አዲስ አበባ፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተከሉ አራት ቢሊዮን ችግኞች የጽድቀት ደረጃ ለመከታተል ከእንጦጦ ኦቭሰርቫቶሪ ጋር በመተባበር በጂአይ ኤስ ወይንም የጂኦግራፊካል መረጃ ሥርዓት ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገለጸ።
የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን፣ የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ፣ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ፤ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ትናንት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን እንደተናገሩት፤ የችግኝ ተከላው ከአራት ቢሊዮንም አልፎ አራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ችግኞች ሊተከሉ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ታይቷል። ችግኞቹ የሚተከሉበት ስፍራዎች እና የእድገት ደረጃቸው ደግሞ በተደራጀ የሳተላይት መረጃ ይጠናቀራል።
እንደ አቶ ዑመር ገለጻ፤ ከእንጦጦ ኦቭሰርቫቶሪ ጋር በመተባበር በሚሰራው የጂኦግራፊካል መረጃ ሥርዓት መሠረት የችግኝ ተከላው ሂደት ብቻ ሳይሆን በቀጣይም የጽድቀት መጠናቸውንም ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ይኖራል።
የጽድቀት መጠኑም ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን በድረገጾች ይፋ ይደረጋል። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ ለችግኝ ተከላው ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ለመንከባከብም አስፈላጊው ትብብር ማድረጉ አስፈላጊ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በመላ አገሪቷ የሚገኙ መምህራን እና ተማሪዎች እስከ ታችኛው ወረዳ እና የቀበሌዎች አስተዳደር ድረስ የማስተባበር ሥራ ይከናወናል። ችግኞቹን ከማጓጓዝ እስከማጽደቅ ያለውን ሥራው ትም ህርት ሚኒስቴር በኃላፊነት ድጋፍና ክትትል ያደርግበታል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ እንደተናገሩት ደግሞ የችግኝ ተከላው በነፍስ ወከፍ 40 ችግኞችን እንዲተከሉ እቅድ የተያዘበት ነው። በመሆኑም በቀሩት የክረምቱ ጊዜያት በጋራ ተከላውን ለማካሄድ እና እንክብካቤ ሥራውን ለማከናወን ዝግጅቶች መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ከደን ልማቱ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ችግኞች በመዘጋጀታቸው የአግሮ ፎረስት ጥቅም ያላቸው አገር በቀል ዛፎች እና የእንስሳት መኖዎችን እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው እንደ ተናገሩት፣ ከተሞችን ውብ እና ጽዱ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የእጽዋት አስተዋጽኦ ወሳኝነት አለው። ሚኒስቴሩም በከተማ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ በትኩረት ክትትል ያደርግበታል።
የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ደግሞ የአየር ንብረት ለውጡን መቋቋም የሚቻለው የደን ሀብትን በማልማት መሆኑን ጠቅሰው ማንኛውም ዜጋ በርብርብ ተከላውን ብቻ ሳይሆን እንክብካቤውንም እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የአራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላው በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድም በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብረወሰን እንደሚሰብር ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
ጌትነት ተስፋማርያም