በግድቡ ግንባታ የታየው አንድነት በባሕር በር ጥያቄአችንም ሊደገም ይገባል!

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ‹‹ቀይ ባሕር እና አባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ፣ ለኢትዮጵያ እድገትና ጥፋት መሰረት ናቸው›› ብለው ነበር። እርግጥ ነው በዘመነው የዓለማችን መልከአ ፖለቲካ ውሀ ከመጠጥነት የተሻገረ የሉአላዊነት ዘብ፣ የሀገር እድገትም መሰረት ነው።

ኢትዮጵያም በውሀ መስመሮች ላይ ጥቅሙን ባሰላው የዘመናችን መልከአ ፖለቲካ ለመጠቀም ከዓመታት በፊት በጉባ ትልቅ ሕልም ሰንቃ፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሰረት ጥላለች ። የጨለመ ሕይወት፣ የደበዘዘ ቤት፣ ኑሯቸው ፈተና የሆነባቸው ሚሊዮን ልቦች እንደ አንድ የሆኑባት ወርቃማ እለት፤ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም። በዚች እለት በጉባ ሰማይ ስር የተቋጠረ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የነፍስ ሕልውና የሆነ የሀገር ትርክትን ቀያሪ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ምድር እውን ሊሆን ተስፋ ተቋጥሮ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጅማሮ እውን ሆነ።

የጅማሮው መጀመሪያ የፕሮጀክቱ የሲቪል ግንባታ ስምምነት ፊርማ ነበር። የወቅቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና የጣሊያኑ ሳሊኒ ደግሞ ተዋዋዮቹ አካላት ናቸው። ሁለተኛና ሶስተኛ ስምምነቶችም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን እና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቡድን መካከል ጥቅምት እና ህዳር 2004 ዓም ተፈረሙ። ከዚህ በኋላ ሳሊኒ ግንባታውን፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን ሊከውን በጉባ ተራሮች ስር ከተሙ።

ወንዝን ተንተርሰው የጨለመባቸው፣ ውሃን ተመርኩዘው ውሀን የተጠሙ ኢትዮጵያውያንም ለዚህ ፕሮጀክት ስኬት በአንድ አበሩ፤ በሕብረትም ተሰለፉ። ኢትዮጵያውያን ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት ሲጀምሩ መነሻቸው ቁጭት፣ መድረሻቸው ጭለማን በብርሀን መተካት ነበር። ለዚህም 13 የትጋት ዓመታት ከ4 ሺህ 748 በላይ የተስፋና የግንባታ ቀናትን ቆጥረዋል። አስደማሚ የግንባታ ፍጥነት የአባይን የውሀ ፍሰት ቅየራ፣ ተደጋጋሚ የውሀ ሙሌት፣ ፈታኝ የግንባታ ምዕራፎች በእነዚህ ዓመታት አልፈዋል።

በዚያው ልክ ፍጥነቱን በገቱ፣ ጊዜውን ባጓተቱ የግንባታ ምዕራፎችም ተፈትኗል። በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተይዘው የነበሩት የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የብረት ገጠማ ስራዎች በጥራትና በፍጥነት ከደረጃቸው ዝቅ ማለትም ከፈተናዎቹ የሚመዘዙ ናቸው። በግንባታ ፕሮጀክቱ የተስተዋሉ የአስተዳደርና የብልሹ አሰራር እንከኖች በተጨማሪ በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ከፈተናዎች ውስጥ ነጥሎ የግድቡን ሕልውና በመታደግ ደረጃ በለውጡ መንግስት የተወሰዱ ጥናት ላይ የተመረኮዙ አሰራሮችና ውሳኔዎች አበርክቷቸው ከፍ ብሎም ይነሳል። ያለፉት ስድስት ዓመታትም የግድቡ ትንሳኤ ተብለው የሚጠቀሱትም በዚሁ ምክንያት ነው። የወቅቱ ፈተና ታሪካዊ ሁነት እውን ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹የዛሬ አምስት ዓመት እዚህ ቦታ ስንመጣ ይሄ ግድብ ውሀ አልነበረውም። ይሄ ግድብ ይህ ግርማ ሞገስ አልነበረውም። ይሄን ግድብ ከችግሩ አውጥተን እናርቀው፣ እናርመው ሲባል ፈተናውም ቀላል አልነበረም። ያን ጊዜ የነበረውን ፈተና የምናውቅ እናውቃለን፤ የሌሉ ሰዎች ላይገባቸው ይችላል›› ብለዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት ግን የግድቡን ግንባታ ለማጓተት ቢቻልም ለማስቀረት የሚደረጉ ተፅዕኖዎች ቀላል አልነበሩም። ከካርቱም እስከ ግብፅ ደግሞም እስከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የዘለቁ ውንጀላዎች ከእነዚህ ይመነዘራሉ። የውስጥ ፈተናዎችም የግድቡ ግንባታ መሰናክሎች ነበሩ። በፈተናዎች ውስጥ የፀናው የግድቡ ግንባታ ሐምሌ 2013 ዓ.ም በግድቡ ሁለት የሀይል ማመንጫ ተርባይኖችን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ውሀ መያዝ የቻለበት ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ተከናወነ። በኢትዮጵያ በኩል ከተፋሰሱ ተጋሪ ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጥረቱን የቀጠለው ግንባታው በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም የግድቡን ግራና ቀኝ ከፍታ 611 ሜትር ላይ አድርሶ ውሀው በግድቡ አናት ላይ መፍሰስ መጀመሩ ተበሰረ።

በዚህ ሶስተኛው ዙር የተያዘው የውሀ መጠን 22 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲደርስም አድርጎታል። ባለፈው ዓመት አራተኛ ዙር የውሀ ሙሌትም ተከናውኗል። ከሰሞኑም ግድቡ ሌላ የስኬት ምዕራፍ የግድቡ ሶስተኛና አራተኛ ተርባይነሮች ስራ ጀምረዋል። ወደ ታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ተጨማሪ የውሀ ማስተንፈሻ በሮችም ተከፍተዋል። ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሲቪል ስራው እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ ይጠናቀቃል። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ የሰጡበት፣ ምኞት ተስፋቸውን የጣሉበት፣ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን መሀንዲስ፣ የፋይናንስ ምንጭም ሆነው የገነቡት ግድብ ነው።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እንደ ዓባይ ገባሮች በሕብራዊነት የተዋሀደ፣ በሕዝቦች አንድነት ከጉባ ተራራ ስር እውን የሆነ ነው። ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እራትም ብርሀንም የሆነ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ግድብ ነው። ዓባይ ለዘመናት የረባ ጥቅም ሳይሰጥ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደድ የሚታይ እንጂ የማይበላ እንጀራ ሆኖ መቆየቱንም እንደትዝታ የምንዘክርበት፣ የታሪክ ምዕራፎች የተዘጉበት እውነት ላይ ደርሰናል። በበርካታ ውጣውረዶች ውስጥ ያለፈው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከባድ የሚመስሉ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ተሻግሮ አሁን ላይ ወደ ፍፃሜው እየተንደረደረ ይገኛል።

ምንም እንኳ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የግድቡን መገንባት ተከትሎ ድርቅ ሊከሰት ይችላል፣ የአስዋን ግድብ ይቀንሳል የሚሉ ክሶችን ሲያቀርቡ ቢደመጡም አሁንም ግን ኢትዮጵያ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውሀ አቅርቦት እንዲደርሳቸው እያደረገች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዳሉትም፤ ኢትዮጵያ ብቻዋን ለመጠቀም ምን አይነት ፍላጎት የላትም። ኢትዮጵያውያን ተካፍሎ መብላት የሚወዱ ሕዝቦች ናቸው። እንደ ሀገርም ኢትዮጵያ ማንንም የሚጎዳ የዲፕሎማሲ መንገድ ተከትላ አታውቅም። በታሪኳ ያስተናገደቻቸው መሪዎችም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ትብብር የሚሹ እንጂ ተቃርኗዊ ዲፕሎማሲ ተከትለው አያውቁም።

ኢትዮጵያ በርካታ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫና ቢኖርባትም በሕዳሴ ግድብ ላይ የምታከናውነውን ስራ ለሰከንድ ሳታቋርጥ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የዕውነት፣ የዕውቀትና የፍትሀዊነት መርህን ይዛ በትብብር መንገዶችም ውጤታማ ሆናለች። ከጉባ እስከ ፀጥታው ምክር ቤት የደረሰ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አጀንዳ ከሰሞኑ ብስራትን አሰምቶናል።

የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሆኑት ግብፅና ሱዳን አሳሪ ስምምነት ሳይፈረም ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ እንዳትሞላና ስራ እንዳትጀምር ሲፈጥሩት የነበረውን ጫና ተሻግሮ ተጨማሪ የኃይል ማመንጨት ደረጃ ላይ ይገኛል። ሕልምም እውን ሆኗል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዋጋ የከፈሉበት የሕዳሴ ግድባችን የሚጨበጥ ተስፋ ሆኖ የሕዝቦች ኩራትም እየሆነ ይገኛል።

ያለፈውንም ሆነ መፃኢ ጊዜዋን የውሀ አካላት የሚወስኑላት ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ድልም በዓለም መድረክ ገናናነቷን ለመመለስ መስፈንጠሪያዋ ነው። የዲፕሎማሲ ጫናናን ተቋቁማ የአፍሪካ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚሰጥ ትምህርትን ለተቀረው ዓለም አስተምራለች። የፕሮጀክቱ ሂደት ጥቅል ስኬቱ ግን የሕዝብ አብሮነት በፈተና ውስጥ መፅናት፣ የአቅምና የዕውቀት ትብብር የማያሳካው እንደማይኖር በጉባ ሰማይ ስር አስመስክሯል። ሕዝቦቿም ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆነው የልማት ጦርነትን እንዴት እንደሚያንኮታኩቱ በጉባ አሳይተዋል ማለት ይቻላል።

ለመጠናቀቅ ጫፍ የደረሰው ግድባችን አሁንም የሕዝቡን ተሳትፎ ይሻል። አንድም በደለል እንዳይጠቃ ችግኞችን በብዛት መትከል ሁለትም ሕዝባዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የምርቃት ሪባኑ እስከሚቆረጥ በሕብረት መቆም ይጠበቃል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዛሬ ከማይቀለበስበት ምዕራፍ ቢደርስም ሂደቱ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ የተለፋበት፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነው በጉልበትም፣ በገንዘብም የተሳተፉበት፣ በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ ያለፈ ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ልማትና ብልፅግና ወደኋላ እንደማይሉ በተግባር ያሳዩበት ፕሮጀክት ነው።

ታዲያ በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተስተዋለው የኢትዮጵያውያን አብሮነት በዛሬው የሕልውና ጥያቄአችን የባሕር በር ላይ ሊደገም ይገባል። የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ለኢትዮጵያ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም። እንደ ከዚህ በፊቱ መቀጠል አንችልም። የብሔራዊ ጥቅም፣ የመኖር አለመኖር የሕልውና ጉዳይ ነው። ይህንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተገንዝቦ ሕዳሴ ግድብ ላይ እንደ ኢትዮጵያዊ ያሳየነውን መተባበር እና ድል የባሕር በር ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ላይም ሊደግመው ይገባል።

ኢትዮጵያ ጠላቶቿ እንድትተራመስ ቢወጥኑም፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተፅእኖ እንዲደረግባት ግፊት ቢያደርጉ ስለ አባይና ስለምታገኘው የባሕር በር ብቻ አይደለም፤ በአጠቃላይ ሀገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በዓለም አቀፍ የውሀ መስመሮች ላይ ስለምትፈጥረው አቅም እንጂ። ለዚህም ነው ትላንት የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማሰናከል የተነጣጠሩ የሴራ ወንጭፎች ዛሬም በባሕር በር ጥያቄዎች ላይ በድጋሚ የሚወረወሩት።

እነዚህን ሴራዎች አክሽፎ ለማለፍ በሕዳሴው ግድብ ላይ የነበረን አንድነት በባሕር በር ጥያቄአችን ላይም ተጠናክሮ ሊደገም ይገባል። ዓባይ ላይ እንደተባበርን ሁሉ በባሕር በር ጉዳያችን ላይም በዛው ልክ መተባበር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በሁለትና በሶስት በኩል የባሕር በር ማግኘቷ ሀገራችን ላይ የሚያመጣውን ጥቅም መገንዘብ ያስፈልጋል። የንግድ ሁኔታችን ይጨምራል፣ የኢኮኖሚ ሁኔታችን ያድጋል፣ ደህንነታችን የተረጋገጠ ይሆናል፣ የፖለቲካ ችግሮቻችንም በዛው ልክ እየተቀረፉ ይሄዳሉ።

ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፈችም ቢሆን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ባለበት ደረጃ ማድረሷ ትልቅ ስኬት ነው። የአሁኑ ትውልድ የአንድነት ማሰሪያና የጋራ ቋንቋም የባሕር በር ሊሆን ይገባል። በዚህ ረገድ ትላንት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጥንስስ ጅማሮ እንደሆነው ሁሉ የዛሬውም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምንም እንከን ሳይገጥመው የሚሳካ አይደለምና የጠነከረ አቋም፣ ሕዝባዊ አንድነትና የበሰለ የድርድር ስራን የሚፈልግ ነው። ይህ ደግሞ የመንግስትንና የሕዝብን ጣምራ ስራን ይፈልጋል።

በእርግጥ ዛሬ ላይ ከብዙ አንድ ከሚያደርጉን ነገሮች ይልቅ የሚለያዩንን ጥቂት ነገሮች ለማጉላት የሚሞክሩ አይጠፉም። ግን ደግሞ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ስራዎች የአብሮነታችን ውጤቶች ናቸው። ይህን ስኬት በባሕር በር ባለቤትነት ለማስቀጠልም የኢትዮጵያውያን አንድነትና በጋራ መቆም፣ መተባበርና መደማመጥ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው። ለውጭ ጠላቶች የኢትዮጵያን ብልፅግና ማጨናገፊያ መንገዶች የሀገር ውስጥ አለመግባባቶች እንደመሆናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን በአግባቡ ተረድቶ አንድነቱን ይበልጥ ሊያጠናክር ይገባል!

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You