“አዲሱን ዓመት መቀበል ያለብን በአዲስ እይታ እና በአዲስ ተነሳሽነት ነው” ዘሪሁን ገብሬ (ዶ/ር) የሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዘሪሁን ገብሬ (ዶ/ር) ይባላሉ። ዘሪሁን (ዶ/ር) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሰሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። በሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በማኅበረሰብ ልማት ‘Community Development’ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። ትምህርታቸውን በአገር ቤት ብቻ ሳይወሰኑ ባህር ማዶ በመሻገር በዳላስ ዩኒቨርሲቲ በትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺ (Transformational Leadership) ሦስተኛ ዲግሪያቸውን መስራት ችለዋል።

ዘሪሁን (ዶ/ር) የሊድስታር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ናቸው። በትምህርት ደረጃ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ፣ ሥነ-መለኮት (‘Theology’)፣ ሰላም እና ግጭት አፈታት እና የፕሮጀክት አስተዳደርም ተምረዋል፣ አራት የተለያዩ መጻሕፍትንም ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል። አዲስ ዘመንም እኝህን ምሁር አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የዛሬው የዘመን እንግዳው አድርጎ አቅርቧቸዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።

 አዲስ ዘመን፦ አዲሱን ዓመት እንዴት ልንቀበለው ይገባል? በአዲሱ ዓመት ያቀደው ዕቅድ እንዴት ሊሳካልን ይችላል?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ አዲሱን ዓመት መቀበል ያለብን በአዲስ እይታ እና በአዲስ ተነሳሽነት ነው ብዬ አምናለሁ። አዲሱን ዓመት በአዲስ ሂደት፣ በአዲስ ግብ እና በአዲስ መርሃግብር መቀበል አለብን። ይህ አንድ ብለን የጀመርነው አዲስ ዓመት በእኔ አተያይ ሁለት ትልልቅ ነገሮች ይዞ ይመጣል። ይኸውም አንዱ እድል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ፈተና ነው።

እንደሚታወቀው በዓመቱ ውስጥ ያሉት 365 ቀናት ናቸው። እነዚህ 365 ቀናት በሙሉ መሥራት የምንችልባቸው ናቸው የሚል እምነት አለኝ፤ ቀናቱ የተሰጡት ደግሞ ለተመረጡ ሰዎች አሊያም ውስን ለሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ለሁሉም እኩል የሚሰጡ ናቸው። ነገር ግን ዋናው ልዩነቱ የሚፈጠረው በተሰጡን ቀናት ያለን አጠቃቀም ላይ ነው። እነዚህን ቀናት በትክክል የምንጠቀምባቸው ከሆነ ፊታችን ያለው የስኬት ጊዜ ይሆናል። ቀናቱን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ግን በኪሳራ የምንኖርበት ጊዜ ይሆናል። እንዲያም ሆኖ ምርጫው በእጃችን በመሆኑ የእኛው ነው።

ሰዎች አሮጌው ዘመን አልፈው ወደ አዲስ ዘመን ሲሸጋገሩ አንድ ማስተዋል የሚጠበቅባቸው ነገር እንዳለ ማጤን አለባቸው። ይኸውም ወደፊት ያሉትን አማራጮች ማየት መቻል ነው። ምንም እንኳ ያሳለፍነው ዓመት የከፋ ቢሆንም፤ አዲሱን ዓመት በአዲስ ስኬት እና በአዲስ ርዕይ መጀመር እንችላለን።

ሁሌም ቢሆን ከአዲሱ ዓመት ጋር የሚመጣ አዲስ ጥንካሬ እና አዲስ ሀሳብ ይኖራል። ይህም በአዲሱ ዓመት ውስጥ ያሉትን ቀናት ሁሉ በጥበብ መጠቀም የስኬት መንገድ ነው። ቀናቱን በትክክል በተሰጠን አግባብ አለመጠቀም ግን ኪሳራ ነው። ስለዚህ አዲሱ ዓመት ይዞ የመጣውን አዳዲስ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም የኛ ድርሻ ነው።

በሌላ በኩል አዲሱ ዓመት የራሱን ትግል እና ውጣ ውረድ ይዞ ይመጣል። ትናንት ከነበርንበት ሕይወት መውጣት ራሱን የቻለ ትግል ነው፤ ከትናንቱ ስህተቶቻችን ለመታረም መሞከር ይህም ትግል ነው፤ ከትናንት ውድቀት ለመውጣት መጣርም እንዲሁ ከባድ ትግል ነው። ስለሆነም ካለንበት ውድቀት እና ጥላቻ ወጥተን ፍቅርን ለማዳበር ጠንካራ ትግል ይጠይቃል።

በአዲሱ ዓመት ትግሉን ለማሸነፍ ከትናንት ተምረን ለሚመጣው ነገር መዘጋጀት አለብን። በአዲሱ ዓመት የትናንቱ ውስብስብ የሆኑ ችግሮቻችን እንደገና እንዳይዙን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ አመራር አና ሀገር ከችግሮቻችን ለመውጣት የምናደርገው ጥረት ጠንካራ ትግል ይጠይቃል። ስለዚህ በአዲሱ ዓመት ራሳችንን ለቀጣይ እድሎች እና ትግሎች ማዘጋጀት የግድ የሚለን ይሆናል።

በአዲሱ ዓመት የትናንትናን ያልተሳካ ኑሮ እንደገና ላለመኖር መወሰን አለብን። በአዲሱ ዓመት እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ እና ሀገር ከፊታችን ላሉ እድሎች እና ትግሎች ራሳችንን ማዘጋጀት ትልቁ ጉዳይ ነው።

ወደ አዲሱ ዓመት ከመሸጋገራችን በፊት የባለፈው ዓመት ዕቅድ እና አፈፃፀም መገምገምም ይጠበቅብናል። እንዲሁም የአዲሱን ዓመት ዕቅዳችን እና ርዕያችንን በጥልቀት መመልከት እና መገምገም አለብን። በምናደርገው ግምገማ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችን በመለየት በአዲሱ ዓመት ክፍተቶቻችንን በመሙላት ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። የዿጉሜን ቀናት የባለፈው ዓመት አፈፃፀማችን የምንገመግመው እና ለአዲሱ ዓመት በአዲስ እቅድ እራሳችንን የምናዘጋጅበት ጊዜ ነው።

አዲሱ ዓመት ችግሮቻችንን ለመፍታት ከፍተኛ ትግል የምናደርግበት ጊዜ ይመስለኛል። በአመቱ አዲስ ሕይወት መኖር መጀመር አለብን። ባለፈው አመቱ ያልተሳካልንን ጉዳይ በማስታወስ ያ እንዲህ መሆን ነበረበት እያልን የምንተክዝበት ሳይሆን፤ በቀጣዩ ዓመት ምን መሆን አለበት የሚለው ላይ ማተኮር የተሻለ ነው ባይ ነኝ።

አዲሱን ዓመት አዲስ የሚያደርገው ዓለምን እንዴት እንደምንመለከተው እና በአዲስ መልኩም ውሳኔ የምናሳልፍበት ነው። ይህንን እንደ ማኅበረሰብ እና መንግስት ማሰብ በጣም አስፈላጊ ነው:: አዲሱ ዓመት ለችግሮቻችን መፍትሄ የምንፈልግበት እንጂ በትናንትናው መሰናክል የምንያዝበት ዘመን መሆን የለበትም።

በአጠቃላይ ይህ የተያያዝነው አዲስ ዓመት ብዙ እድሎችን እና ፈተናዎችን ይዞ ወደ እኛ እየመጣ ነው። ዕድሎቹን ተጠቅመን ትግሉን ለማሸነፍ እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። በአመቱ ከስህታችን በመማር በሚቀጥለው ጊዜ የተሻለ ሥራ ለመስራት ማዘጋጀት አለብን።

መዘንጋት የሌለበት ነገር ያለፈውን መለወጥ ባንችልም ዛሬን ልንጠቀምበት እና ለነገ እራሳችንን ማዘጋጀት እንደምንችል ነው። የእኛ አመለካከት ለዚህ ወሳኝ ነው። አንድ ሰው አመለካከቱ ከተቀየረ ሕይወቱ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታው ይለወጣል።

ጠንካራ ሰዎች እድሎችን ሲመለከቱ፣ ደካማ ሰዎች ደግሞ መሰናክሎችን በማሰብ ተስፋ ይቆርጣሉ። ጠንካራ ሰዎች ስለወደፊቱ ስኬት እና እድገትን ያስባሉ። ደካማ ሰዎች ደግሞ ስለ ውድቀት ያስባሉ። ደካማ ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ብቻ ላይ ያተኩራሉ። ጠንካራ ሰው ለመሆን በአመለካከታችን ላይ መሥራት አለብን።

አዲስ ዘመን፦ ከፊታችን ያሉትን እድሎች ለመጠቀም እና ትግሉን ደግሞ በድል ለመሻገር እና ስህተታችንን ለማረም እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ እና ሀገር ምን ማድረግ አለብን?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ ሰው ከውድቀቱ፣ ከድክመቱ እና ከስህተቱ የበለጠ ይማራል። የማይታበለው ሀቅ ቢኖር ለዓመታት እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ እና ሀገር የሰራናቸው ብዙ ስህተቶች አሉ። ስህተቶቹ ከአሮጌው ዓመት ጋር አልፈዋል። በአዲሱ ዓመት ውስጥ ያሉ 365 ቀናት በትክክል ለመጠቀም አዲስ እቅድ እና መርሃ ግብር በማውጣት በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል። የዓመቱን ቀናት በሙሉ በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው በዓመቱ ብዙ ነገሮችን ማከናወን እንችላለን። ዕቅዳችንን ተግባራዊ ካላደረግን ግን ባለንበት እንቆያለን። ስለዚህ ካለፈው ተምረን ከፊታችን ለሚመጡት አዳዲስ ነገሮች እራሳችንን ማዘጋጀት ብቁ ማድረግ ከእኛ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።

ከፊታችን ባሉት ቀናት ውስጥ ጠንክረን የምንሠራበት ጊዜ መሆን አለበት። ቁጭ ብለን ስለ ትናንት ድክመታችን ከማሰብ ተግተን በመስራት ከችግር እና ከድህነት መውጣት የእኛ ድርሻ ነው ባይ ነኝ። የሚያጋጥሙን ችግሮች እንቅፋት ሳይሆን ጠንክረን እንድንሠራ እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባል። ስላለፈው ነገር መጨናነቅ ትተን የወደፊቱ ላይ አተኩረን መሥራት ከአንድ ብልህ ሰው የሚጠበቅ ነው።

ቀናት በራሳቸው ጥሩም መጥፎም አይደሉም:: ቀናትን ጥሩ እና መጥፎ ናቸው ብለን ባንፈርጃቸው መልካም ነው። ምክንያቱም መልካሙን እና ክፉውን ቀን የሚወስኑት የምንኖርበት ሁኔታ ነው። በፊታችን ያሉትን ቀናት በትክክል ከተጠቀምንበት ይሳካልናል፤ ካልተጠቀምንበት ግን ስኬት የለም። በመጪዎቹ ቀናት በትክክል ለመጠቀም አዳዲስ አመለካከቶች፣ አዳዲስ እቅዶች እንዲሁም መርሃ ግብሮች እና ግቦች ሊኖረን ይገባል:: ያለፉት ቀናት ተመልሰው አይመጡም። ስለዚህ ከፊታችን ያሉትን ቀናት በተሻለ ሁኔታ መጠቀም የግድ ይለናል። ሁሉን ቀናት በአዲስ አእምሮ እና ፕሮግራም መቀበል አለብን። ለመጪው አዲስ ዓመት ያቀድነውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀትም ቁርጠኛ መሆንም ከእኛ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።

አዲስ ዘመን፦ በአዲሱ ዓመት ዕቅዳችንን በትክክል ለማሳካት ምን ማድረግ አለብን?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ ዕቅድ የስኬት አንድ በመቶኛ ሲሆን፣ 99 በመቶው የእቅዱ አፈፃፀም ነው። ስኬታማ ሰዎች የዕቅድ ጥቅምን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው:: የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ ሰዎችም የዕቅድ ጥቅም በደንብ የገባቸው ናቸው:: ዕቅዳችን ተግባራዊ ካልሆነ ግን በወረቀት ላይ የሚቀር ይሆናል። ስለዚህ የዓመቱን ዕቅዳችን በግማሽ ዓመት፣ በሩብ ዓመት፣ በወራት፣ በሳምንታት፣ በቀናት እና በሰዓታት ከፍለን ተግባራዊ ማድረግ አለብን። የእለት ተእለት ሥራዎቻችንን እየገመገምን መሄድም ይጠበቅብናል። ተግባራዊ ያልሆነ ዕቅድ ከነምክንያቱ መቀመጥ አለበት።

እቅድ ሲባል አሁን ባለንበት እና መድረስ በምንፈልግበት መካከል ያለ ድልድይ ነው። የምንፈልገው ቦታ ለመድረስ ድልድዩን እየገነባን መሄድ አለብን። ርዕያችን የሚሳካው በዕቅዳችን አፈፃፀም ነው። ስለዚህ ለነገ ዛሬ ማቀድ አለብን:: ዕቅድ አቅደን አለመተግበር ግን ጊዜ ማባከን ነው። ስለዚህ ያቀድነውን እቅድ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። የዕቅድ አፈፃፀማችን በየጊዜው እየገመገምን ካልሄድን በመጨረሻ እንዳሰብነው አይሆንም። ዕቅዳችንን ተግባራዊ ማድረግ ካልቻልን በየዓመቱ ማቀድ ብቻ ሆኖ ይቀራል።

አዲስ ዘመን፦ ባለፈው ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተስተውለው የቆዩትን የጸጥታ ችግሮችን በአዲሱ ዓመት እንዳይደገሙ ለማድረግ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ የአገራችን የጸጥታ ችግር ብዙ ነገሮችን የሚያካትት ነው፤ ቢሆንም በሚከተሉት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ለወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር ላይ ነው ባይ ነኝ። ስራ አጥነት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግር ሲሆን፣ ድህነት ደግሞ የታዳጊ ሀገራት ትልቁ ፈተና ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በተደረገ አንድ ጥናት መሰረት ከስድስት ወጣቶች መካከል ስራ የሚያገኘው አንዱ ወጣት ብቻ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ስራ አጥነት 50 በመቶ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 89 በመቶ የሚሆነው በታዳጊ ሀገራት ነው። በወጣቶች ላይ መስራት ማለት ሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እንደመስራት የሚቆጠር ነው።

ሳይሠራ የሚበላ ሰው ችግር ለመፍጠር ዝግጁ ነው:: “ሥራ ፈት አእምሮ የሰይጣን መመሪያ ነው” ይላሉ ፈረንጆች። ስለዚህ ለወጣቶች ተጨማሪ የስራ እድል ቢፈጠር ግጭቶች እና የጸጥታ ችግሮች በዚህ አይቀጥሉም ብዬ አምናለሁ። በሁለተኛ ደረጃ መልካም አስተዳደርን እስከ መንደር ድረስ ማስፈን ነው፤ መንግስት በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፈታት አለባቸው።

ሦስተኛው የሀገሪቱን የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት ለጸጥታ ችግር መንስኤ ወይም ምንጭ ናቸው የተባሉትን ነገሮች በአግባቡ መመርመር አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ። የጸጥታ ችግርን ለመፍታት የሀገሪቱ ሕብረተሰብ ካለፈው በመማር በሠላም ግንባታ ላይ በጋራ መሥራት አለበት። በጸጥታ ችግር ከደረሰብን ጉዳት ተምረን ሠላም እና ጸጥታን ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን፦ የአገራችን እና ያደጉት አገራት የስራ ባሕል እንዲሁም የጊዜ አጠቃቀምን እንዴት ይገልፃሉ?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ ያደጉ አገሮች የሥራን እና የጊዜን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ:: ሳይሠሩ መኖር እንደማይችሉ አሳምረው የተረዱ ናቸው። ለአብነት ያህል መጥቀስ ካስፈለገ በአገራችን ቡናን አንድ ጊዜ በመትከል በየዓመቱ ምርት እናገኛለን። በአገራችን ትንሽ በመስራት መኖር ስለሚቻል የስራ ባህላችን ደካማ ነው።

በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የዋጋ ንረት ለመፍታት የስራ ባህላችን ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት እላለሁ። ለውጥ ለማምጣት እንደ ግለሰብም ሆነ በምንሰራበት ድርጅት ውስጥ የስራ ባህላችን ሙሉ ለሙሉ መለወጥ ብሎም በአፋጣኝ መሻሻል አለበት። አለበለዚያ ዛሬ ላለው ትውልድ ነገ ቀላል የሚባል ጊዜ አይሆንም።

የተያያዝነው አዲሱ ዓመት የውድድር ዘመን ነው፤ በመሆኑም ጊዜያችንን በአግባቡ በመጠቀም እማ ጠንክረን በመስራት ብርቱ ተፎካካሪ መሆን አለብን። ሠርተን ከምናገኘው ገቢ መቆጠብ እና ከቆጠብነው ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግ አለብን። ጊዜው የውድድር ነው፤ ስለሆነም ይህ ትውልድ በውድድር ዘመኑ ጠንካራ እና ተፎካካሪ ለመሆን ጠንክሮ መስራት አለበት።

ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ያልቻሉ መተዳደሪያ እስኪያጡ ድረስ ሊሰቃዩ ይችላሉ። ዘመኑ የዲጂታል ስለሆነ ወደፊት በመዝረፍ ወይም መስረቅ አይቻልም። ስለዚህ የሚያወጣን ጠንክረን ለመስራት ዝግጁ መሆን ብቻ ነው።

ያልተዘጋጀ ሰው ራሱን ላዘጋጀ ሰው ሠራተኛ ይሆናል። ራስን ማዘጋጀት ማለት እግዚአብሔር የሰጠን ጊዜ እና ስጦታ በደንብ ለመጠቀም መዘጋጀት ማለት ነው። አንድ ቀን 24 ሰዓት አለው። እግዚአብሔር የሰጠንን ጊዜ እና አእምሯችንን ለመጠቀም እራሳችንን ማዘጋጀት አለብን። ስኬታማ ለመሆን አእምሮአችንንና ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም ይኖርብናል።

ጊዜን መበደር፣ ማበደር፣ መውሰድ፣ ማቆም፣ ማራዘም፣ ማሳጠር አንችልም። በጊዜ መጠቀም ስኬታማ እንደሚያደርግም ሁሉ በትክክል አለመጠቀም ደግሞ የውድቀት መንስኤ ነው። ስለዚህ ጊዜን በትክክል የመጠቀም ጥቅም በደንብ መረዳት አለብን።

ብዙ ወጣቶቻችን በማኅበራዊ ድህረ ገጽ ላይ የሚለቀቁትን ቀልዶች በማየት ጊዜያቸውን እያጠፉ ነው። አሁን ካሉበት ኑሮ ለመውጣት ራሳቸውን በትምህርት ማዘጋጀት አለባቸው። ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ነገር መጠቀም መቻል አለባቸው።

ማኅበራዊ ሚዲያን ሕይወታችንን ለመቀየርና ለማሻሻል መጠቀም አለብን። ስለ አንተ የሚያስብ የመጀመሪያው ሰው ራስህ ነው። ሌላው ቀጥሎ ይመጣል። አሁን ያለው ትውልድ ራሱን ለመለወጥ ዝግጁ ካልሆነ ራሱን ለመለወጥ ለተዘጋጀ ሰው ሠራተኛ ወይም ይመስላል ይሆናል። ትክክለኛ ራዕይ ለስኬታችን ወሳኝ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ወጣቶች የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው ሕይወት እንዲቀይሩና በሀገሪቱ ልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ብዙ ወጣቶች አሏቸው። በቀድሞው መረጃ መሰረት 87 በመቶ ወጣቶች በታዳጊ ሀገራት ይገኛሉ። እንደ ሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ጥቅሙ ከፍተኛ ነው። ምሁራንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሊሰሩ ይገባል። በትውልዱ ወይም ወጣቱ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ በሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እንደመስራት የሚቆጠር ተግባር ነው።

ብዙ ሀገሮች ያደጉት በወጣቶች ላይ በመሥራት ነው። ስለዚህ እንደ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና ሀገር በወጣቶች ላይ መስራት አስፈላጊ ነው። የሀገራችን የትምህርት ስርዓትም የወጣቶችን የወደፊት እጣ ፈንታ በደንብ የሚያመለክት መሆን አለበት። ወጣቶች ላይ ብንሠራ ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለአገራቸው ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ:: እንደ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ወጣቶችን የሚያበቃ እና መንገድ የሚያሳይ መሆን አለበት።

ወጣቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለማሻሻልና የወደፊት ሕይወታቸውን ስኬታማ ለማድረግ በንቃት መሥራት አለባቸው። ተሠርተው ከሚያገኙት ገቢም መቆጠብ አለባቸው።

ብዙ ወጣቶች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ሥራ በመፈለግ ሰፊ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ። የስራ እድል መፈለግ ብዙ ፈተናዎች አሉት:: የስራ የማግኘት ዕድልም ጠባብ ነው:: ስለሆነም ወጣቶች ተቀጥረው ከመሥራት የራሳቸውን ስራ መፍጠር ላይ ማተኮር አለባቸው ባይ ነኝ። ተቀጥሮ መሥራት እና የራስን ሥራ ፈጥሮ በግል መሥራት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ተቀጥሮ የሚሠሩ ሰው ገቢው በወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የራሱ የግል ሥራ የሚሠራ ሰው ግን በየቀኑ ገቢ ያገኛል። የራሱን ስራ ፈጥሮ የሚሠራ ሰው ከራሱ አልፎ ለሌሎች ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል። በዚህም እንቅስቃሴው ለአገርም ይተርፋል።

ወጣትነት የሚሮጡበት እና የሚሠሩበት ጊዜ ነው፤ ስለሆነም ወጣቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በጥበብ መጠቀም አለባቸው። ወጣቶች አልባሌ ቦታ መዋልና ከመጥፎ ጓደኞቻቸው ጋር ከመዋል ራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው። ይህ ትውልድ ስለራሱ እና ለቀጣይ ትውልድ መልካም ነገርን ለማስተላለፍ ተግቶ መስራት ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን፦ የዿጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ተሰይመው በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተከብረው አልፈዋል። በዚህም መሰረት ጳጉሜ 1 ‘የሽግግር ቀን’ ተብሎ ተከብሯል። ሽግግር ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት መሻገርም ጭምር ነውና ከዚህ በመነሳት ‘ሽግግር’ የሚለውን ቃል እንዴት ይገልጹታል?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ በዚህ አገላለጽ ሽግግር የሚለው ቃል ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገርን ያመለክታል። ወደ አዲሱ ዓመት ከመሻገራችን በፊት ጠራርገን ማስወገድ ያለብን ብዙ አሮጌ ነገሮች አሉን። ከአሮጌው አመለካከታችን ወጥተን በአዲስ እይታ ወደ አዲሱ ዓመት መሄድ አለብን። አመለካከታችን የወደፊት ሕይወታችንን ይወስናል። በአዲሱ ዓመት እንደ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ እና ሀገር በአዲስ አስተሳሰብ፣ ሂደት እና ራዕይ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር አለብን።

አዲስ ዘመን፦ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ለሕዝብ እና ለሀገሪቱ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖርዎ ይሆን?

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ በአዲሱ ዓመት (2017 ዓ.ም) ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት፣ በፍቅር እና በደስታ አብረው የሚኖሩበት፣ ሰዎች በነፃነት ወደ ፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበት ወቅት እንዲሆን ትልቁ ምኞቴ ነው። ሰዎች ወደፈለጉበት አቅጣጫ ተንቀሳቅሰው የሚነግዱበት፣ የሚማሩበት እና በሁሉም መንገድ የተሳካ ዓመት እንዲሆንላቸውም እመኛለሁ።

በአዲሱ ዓመት ሰዎች በነገሮች የሚጣሉበት ሳይሆን፣ ያለው ሰው የሌለውን የሚረዳበት፣ የሚመራው አመራር ለሚመራው ሕዝብ የሚያስብበት፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚከባበሩበት ዓመት እንዲሆን መሻቴ ነው። ያለፈው ነገር ለሕዝባችን እንደ ሕልም ሆኖ የሚደነቁበት ጊዜ እንዲሆን እመኛለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ለሰጡን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን።

ዘሪሁን (ዶ/ር)፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You