎች፣ ሰባት ደቡብ ሱዳን እና የሳዑዲ አረቢያ ዜጎችም ይገኙበታል። የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገብረመስቀል ገብረጻድቅ እንደተናገሩት ከቅድመ ትምህርት ክፍል ባዮ- ቴክኖሊጂ፣ ፋርማሲና ጋዜጠኝነትን ጨምሮ በስድስት ዘርፎች ያስመረቀው ለመጀመሪያ ዙር መሆኑንም ተናግረዋል። ተመራቂ ተማሪዎች መልካም ሥነ ምግባር ተላብሰው በቁርጠኝነት አገርና ሕዝብን እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤ ለእድገትና ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመቅዳት፣ የማላመድና የማሸጋገር እንዲሁም አገር በቀል እውቀትን በመጠቀም ተመራቂ ተማሪዎች ለችግሮች መፍትሄ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያካበቱትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ለአገራቸው እድገትና የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል። ጠንክረው በመሥራት ስኬታማ እንዲሆኑና በምሳሌነት የሚጠቀስ ተግባር እንዲያበረክቱም አሳስበዋል።
በከፍተኛ ማዕረግ በሕግ ትምህርት የተመ ረቀችው ተማሪ ልዕልት እንዳለ በበኩሏ ኩረጃ፣ የምርምርና የጥናት ጽሑፎችን ቀድቶ ማቅረብና በቡድን ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች በአንድ ሰው እንዲሠራ ማድረግ ለመማር ማስተማር ሂደቱ ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቅሳለች። በመሆኑም ተጽእኖውን በመረዳት ድርጊቱም ማስቆም ይገባል ስትል ገልጻለች። በፍትህ ሥርዓቱ የሚታዩ ችግሮችንና ክፍተቶችን ለመሙላት የድርሻዋን እንደምትወጣም ተናግራለች።
በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ዘርፍ ሜዳልያ በማግኘት የተመረቀችው ተማሪ ፍቅርዓለም አስማማው በበኩሏ፤ ኩረጃ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው ስትል ጠቅሳለች። ችግሩ መፈታት ያለበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ አለመሆኑን በመግለጽ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት ስትል ጠቁማለች።
በሌላ ዜናም ብቁ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራትና ጥራት ያለው ትምህርት በአገር ደረጃ እንዲኖር ለማድረግ ከታችኛው ክፍል የጀመረ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ተመራቂ ተማሪዎች መናገራቸውን ሪፖርተራችን ሞገስ ጸጋዬ ዘግ ቧል።
በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሜዳሊያ ተሸላ ሚዋ አገሬ ማናዬ በምረቃው ወቅት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገረችው፤ ተማሪዎች በአቅማቸው መስራት ካልቻሉ የትምህርት ጥራትም ሆነ አገርን የማልማታቸው ሁኔታ ውጤታማ አይሆንም።
ምክንያቱም ከምረቃ በኋላ ያወቁት ነገር ስለሌለ ለሥራ ይቸገራሉ። በተለይ መመረቂያ ጽሑፍ ሳይቀር ከሌሎች ኮርጀው ለማለፍ ስለሚጥሩ ውጤታማነታቸው አጠያያቂ ከመሆኑም በላይ በሥራ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን አያስችላቸውም።
አማካሪ መምህራን፣ ተማሪዎችና መንግሥት ለትምህርት ጥራቱ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የምትገልጸው አገሬ፤ ጥራት ያለው ትምህርትም ሆነ አቅም ያለው ተማሪን ማግኘት እንዳይቻል የሆነው የኩረጃ ባህሉ ከታች ጀምሮ እየዳበረ መምጣቱ እንደሆነ ትናገራለች።
የሁለተኛ ዲግሪና የማዕረግ ተመራቂው ታደለ ቶሎሳ በበኩሉ፤ የመንግሥት አቅም ግንባታና ጥራት ያለው ትምህርት መስጠት ከታችኛው ክፍል የጀመረ አለመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የሚቸገረው ተማሪ እንዲበዛ አድርጓል ብሏል።
ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ መስኮች ያሰለጥናል ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታከለ መላኩ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት 30ሺ 999 ተማሪዎችን የሚያስተምር ሲሆን፤ ባለፉት ዓመታት 33ሺ 547 በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል።
በትናንትናው ዕለት በቅድመ ምረቃ፣ በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራም 4ሺ265ያስመረቀ ሲሆን፤ በድህረ ምረቃ፣ በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራም 5ሺ 28 ተማሪዎችን ለማስመረቅ በቅቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ ዲግሪ እና በዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን 6ሺ 857 ተማሪዎችን ማስመረቁ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ድልነሳው ምንውዬለት ዘግቧል፡፡ ከም ሩቋኑ መካከል 35 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ እንዳሉት በሥርዓተ ጾታ ላይ በተሰራው ጠንካራ ሥራ የሴቶችን ቁጥር ማሳደግ ተችሏል።
ዩኒቨርሲቲው በበጀት ዓመቱ 60 የምርምር ውጤቶችን በታወቁ ጆርናሎች ማሳተሙን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
በጋዜጣው ሪፖርተሮች