• ከአንድ ሺ በላይ ሕገወጥ ግንባታዎች ተገንብተዋል
• ለመምህራን በተገነባው ቤት ሕገወጦች ገብተውበታል
ሐረር፡- በሐረሪ ክልል ከለውጡ ሂደት ጋር ተያይዞ በነበረው ትርምስ ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ችግሮች እና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንደነበር የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልሀኪም አብድልማሊክ በስፍራው ለተገኘው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በጥብቅ የደን ልማት በተለይም በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተሰራውና ሀገር በቀል ዕጽዋት እና ፍራፍሬ የሚገኝበት ሴላት ፓርክን ጨምሮ፣ በጀጎል ግንብ ውስጥ እና ዙሪያው እንዲሁም የሃይማኖት ስፍራዎች ሳይቀር ከአንድ ሺ በላይ ሕገ ወጥ ግንባታዎች እና የመሬት ወረራዎች ተካሂደዋል፡፡ በተጨማሪም 150 ሄክታር መሬት በሕገ ወጥ መንገድ ተይዟል።
መምህራንም ካላቸው አነስተኛ ደመወዝ ሃያ በመቶ ቆጥበውና ሰማንያ በመቶ ከባንክ በተገኘ ብድር የተገነባላቸው ቤት ተጠናቅቆ ርክክብ ሊደረግ በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት ሕገወጥ ግለሰቦች ሰብረው በመግባት እየኖሩበት እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
አቶ አብዱልሀኪም እንደሚሉት፤ የሕግ የበላይነት ተጥሶ ሥርዓት አልበኝነት ሲነግስ በትዕግስት ሲታለፍ የቆየው የለውጡ ባህሪ የተወሰነ መንገራገጮች ይኖሩታል በሚል ነበር። ሆኖም ነገሩን ለማረጋጋት ብዙ ጊዜ በመውሰዱ ሕገወጥ ድርጊቱ ተከስቷል።
ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቂ ካሳ አላገኘንም የሚለው ጥያቄም መልስ ሳያገኝ የቆየው በዚህ ችግር ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው ፤ መረጋጋቶች ሲሰፍን ከሕዝቡ ጋር ተወያይቶ ወደ 59 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ካሳ መከፈሉን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አብዱልሀኪም ገለጻ፤ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ አካላት ላይ የተለያዩ ሥራዎች ተሰርተዋል። የመጀመሪያው በተሃድሶ የሥነምግባር ችግራ ቸውን እንዲፈቱ ማድረግ ሲሆን፤ ሌላው በዚህ ያልታረሙትንና ከፍተኛ የሥነምግባር ችግር ያለባቸውን ደግሞ በመቀነስ እና በአዲስ መልክ በማደራጀት ወደሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
የመምህራኑን ቤት በተመለከተ ደግሞ በሕግ አግባብ በመሄድ በቅርቡ ከሕገወጦች በመቀበል ለመምህራኑ የሚተላለፍበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የመኖሪያ ቤት የሌላቸውን የክልሉ ነዋሪዎችንም የቤት ባለቤት የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
አብርሃም ተወልደ