የእርሷ ነገር – “ጠብ ያለሽ በዳቦ”

ደብዳቤ ማርቀቁን የተካነችበት የዓመታት ሥራዋ ከሆነ ከራርሟል። የብዙዎቹ ደብዳቤዎቿ ይዘቶችም ኡኡታ! የሞላባቸው ናቸው፣ በደብዳቤዎቿ ግርጌ ያሉ ዓረፍተ ነገሮች ደግሞ “ከኡኡታዬ ጋር አብራችሁኝ ሁኑ” የሚል መልዕክት ያዘሉ ተማጽኖዎች ናቸው። ይህች ሀገር አፍሪካዊ ማንነትን ወደጎን የጣለች ከመሆኗ በላይ ብትችል በዋናነት ኢትዮጵያን ከፍ ሲልም ምሥራቅ አፍሪካን ለማባላት በመጣጣር ላይ የምትገኝ ነች።

ይህች ሀገር፣ ታላቋን ሀገር ኢትዮጵያን የምትፈታተናት ለምን እንደሆነ ከብዙዎቹ የተደበቀ ምስጢር እንዳልሆነ አስባለሁ። ከዘመናት በፊት ሲያባንናት የነበረው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ነበር ፣ ዛሬም ድረስ ሲያስበረግጋት የሰነበተው ይኸው ታላቁ ወንዝ ዓባይ ነው።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም በአራተኛ ምዕተ ዓመት የነበረ አንድ ፋላስፋ፤ ግብጽ የናይል ስጦታ እንደሆነችና ‘ናይልን የተቆጣጠረ ሁሉ ግብጽን በእጁ እንዳደረገ ይቆጠራል’ በማለቱ ፤ ግብጻውያን ገዥዎች ይህንን ቅዠት ተግባራዊ ለማድረግ ለዘመናት ሲሯሯጡ ኖረዋል። የተባሉትን ያንኑ ተረት የሙጥኝ ብለው ዛሬም ድረስ ተጣብቀውበት ቀርተዋል።

በዚህ ባፈጀ አባባል ከመወረሳቸው የተነሳ ሁሌም ሕልማቸው የዓባይን ምንጭ መቆጣጠር ነው ፣ እሱ የማይሳካላቸው ከሆነ ደግሞ የዓባይ ወንዝ አመንጪ የሆነችውን ኢትዮጵያን ማተራመስ የዘወትር እቅዳቸው አድርገው ዘልቀዋል። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ መጣሏን ባስተዋሉ ጊዜ ሀገራችንን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሰላሙ ዙሪያ ለማዳከም በብዙ ኳትነዋል፤ ወጥተዋል፤ ወርደዋል። እነሆ! በቀጥታም ሆነ በተልዕኮ ልማቷን ለማደናቀፍና ሰላሟን ለማደፍረስ ከ13 ዓመታት በላይ ተግተዋል።

ለጊዜው በተዘዋዋሪ የሚያደርጓቸውን ሴራዎች ወደጎን እንዳርግና በቀጥታ ሲያደርጉ የነበረውን የክፋት ጥግ እናስታውስ። ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ገና ግድቡን በጀመረችበት አካባቢ የወንዙን አቅጣጫ መቀየሩን ሲሰሙ “ኡ!ኡ!..” አሉ፤ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ግድቡ የመጀመሪያውን ዙሩ ውሃ መያዝ ጀመረ ሲባል፣ “ያዙኝ! ልቀቁኝ!” ሲሉ ተደመጡ።

በየዓመቱ ሁለተኛውና ሶስተኛው ዙር ውሃ መያዙን ሲሰሙ “እሪ!” በማለት የድረሱልኝ ጥሪ አሰሙ። ሁለቱ ተርባይኖች ተጠባቂውን ኃይል ማመንጨት ጀመሩ በተባሉ ጊዜ ደግሞ “ወይኔ! ጉዴ ፈላ!” ሲሉ አምቧረቁ። ክሳቸውን ይዘው በመሮጥ አብረዋቸው የሚጮኹላቸውን ፈለጉ፤ በዚያም አልሰምር ሲላቸው ኢትዮጵያውያኑን አንዱን በአንዱ ላይ በማነሳሳት ማፋጀትን አማራጭ አደረጉ።

እርግጥ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰባትም ማለት አይቻልም። በተለይ ግብጽ በተልዕኮ በምታደርገው ኢትዮጵያን የማተራመስ ስልት፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰምሮላታል ማለት ያስደፍራል። ለበርካታ ዓመታት እርስ በእርስ እንድንፋጅ የተለያየ ርዕስ እየሰጠችን በብዙ ፈትናናለች፤ አጀንዳ ከመስጠት ባሻገር ፤ ባንዳዎችን እስከማስታጠቅ የዘለቀ ትጋት አሳይታለች። በዓለም አቀፉ መድረክ አቁማን ልትሞግተን ጥራለች፤ “የእኔ ነው” በምትለው በአረብ ሊግ ጉያ ተሸሽጋ ጫና ለመፍጠር ደፋ ቀና ስትል ከርማለች።

ነገር ግን ለግብጽ እያንዳንዱ ርምጃ ኢትዮጵያ አንዴም ቢሆን ሸብረክ ስትል አልተስተዋችም። ግብጽ በክፋት በትር በራችንን ደጋግማ ለማንኳኳት ብትሞክርም ሊከፈትላት አልቻለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ባቀረበቻቸው ተደራራቢ ክሶች ተገቢውን ምላሽ ሲሰጡ የከረሙት የኢትዮጵያ መንግሥትና ምሁራኗ ሁሌም ቢሆን ኢትዮጵያ ውሃውን መጠቀም የምትሻው ፍትሃዊነትን በተላበሰ መንገድ መሆኑንና በውሃ ሀብቱ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት እንዳላት ደጋግመው አስረግጠው ሲያብራሩላት ሰንብተዋል።

ይሁንና ግብጽ እውነታውን እያወቀች ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያን ከልማት ለማሰናከል በብዙ እየጣረች ትገኛለች። በተለይ ልማታችንን ተረጋግተን እንዳናሳልጥ ሰላማችንን በተዘዋዋሪ በማደፍረሱ በኩል

የቻለችውን ያህል ትባዝናለች። የተለያዩ አዳዲስ ርዕሰ ጉዳዮችን እየፈጠረች በሌሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች በመታገዝ ተልዕኮዋን እያስፈጸመች ትገኛለች። ትልቁ እና ዋንኛ ዓላማዋ ደግሞ ኢትዮጵያ በምንም አይነት መንገድ በኢኮኖሚ እንዳትጠነክር፣ በፖለቲካውም እንዳይሳካላት ለማድረግ ነው። በጥቅሉ በቀጣናውም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ተሰሚነት እንዳይኖራት ማድረግ ነው።

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለማዳከም በተናጠል የምታደርገው እኩይ ተግባር አመርቂና አዋጭ ሆኖ ስላልታያት ደግሞ በአሁኑ ወቅት ስልቷን ቀይራ ሌላ የሴራዋ ተጋሪ የሆነ አካል በመጠቀም የተቻላትን ሁሉ በመሞከር ላይ ትገኛለች። ሰሞኑንም የተስተዋለው ጉዳይ ይኸው ነው። ግብጽ፣ አፍሪካዊነቷን አምና ለመቀበል ቋቅ ሲላት መኖሯን ዘንግታው ኢትዮጵያን መጉዳት እችላለሁ በሚል ተላላ እሳቤ ወደሶማሊያ ማቅናቷ በቀጣናው ትልቅ አጀንዳ ሆኖ መወራት ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።

ሶማሊያ፣ ሰላሟን በማረጋገጥ ረገድ እመቤቷ የሆነቻት ኢትዮጵያን ወደጎን አድርጋ ከግብጽ ጋር በአመራሮቿ አማካይነት ሽር ጉድ ስትል እንደቆየችም ተጤኗል። ግብጽ ወደ ሶማሊያ የመሄዷ ነገር ያው የሚታወቅ እኩይ ዓላማ አንግባ ነው። አሯሩጦ የወሰዳት ነገር ወዲህ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍጻሜውን ያገኛል፤ ተጨማሪ ኃይልም ያመነጫል መባሉ አንዱ ነው፣ ወዲያ ደግሞ ሀገራችን ከራስ ገዟ ሱማሊላንድ ጋር የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟ እና እሱ እውን ከሆነ “አበቃልኝ በቃ” በሚል ፍራት አቅል አሳቷት ነው።

ኢትዮጵያን ከልማቷ ለማናጠብ በራሷ ወጥታ ወርዳ ያቃታትን ሴራ በሌሎች ለመጠቀም እየሞከረች ነው። ከአስራ አምስት ቀናት በፊት ወደ ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ የደረሱት የግብጽ ሁለት የጦር አውሮፕላኖች መሣሪያዎችን የጫኑ ስለመሆናቸው ተሰምቷል። ‘ጠብ ያለሽ በዳቦ…’ እንዲሉ ይህ አካሔዷ እርሷን ጨምሮ ለማንም ቢሆን የሚያዋጣ አይደለም።

የ“ጠብ ያለሽ በዳቦ” አካሔዷን ልታቆም ይገባል። እውነት ለመናገር ግብጽ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን መሆናችንን የዘነጋች ይመስላል። ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን ከወኔ እና ቆፍጣና ልብ ጋር ሲነጻጸር ምንም እንደሆነ የእኛን ያለፈ ታሪክ ማገላበጡ ብቻ በቂ ይመስለኛል። ያውም የአንጸባራቂ ታሪክ ባለቤት ስለመሆናችን መረሳት የለበትም።

ቀጣናው በአግባቡ ሲጠበቅ የኖረው በኢትዮጵያ ቆፍጣናነት እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። አሁንም ቢሆን በቀጣናው ለመፍጠር የተሞከረው ውጥረት የሚረግበው በእኛው በኢትዮጵያውያን ትጋት ነው። እኛ ለበርካታ ዓመታት የሶማሊያውያንን ችግር ስንፈታ፤ ሠላማቸውን ስናስጠበቅ የኖርን ነን።

ቁልፍ አጋራቸው መሆናችን ሊረሳ አይገባም። ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ሆድና ጀርባ ለመሆን የሚዳዳት ከሆነ ደግሞ መከራን በገዛ እጇ በራሷ ላይ እንደጋበዘች ይቆጠራል። ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ደህንነት ወታደሮቿን ስትገብር ቆይታለች። ከፍ ያለ መስዋዕትነትም ከፍላለች፤ አሁንም ቢሆን ሶማሊያ የሚሻላት እውነተኛ ከሆነችው ጎረቤቷ ጋር ህብረት ማድረግ ነው። ካልሆነ ግን “በሞኝ ክንድ የእባብ ጉድጓድ ይለካል” ነውና ነገሩ ምርጫዋን ማስተካከል የእርሷ ፋንታ ነው።

የዓባይ ግድብ፣ ለቀጣናዊ ትስስር ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እንጂ ሰላምን የሚያደፈርስ አይደለም፤ መሆን የለበትምም። ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የሚመጡባትን ጫናዎች መቋቋም የምትሻው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርህን መመሪያዋ በማድረግ ነው።

ወትሮም ቢሆን ኢትዮጵያ ዓባይን በትበብር ላይ ተመስርተን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጠቀምበት እንጂ ለብቻዬን ልያዘው አላለችም። የውሃ ሀብት ክፍል አጠቃቀማችን ፍትሃዊና ምክንያታዊ መሆን ከቻለ ደግሞ ቀጣናውን ጨምሮ ለሌሎች የሚተርፍ ልማትን ማካሔድ ያስችለናል። ከዚህ በተረፈ የግብጽን ጉዳይ በማስታመም ብቻ መዝለቅ ለሌላ ድፍረት እንድትበረታታ የማድረግ ያህል ነውና ቦታዋን እንድታውቅ ማድረጉ ተገቢ ነው እላለሁ።

ወጋሶ

አዲስ ዘመን  መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You