ጥራትና ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት ለወጣቶችና አፍላ ወጣቶች

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በቁጥር የበዙ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የጤናና በሌሎችም ሴክተሮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው። ይህንኑ መብታቸውን ለማስከበር ታዲያ ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ለወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ይሁንና ለወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የሚሰጠው አገልግሎት ወጣቱን የሚያረካና በሕይወቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን በጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እናዳለበት ታምኖበታል። ለዛም ነው አምስተኛው የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ጉባኤ ‹‹ተደራሽነትና ጥራት፤ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት ለሁሉም አፍላ ወጣቶች›› በሚል መሪ ቃል ሰሞኑን የተካሄደው።

የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደሚናገሩት፣ ከዚህ በፊት የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት በአብዛኛው ትኩረቱ ተደራሽነት ላይ ነበር። ነገር ግን ተደራሽነት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ከተደራሽነት ቀጥሎ ጥራት ላይ፣ ከጥራት በኋላ ደግሞ ምላሽ መስጠት የሚችል የጤና አገልግሎት ለወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የጤና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች በሁሉም አቅጣጫ ለሚፈልጉት ነገር ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አምስተኛው ጉባኤ ተካሂዷል። ስራው የአንድ ሴክተር ባለመሆኑም ነው በጉባኤው ላይ ትምህርት ሚንስቴርና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተሳታፊ የሆኑት።

የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ተቀይሮ የተለያዩ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ከነዚህ ስራዎች ውስጥ አንዱ መስተካከል፣ መታደስና መቀየር ያለባቸው ነገሮችን ማከናወን ነው። ፖሊሲው መከላከል ላይ ያተኮረ ቢሆንም አክሞ ማዳንንም ያካተተ ነበር። ከዚህ አንፃር ወጣቶች ብዙ ነገር በመያዛቸው አሁንም መከላከል ላይ አተኩሮ መስራት ያስፈልጋል። ወጣቶች በተለያዩ ነገሮች ሲያዙ፣ ሲቸገሩና ሲታመሙ፣ ከአእምሮ ሕመም ጀምሮ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞች ሲጠቁ እንደ ሀገር አክሞ የማዳን አቅም ያስፈልጋል።

ይህንንም ለማድረግ መንግስት ስትራቴጂ በመቅረፅ ከሰነድ አንስቶ የሚተገበሩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በተጨማሪም በሁለተኛው የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅድና በመካከለኛ ዘመን የጤና እድገትና ኢንቨስትመንት እቅድ ውስጥ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ስትራቴጂ የስነ ተዋልዶ ጤና ስትራቴጂዎች ተካተዋል። ስትራቴጂዎች የሚተገበሩት ደግሞ በራሳቸው በወጣቶች፣ በሴክተሮች የበለጠ ደግሞ በማኅበረሰቡ ነው። አሁን ደግሞ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤናቸውን ለመጠበቅ ወደራሳቸው የሚመለከቱበት ግዜ ነው።

ሚንስትሯ እንደሚናገሩት፣ ጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። የ2017 ዓመት ደግሞ የአገልግሎት ዓመት እንዲሆን በመሰየሙ በየትኞቹ የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና አገልግሎት ዙሪያ መስራት እንደሚያስፈልግ መነጋገር ያሻል። ከአመጋገብ ስርዓት አንስቶ የጤና መረጃዎችን እስከመጠቀም ድረስ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ተረድቶ ስራዎችን ማከናወን ይገባል። ምክንያቱም ከጤና መረጃዎች በላይ የሆኑ መረጃዎችን የሚቀበል ትውልድ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የሚወሰደውም የሚሰጠውም መረጃ ምን ያህል ራስን፣ ቤተሰብንና ትውልድን የሚጠቅም እንደሆነ ወጣቱ ማየት አለበት።

ብዙ ወጣቶች በዓለም ላይ ለሳይበር ሴኪዩሪቲ ከዛም በበለጠ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚመጡ ነገሮች ጥቃት የሚደርስባቸው ናቸው። በኢትዮጵያም ቴክኖሎጂው እያደገ በመጣ ቁጥር የኢንፎርሜሽን ወረርሽኝ እየጨመረ ይመጣል። ስለዚህ ቴክኖሎጂውን ተከትሎ የሚመጣውን መረጃ በተገቢው መንገድ መጠቀም ካልተቻለ ወጣቱን ስለሚጎዳ በትብብር መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ጤና ሚኒስቴር በአየር ሰዓት ፕሮግራሙ፣ በማኅበራዊ ሚዲያው ወጣቱን የሚጠቅሙና መረጃዎችን የሚያገኝበትን ስራዎች ከአጋር ድርጅቶችና ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን እያከናወነ ይገኛል።

ጤና ሚኒስቴር አካል ጉዳተኛ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ያማከሉ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም የተሰራው ስራ ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም። ስለዚህ ሁሉንም ወጣቶችን ያማከለ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። አካል ጉዳተኛ ወጣቶችን በጤናው መስክ ተጠቃሚ ሚሆኑባቸውን ስራዎች መስራት ይገባል። በተለይ ደግሞ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የሚያገኙት መረጃ ሙሉ እንዲሆን ማድረግ ትምህርት ሚኒስቴርና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ድርሻ ነው። አጋር ድርጅቶችም ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አካል ጉዳተኛ ወጣቶችን መደገፍ ይኖርባቸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ በወጣቶች ላይ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል አምና የተጀመረው ‹‹የብልህ ጅምር›› የተሰኘው መርሃ ግብር አንዱ ሲሆን ከዚህ በበለጠ ደግሞ ሌሎች ፕሮግራሞችን በመቅረፅ በወጣቶች ላይ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። አፍላ ወጣትነት ደግሞ በብዙ መልኩ ተጋላጭነት የሚታይበት፣ ካልታሰበ እርግዝና አንስቶ ለበርካታ የጤና እክል የሚጋለጡበት ነው። ከዚህ አንፃር የስነ ተዋልዶ ጤና ስራ የሁሉም ስራ ሊሆን ይገባል። በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የሚከናወኑ ትላልቅ ስራዎች ወጣቱን ያማከሉ፣ ወጣቱን መድረስ የሚችሉ ከትምህርት ቤት እስከ እያንዳንዱ መኖሪያ ቤት ድረስ ማንም ሰው በየትኛውም ግዜ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ ከተሰራ ከተደራሽነት በለጠ ጥራት ያለው መረጃ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። ከዚህ አንፃርም በርካታ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል።

በዩኒቨርሲቲዎች፣ በወጣት ማእከላት፣ በስራ ቦታዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች በስነ ተዋልዶ ጤና ወጣቶችንና አፍላ ወጣቶችን ያማከሉ ስራዎች ተጠናክረው ይሰራሉ። ነገር ግን ስራው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ብቻ የሚሸፈን ሳይሆን ወጣቶችን ይበልጥ የሚያሳትፍ የአቻ ለአቻ የጤና ትምህርት በጤና ተቋማት ውስጥና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።

የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፣ የዘንድሮውን አምስተኛው የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ጉባኤ ከባለፈው ጉባኤ በብዙ መልኩ ለየት ያደርገዋል። የዘንድሮው ጉባኤ መሪ ቃል ‹‹ተደራሽነትና ጥራት፤ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓት ለአፍላ ወታቶችና ወጣቶች›› የተባለውም በቀጣይ የሚከናወኑ ስራዎች በዚህ ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ነው። ተደራሽነት ሲባል ደግሞ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ እንደመሆናቸው በነዚህ ቦታዎች ላይ አስፈላጊ የሚባሉ የጤናና በሌሎች ሴክተሮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት አላቸው። ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስትና ሌሎች አጋር አካላት ለወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ሲሰራ ቆይቷል።

ጥራት ሲባል ደግሞ የሚሰጡ አገልግሎቶች የወጣቶችና የአፍላ ወጣቶችን ፍላጎት የሚያረካ፣ በሕይወታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ መሆን አለበት። አዲሱ አራተኛው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ ለአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። ይህም በተለያዩ ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓቶች ውስጥ የሚካተት ስለሆነ የሚገነባው የጤና ስርዓት ለአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የቅድሚያ ቅድሚያ እንደሚሰጥ የሚሰጥ ነው።

ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ስራዎች ለወጣቶችና አፍላ ወጣቶች በጤና ሚኒስቴር በኩል ተከናውነዋል። በተለይ ደግሞ የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እቅዶች ወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን መአከል ያደረጉ እንዲሆኑ ተደርጓል። በእቅድና በዶክመንት ብቻ ሳይሆን በስራዎችም እንዲገለጥ ጥረት ተደርጓል። በዋናነት በየደረጃው መዋቅር እንዲኖርና ካውንስል በየደረጃው ተቋቁሞ ወጣቶች በተለያዩ ደረጃዎች እርስ በርሳቸው እንዲማማሩ ማድረግና ድምፃቸው እንዲሰማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ወጣቶች ለጤና መረጃ ያላቸው ተደራሽነት እንዲሻሻል ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል።

የወጣቶችና አፍላ ወጣቶችን ፍላጎት ማሳካት የሚቻለው ሁሉም ሲረባረብ ነው። ስለዚህ ስራው የጤና ሚኒስቴር ብቻ ባለመሆኑና ዘርፈ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሁሉንም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ርብርብ ይጠይቃል። በተለይ ወጣቶች እርስ በርሳቸው ተደራጅተው የበለጠ ለጤናቸውና ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳያቸው የሚጠቅሙ ስራዎችን ማከናወን ይኖርባቸዋል። በቀጣይም በሀገሪቱ ያሉ ርካታ ጎጂ ባህላዊ ደርጊቶችን ለመቀነስ ጠና ሚኒስቴር ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን እቅድ አስቀምጦ ይሰራል።

ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአብዛኛው ወጣቶችን እያጠቁ እንደመሆናቸው በነዚህም ላይ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት በአስርና በሶስት ዓመት የጤና እቅድ ውስጥ በተለየ መንገድ ተቀምጦ የሚሰራበት ይሆናል።

ከዚህ ውጪ ወጣቶች በአብዛኛው የሚገኙት በትምህርት ተቋማት ውስጥ እንደመሆኑ በዩኒቨርሲቲ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሌሎችም የተለያዩ የልማት አካባቢዎች ላይ በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው። ኢትዮጵያ ከእዳ ወደ ምንዳ በምታደርገው ሽግግር ፈጠራና ፍጥነት በጣም ወሳኝ ናቸው። ስለዚህ ወጣቶች ለፈጠራና የተጀመሩ ስራዎችን በፍጥነት ለመጨረስ ዋነኛና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው በመሆኑ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ ለመቀየር የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።

የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደሚሉት የአፍላ ወጣትነት እድሜ የኅብረተሰቡን የቀጣይ ትውልድ ማፍራት ሁኔታ የሚወስን ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወጣት ቁጥራቸው ከጠቅላላው ሕዝብ አንፃር ከፍተኛ የሆኑባቸው ሀገራት ለወጣቶች አስቻይ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ፣ ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው ካልተረጋገጠ ለሚታሰበው ብልፅግና እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ በአፍላ ወጣቶችና በወጣቶች ዙሪያ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ወጣቶች አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊ፣ ማኅበራዊ ለውጦች የሚከሰትበት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የሕይወታቸው ሂደትና ኡደት ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። ምክንያቱም በዚህ እድሜ ክልል በሚፈጠሩ ስሜታዊነት፣ የአቻ ግፊቶች፣ የመረጃ እጥረት የተነሳ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ለጤናና ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ። የስነ ተዋልዶ ጤና ችግር ደግሞ ለኤች አይ ቪ ኤድስ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች፣ ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለጽንስ ማቋረጥ፣ ለአደንዛዥ እፆች፣ ለአልኮል መጠጦች፣ ለአእምሮ ጤና እክል፣ ለአካል ጉዳትና ለሌሎችም ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

ስለዚህ አፍላ እድሜ ላይ ያሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች ጤናቸው በተሟላ መልኩ እንዲጠበቅ ሁሉም ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። ጤናቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እርስ በርሳቸው ተቀራርበው የሚወያዩበትና ራሳቸው የመፍትሄ አካል የሚሆኑበት መንገድ መዘጋጀት ይኖርበታል። ወጣቶች በራሳቸው የእድሜ ክልል ውስጥ የራሳቸውን ችግር ሲነጋገሩ ይበልጥ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።

ሚኒስትሯ እንደሚያብራሩት እንደ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ባሉ ከ3 ሺ በላይ በሚሆኑ ወጣት ስብዕና መገንቢያ ማእከላት ውስጥ የጤና አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ነገር ግን በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱ እየተሰጠ ባለመሆኑ በላይ የስነ ተዋልዶ ጤናን በሚመለከት ንግግር የሚያስፈልገው ጉዳይ በመሆኑ ለዚህ አፅንኦት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።

ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‹‹ዩ ሪፖርት›› የተሰኘ የዲጂታል ስርአት ተጀምሯል። እስካሁንም ከ20 ሺ በላይ ወጣቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በሌላ በኩል የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚነት በተለይ ደግሞ በግጭት በተፈናቀሉ አካባቢዎች ላይ እየጨመረ መጥቷል። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጤናና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በተለይም የሕግ አካላትን በማሳተፍ የአደንዛዥ እፅ ግብረ ኃይል እዲቋቋም ተደርጓል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 4/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You