ከተማ አስተዳደሩ የመማር ማስተማር ሥራውን በታቀደው ጊዜ ለመጀመር ዝግጅት አድርጓል

  • ከ140 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በታቀደው ጊዜ ለመጀመር ዝግጅት ማድረጉን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ከ140ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አብዱሽ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ አራት የገጠርና ዘጠኝ የከተማ ወረዳዎች ከፍተኛ ንቅናቄ በማካሄድ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና የ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በታቀደው ጊዜ ለመጀመር በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህም በከተማ በአስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ መካሄድ የተጀመረ መሆኑን ገልጸው፤ የመማር ማስተማር ሥራው መስከረም 07 ቀን 2017ዓ.ም በተቀመጠው ሀገራዊ አቅጣጫ መሠረት እንደሚጀመር አቶ አቡበከር ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት 122ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መቻሉን ያስታወሱት አቶ አቡበከር፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ጨምሮ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከ140ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ አነስተኛ የኢኮኖሚ መሠረት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተለይተው የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ተግባርም የተማሪ ቁጥርና ውጤታማነት እጅጉን እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የምገባ ፕሮግራሙ ከአካባቢው ባለሀብቶች ጋር በመተባበር እየተከናወነ መሆኑን አውስተው፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመንም የከተማ አስተዳደሩ ለምገባ ይመድብ የነበረውን በጀት በማሳደጉ በተለይም በገጠር ትምህርት ቤቶች ፕሮግራሙን አጠናክሮ ለማስቀጠል አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

የመግዛት አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ለመደገፍ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በማዋቀር የደብተር፣ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)ና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ሀብት የማሰባሰብ ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን አመልክተው፤ ትምህርት ቤቶች እንደተከፈቱ ለተማሪዎች የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በከተማ አስተዳደሩ ከሚገኙ 87 የአንደኛ ደረጃና 13 የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኞቹ እድሳት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ የትምህርት ቤቶቹን ጥራት ለማሻሻል ይሠራል፡፡

‹‹ትምህርት ለትውልድ›› በሚል መሪ ቃል እንደ ሀገር የተጀመረውን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ንቅናቄ ተከትሎ መማሪያ ክፍሎችን የማደስ፣ የተማሪዎች መቀመጫና ጥቁር ሰሌዳ የማሟላት ተግባር ሲከናወን ቆይቷል፡፡ ንቅናቄውም ውጤታማ እንደሆነ መገንዘብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ ከቅድመ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል በርካታ ቁጥር ያለው የመማሪያ መጽሐፍት ህትመት በማከናወን ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል፡፡

ተጨማሪ የመማሪያ መጽሐፍት በህትመት ላይ የሚገኝ በመሆኑ በ2017 ዓ.ም ለእያንዳንዱ ተማሪ ለግሉ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ለሁለተኛ ደረጃ የሚያስፈልገው መጽሐፍ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል እየቀረበ ሲሆን በመጀሪያው ዙር አንድ መጽሐፍ ለሶስት ማዳረስ እንደተቻለና ሁለተኛው ዙር በቅርቡ እንደሚደርስ አመላክተዋል፡፡

የድሬዳዋና አካባቢዋ ነዋሪ እድሜው ለትምህርት የደረሰ ህጻን ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገባ በመተባበር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You