የትምህርቱ ዘርፍ ዐበይት ክንውኖች

ያለፈው ዓመት አንድ ራሱን የቻለ፤ ወይም ራሳቸውን የቻሉ ስራዎች የተሰሩበት ዓመት ሲሆን፣ ክንውኖቹም እንደየ ተቋማቱ ይለያያሉ። ″ይለያያል″ ወይም ″ይለያያሉ″ የሚለውን በጠባብ ትርጉሙ ካልወሰድነው በስተቀር እየሰፋ ይሄዳልና ልዩነቱን ከክንውን ብዛት አኳያ እንጂ ከጥራት፣ ብቃት ወዘተ እንዳልሆነ ይታወቅ።

ከለውጡ በኋላ ባፋጣኝ ስርዓቱን ወደ ማሻሻል ተግባር የተገባበት (ወይም የገባ) ተቋም ቢኖር ከትምህርት ሚኒስቴር ቀዳሚ ነው። ስብራቱ፣ ቅጭቱ፣ ውልቃቱ ሁሉ ብሶ የነበረው እዚህ ዘርፍ ውስጥ ስለ ነበረ ይመስላል በወቅቱ ሁሉም አይንና ጆሮውን ጥሎ ሲያይ እና ሲያዳምጥ የነበረው በዚሁ በትምህርትና አካባቢው ላይ ነበርና ተቋሙ ″ሪፎርም″ ተግባር በፍጥነት መግባቱ ተገቢና የሚጠበቅ ተግባር እና ኃላፊነት ነው።

በዚሁ ትምህርት ሚኒስቴር ″ሪፎርም″ በሚለው (የለውጥ አሰራር) አማካኝነት፤ ወይም ″ወደ ሪፎርም ስራዎች ገብቻለሁ″ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ጥቂት ዓመታት (በተለይ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ማለት ይቻላል) የተቆጠሩ ሲሆን፣ በእርግጥም ከማንም በላይ በከፍተኛ ደረጃ በሪፎርም ስራ ውስጥ ራሱን ሙሉ ለሙሉ አስገብቶ የሰራ ተቋም ይጠራ ከተባለ በሙሉ ድምፅ ″ትምህርት ሚኒስቴር″ የማይል ይኖራል ብሎ ማሰብ በማይቻልበት ደረጃ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በትምህርት ላይ ደርሶ የነበረው የከፋ ቅጭት፣ ስብራትና ውልቃት ከባድ ነበርና እንዲህ በቀላሉ ይወገዳል ብሎ ማሰብ ከባድ ስለሚሆን ሪፎርሙ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ላይ በመስማማት ተቋሙ በ2016 ዓ·ም ያከናወናቸውን ዐበይት ተግባራት ቀጥለን እንመልከት።

ከላይ እደጠቀስነው፣ በማእከል የተሰሩትን ስራዎች መነሻ አድርገው በየክልሎችና ከተማ መስተዳድር ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የተሰሩት ስራዎች እንዳሉ ሆነው፣ እንደ አገር ትምህርት ሚኒስቴር የሰራቸውን ስራዎች ብቻ ብንመለከት በርካቶች ሆነው የምናገኛቸው ሲሆን፤ በትምህርት ሴክተሩ ላይ የደረሱ ስብራቶችን ለመጠገን ሁሉንም ካነቃቃው የፈተናው ዘርፍ ርምጃዎች በመጀመር ወደ ሌሎቹ እንዝለቅ።

በፈተናና ምዘና አካባቢ በርካታ የተሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን፣ ዝቅ ብለንና ራሱን አስችለን ከምናየው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ሳንጨምር፣ ሀገር አቀፍ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች የመግቢያ ፈተና (NGAT)፤ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን የመውጫ ፈተና፣ ያሉበትን ሁኔታ ማወቂያ (የአስተሳሰብ) መለኪያ የሆነው ″አፕቲቲዩድ ቴስት″፤ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በራሳቸው በየደረጃው የሚሰጧቸው ፈተናዎች ሁሉ በዚሁ ባሳለፍነው ዓመትም በአግባቡ ተከናውነው አልፈዋል።

ሌላውና ″ግዙፍ″ የተባው የዓመቱ ተግባር ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በራስ-ገዝነት የማደራጀት ጉዳይ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች የላቀ ውጤት እንዲያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተማር ብቁ ምሁራንን እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል፤ በማንኛውም ነገር ራሳቸውን እንዲችሉ እድል ይፈጥርላቸዋል የተባለው ጉዳይ ነው። በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ወደ ስራ መግባቱ በተደጋጋሚ የተገለፀ ጉዳይ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረትም ለራስ-ገዝነት የሚያበቁትን ተግባራት በክፍል ከፋፍሎ እየሰራ የሚገኝና የመጀመሪያውን ዙርም አጠናቅቆ ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችለው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል።

ዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን አወዳድሮ በመቀበል ከአገርም ባለፈ ለዓለም የሚተርፉ ልሂቃንን ለማፍራት ነፃነት እንደሚያስፈልግ በዚሁ፣ ሰሞኑን በሰጠው ይፋዊ መግለጫው ያስረዳ ሲሆን፤ ይህንን ለማድረግ ይህንን ለማሳካት ደግሞ ተቋማዊ ነጻነት፤ አስተዳዳራዊ ነጻነት፤ የፋይናንስ ነጻነት እና አካዳሚክ ነጻነት ማግኘትን የግድ ይል ነበር።

በተወካዮች ምክር ቤት ስለ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ አዋጅ ቁጥር 1294/2015፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 537/2016 ድንጋጌ መሰረት የመጀመሪያው (ሌሎች ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችም ይከተሉታል ተብሎ ይጠበቃል) የመንግሥት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲደራጅ የተወሰነው አአዩ፤ ራስ ገዝ መሆኑ እነዚህን፣ ከላይ የጠቀስናቸውንና ሌሎች በርካታ (መምህራንንም ሆነ ተማሪዎችን መምረጥን ጨምሮ) መብቶችን (እና ግዴታዎችን?) ሁሉ እንዳጎናፀፈው ተነግሯል። በዚሁ መሰረትም በዚህ፣ በያዝነው 2017 ዓ/ም ወደ ተግባር እንደሚገባ በተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ አማካኝነት ባለፈው ሳምንት ይፋ ሆኗል።

ወደ ሌላው አፈፃፀም እንሂድ።

ሰሞኑን ″ፍትሃዊ እና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም!” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው፣ 33ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ የዚሁ ያከናወንነው 2016 አፈፃፀም አካል ሲሆን፤ በጉባኤው ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የመላው ኢትዮጵያውያን እንጂ የተቋቋሙበት መንደር አይደሉም” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ፕ/ር በትምህርት ዘርፍ ላይ ያሉ አመራሮች የትምህርት ሥራን ከፖለቲካ መለየት ያለባቸው መሆኑን፤ ከዚህ በኋላ በምንም ዓይነት ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በአካባቢ የሚመደብበት ምንም አይነት ሁኔታ እንደማይኖር፤ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምደባ በውድድር እና በብቃት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን የሚሰራ መሆኑ፤ ለሁሉም ጉዳዮች መመሪያዎች የተዘጋጁ መሆናቸው መነገሩ የ2017ን አፈፃፀም ከወዲሁ አውቀን እንድንከታተል እድል ሰጪ ስለሆነ እዚህ መጥቀሱ ተገቢ ይሆናል።

ባሳለፍነው 2016 “አዲሱ ስርዓተ ትምህርት አንድ ተማሪ 3 ቋንቋዎችን እንዲናገር የሚያስችል″ ሆኖ መቀረፁን ያስታወቀው ትምህርት ሚኒስቴር ″ከትምህርት ሚኒስቴር ዓበይት የሪፎርም ትኩረቶች አንዱ የስርዓተ ትምህርት ሪፎርም ነው።″ በሚል ቁርጥ ያለ አቋም ″ተማሪዎች በቅድመ አንደኛ ደረጃ በአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ በአንደኛ ደረጃ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛ ከዚያም ከ3ኛ ክፍል በኋላ ሌላ የአጎራባች ክልል ቋንቋ እንደሚማሩ″ የተወሰነበት ዓመት ሆኖ አልፏል። ይህም እንደ አንድ የተቋሙ ከፍተኛ የሪፎርም አካል ሆኖ ተወስዶለታል። ውጤቱን ከ2017 ጀምሮ የምንመለከተው ሆኖ የውሳኔው መሰረት 2016 ሲሆን፤ ″ስርዓተ ትምህርቱ በሀገር በቀል ምሁራን ጥናት ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ″ የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

ባሳለፍነው ዓመት፣ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች የነበሩትን፤ ነገር ግን በማን አለብኙ ስርዓት የተነቀሉትን ነጥቦች ባገናዘበ መልኩ ትምህርትና ትምህርት ነክ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ ስርአተ-ትምህርቱ የግብረገብ እና የተግባር ትምህርቶችን እንዲያካትት ተደርጓል፤ በሥርዓተ ትምህርቱ ችግሮች ዙሪያ ከመምህራን፣ ከወላጆች እና ከተማሪዎች የሚነሱ ሀሳቦችንም ለማካተት አስፈላጊው ሁሉ ተደርጓል፤ ወደ ፊትም ይደረጋል። የመማሪያ መጻሕፍ ስርጭትን በተመለከተም ያሉ የበጀት ችግሮችን በመቋቋም በአማካይ ያለውን ተደራሽነት ለመጨመር (በተለይ ቴክኖሎጂ ተኮር አሰራርን ለማበጀት) የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልፇል። ይህም የ2017ን የስራ አፈፃፀም ከወዲሁ አውቀን አስፈላጊውን ክትትል እንድናደርግ ያግዘናል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከሚወሰዱት ርምጃዎች አንዱ የሆነውን፣ ኩረጃን ለማስቀረት በተወሰደው ″ተማሪዎችን በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት″ የመፈተኑ ርምጃ በ2016ም በመቀጠል ሶስተኛ ዙሩን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ ይህም የፈተና ስርዓት በሰላም መጠናቀቁ በወቅቱ ተገልፇል። ውጤቱስ? ባለፈው ሰኞ እለት እንደ ተገለፀው:-

″የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 701ሺህ 749 ተማሪዎች መካከል 684ሺህ 205 ተማሪዎች ወይም 97.5 በመቶዎቹ ፈተናውን ወስደዋል″ ያሉለት፤ ከትናንት በስቲያ፣ ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ የተደረገውን የተፈታኞች ውጤት በተመለከተም “በጥቅሉ የዘንድሮው ውጤት ካለፉት ሁለት ፈተናዎች የተሻለ ነው”፤ ″አጠቃላይ ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች [36,409] 5.4 በመቶ ናቸው። አዲስ አበባ 10,690 (21.4 በመቶ) ተማሪዎችን በማሳለፍ ከፍተኛውን ስፍራ ይዟል።″ (ትምህርት ሚኒስቴር)

ሌላው ባለፈው ዓመት በትምህርቱ ዘርፍ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ከተለያዩ አገራት፣ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች መከናወናቸው ሲሆን፤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከደቡብ ኮሪያ (ከጠቅላይ ሚኒስትርና ትምህርት ሚኒስትሩ ጋር)፣ ከኳታር መንግስት፣ ከአሜሪካው የረትገር ዩኒቨርሲቲ ወዘተርፈ ጋር የተደረጉት ስምምነቶች፣ የተደረሰባቸው መግባባቶች በትምህርቱ ዘርፍ ደርሶ የነበረው ጉዳት መልሶ ለመጠገን ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሂደታችን ነካ ነካ ነውና አሁን ደግሞ ወደ ስልጠናዎች እንሂድ።

ትምህርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው 2016 ካከናወናቸው በርካታ ተግባራት መካከል እንደ ስልጠና መስጠት ሲሆን፣ ከእነዚህ ስልጠናዎች መካከል ደግሞ በአይነቱም ሆነ ይዘቱ ″ልዩ″ የተባለው ይገኝበታል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ፕ/ር የ2016 ዓ.ም የሁለተኛው ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርትን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ባቀረቡበት እለት ስልጠናው የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን አቅም ማሳደግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልፀው ነበር። በወቅቱ ከስልጠናዎችም ትኩረትን አግኝቶ የነበረው ደግሞ ″ልዩ″ የተባለው ስልጠና ነበር።

በዚሁ መሰረትም ″ለተከታታይ 24 ቀናት ሲሰጥ የቆየው የመምህራንና ትምህርት ቤት አመራሮች ልዩ አቅም ግንባታ ስልጠና″ ተጠናቀቀ። ስልጠናውም ″መምህራን በሚያስተምሩበት የትምህርት አይነት፣ የማስተማር ስነ- ዘዴ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ላይ ብቃታቸውን ለማሻሻል ታሳቢ ተደርጎ ለመምህራን የ120 ሰዓታት፣ ለትምህርት ቤት አመራሮች ለ60 ሰዓታት ተሰጥቷል።″

ከሐምሌ 22/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም የተካሄደው ልዩ የክረምት መርሀ-ግብር ስልጠና በ28 ዩኒቨርሲቲዎች ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ 49ሺህ 505 መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች፣ 2ሺህ 892 አሰልጣኞች፤ እንዲሁም 224 ዋና አሰልጣኞች ተሳትፈውበታል። በስልጠናው መሰረትም 2017 የተሻለ የመማር ማስተማር ውጤት ይመዘገብበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ከእንባ ጠባቂ ተቋም የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሰጠው ስልጠና ይህ ብቻ አይደለም። ከዚህ ከ″ልዩ የክረምት መርሀ-ግብር ስልጠና″ ባሻገር ሌሎች በርካታ ስልጠናዎች በተለያዩ እርከን ለሚገኙ አባላት የተሰጡ ሲሆን፣ በተለይ ለተማሪዎች የተሰጠና እየተሰጠ ያለው የስቴም (STEM) ስልጠና፣ በተለያዩ አገራት የተካሄዱ ስልጠናዎችን፣ የውጪ የትምህርት እድሎችን፣ ሌሎች ውድድሮችን (በቻይና፣ ሁዋዌ የተካሄደውን ጨምሮ) እና እዚህ ያልዘረዘርናቸው በርካታ የስራ ላይና ከስራ ውጪ ስልጠናዎች ተሰጥተው አቅም የማጎልበት ስራዎች መሰራታቸውም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተከታታይ የሚወጡ ሰነዶች ያስረዳሉ።

በወፍ በረር ያደረግነውንና በትምህርቱ ሴክተር በተጠናቀቀው ዓመት የታዩትን የዋና ዋና አፈፃፀሞች ምልክታ በዚሁ እናበቃለን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You