ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለም የስልጣኔ መድረክ የራሳቸውን አሻራ ማኖር ችለዋል። ከአክሱም እስከ ላሊበላ ያሉ ጥንታዊ ቅርሶች የኢትዮጵያውያንን ባለብዙ እውቀትና ማስተዋል የሚያሳዩ ሕያው እውነቶች ናቸው። አለት ፈልፍለው ቤት መሥራት፣ ድንጋይ ቀርፆ ሀውልት ማቆም ከዘመናት በፊት ኢትዮጵያውያን የተካኑት ጥበብ ነው።
ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያን ከሌሎች የዓለማችን ሀገራት ለየት የሚያደርጋት የራሷ የዘመን አቆጣጠር መከተሏ ነው። ለዚህ ጥበብ መነሻ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ተቋማት አሉ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አበርክቶ የላቀ ነው። ይህ የዘመን አቆጣጠር ስርዓትም ለዘመናት በጽሁፍ ተከትቦ ከትውልድ ትውልድ አየተሸጋጋረ ዛሬ ለይ ደርሷል።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አንድ ዓመት በውስጡ አስራ ሶስት ወራትን ሲይዝ በአራት ወቅቶች የተከፋፈለ ነው። እነዚህም ወቅቶች አራቱ ክፍላተ ዘመናት በመባል ሲታወቁ ዘመነ መፀው፣ ዘመነ ሐጋይ፣ ዘመነ ጸደይ፣ ዘመነ ክረምት ይባላሉ።
የዘመን አቆጣጠር ዓመታትን፣ ወራትን፣ ሳምንታትን፣ ዕለታትን፣ ደቂቃን እና ድቁቅ ሰዓታትን በየሥፍራቸው (በየመጠናቸው) የሚገልጽ፤ የሚተነትን፤ የሚለካ የቤተ ክርስቲያን የቁጥር ትምህርት ነው። እነዚህ ዅሉ ተመርምረው፣ ተመዝነው፣ ተቆጥረው ሲያበቁ ምድብና ቀመር ተሰጥቷቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ የሚያሳውቅ የዘመን አቆጣጠር – ‹ሐሳበ ዘመን› ይባላል።
ዓመታት፣ ወራት፣ ሳምንታት፣ ዕለታትና ሰዓታት የሚለኩት (የሚሠፈሩት፣ የሚቆጠሩት) በሰባቱ መሥፈሪያና በሰባቱ አዕዋዳት ነው። ሰባቱ መሥፈርታት የሚባሉትም፡- ሳድሲት፣ ኃምሲት፣ ራብዒት፣ ሣልሲት፣ ካልዒት፣ ኬክሮስ እና ዕለት ሲኾኑ ሰባቱ አዕዋዳት ደግሞ፡- ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ ቀመር ናቸው።
የኢትዮጵያ እምነታዊ ባህል የሚወረሰው በሦስት ዐይነት ጠባይ ነው። አንዱ ሕገ ልቡና ይባላል። ከመጽሐፍ በፊት የነበረ ነው። ከአበውቃል በቃል የተወረሰ ነው። ሁለተኛው በሕገ ኦሪት ከኦሪት የተቀዳ ነው። ሦስተኛው በሕገ ወንጌል ከወንጌል የተማርነው ነው። በዚህ ዐይነት ከወረስናቸው በዓላት ማለት በሦስቱም ጠባያት ከወረስናቸው በዓላት የየራሳቸው መልክ ያላቸው አሉ። የዘመን አቆጣጠር ስርአቱም እነዚህን ሁሉ የሚያካታት ሆኖ እናገኘዋለን።
የግብጽ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በሐሳበ ፀሓይ መሠረት (solar) የተቀመረና የዓመቱ እና የወራቶቹ እርዝማኔ እኩል ሲሆን በሁለቱ መሃል ያለው ልዩነት የወራትና ቀናት የቋንቋ ስያሜ እና የዓመቱ አቆጣጠር በስተቀር በዘመን መለወጫ ቀን፥ በወራትና ቀናት አቆጣጠር ተመሳሳይ ናቸው።
ለምሳሌም፦ የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን በኢትዮጵያ መስከረም አንድ ሲሆን በግብጽም ይህንኑ ዕለት ቶውት አንድ (Tout 1) በማለት የዓመቱ የመጀመሪያ ቀናቸው ነው። በአጠቃላይ በሁለቱም የዘመን አቆጣጠር በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት 12 ባለ 30 እና 1 ባለ 5 ቀናት በድምሩ 365 ቀናት ሲኖሩ፤ አራተኛው ዓመት (በተውሳክ) 12 ባለ 30 ቀናትና 1 ባለ 6 ቀናት በድምሩ 366 ቀናት ያሏቸው ስለሆነ ምንም እንኳን በአውሮጳ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ክርስቲያኖች ጋር ቢለያይም በሁለቱ አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ በዓላትን በአንድ ቀን ያከብራሉ።
የግብጽ፥ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አንድ ሲሆን፤ የቀኖችና ወሮች ስያሜና የዘመን ቁጥር በተመለከተ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ አንድ ሲሆን የሁሉም አቆጣጠር ከጌታ ልደት ጀምሮ አንድ ብሎ በመጀመር ዘመኑንም ዓመተ ምሕረት ይሉት የነበረውን ግብጻውያኑ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ በመሆኑ በ284 ዓ.ም.) ጀምረው የሮም ንጉሥ ስም ዓመተ ዲዮቅልጥያኖስ (Anno Diocletian) ብለው እንዲቀይሩ በመገደዳቸው ዘመኑ በስሙ ሲጠራ ነበር።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ መንግስት የግሪጎርያውያንን የዘመን አቆጣጠር ሲከተል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ከኢትዮጵያ ሲኖዶስ ከተለየች በኋላ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠርን መጠቀሙን የቀጠለች ቢሆንም ስያሜውን ግን የግእዝ አቆጣጠር ብላ ሰይማዋለች።
የጁሊያን፥ የባይዛንታይን (Byzantine calendar) እና የግሪጎሪያን አቆጠጠር ዓመት በቀናት ርዝማኔ ማለትም በመደበኞቹ ሦስት ዓመታት 365 ቀናት አራተኛው ዓመት (በተውሳክ) 366 ቀናት ያሉት በመሆኑ ከእኛና ከግብፅ ጋር እኩል ሲሆን፤ አንድ ዓመት 7 ባለ 31 ቀናት፥ 4 ባለ 30 ቀናትና 1 ባለ 28 ቀናት፥ በተውሳክ ባለ 29 ቀናት 12 ወራት አሉት።
የባይዛንታይን ዘመን አቆጣጠር (Byzantine calendar) የጁሊያን ዘመን አቆጣጠርን መሠረት ያደረገ ሲሆን ልዩነቱ የጁሊያን ኦገስት 31 የዓመቱ መጨረሻ ሲሆን በማግስቱ ሴፕቴምበር 1 የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን ነው።
በሌላም በኩል የጁሊያን ከ525 ጀምሮ የጌታ ዓመት (AD) ሲሉ ባይዛንታይን ደግሞ ዓመተ ዓለም Anno Mundi (in the year of the world) በማለት ይጠሩታል ለምሳሌ በጁሊያን ኦገስት 31 ቀን 2023 AD በባይዛንታይን ኦገስት 31ቀን 7531 AM ሲሆን በማግስቱ በጁሊያን ሴፕቴምበር 1 ቀን 2024 AD ሲባል በባይዛንታይን ደግሞ ሴፕቴምበር 1 ቀን 7532 AM (በኢትዮጵያ (2015) ዓ.ም ወይም (7513) ዓመተ ዓለም) በማለት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በመጠቀም ላይ ሲሆኑ ከመንግሥታዊ አገልግሎት ከራሺያ (የቀድሞው ሶቪየት ሕብረት) በ1917፥ ከግሪክ በ1926 ቦታውን ለግሪጎርያን አቆጣጠር ለቋል።
የሮማውያን ዘመን አቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ እየተስተካከለ መጥቶ ከጌታ ልደት 46 ዓመት በፊት (708 AUC) በጁሊየስ ቄሳር ከሐሳበ ጨረቃ ወደ ሐሳበ ፀሐይ ሲቀየር እንደገና ከጌታ ልደት 8 ዓመት በፊት (746 AUC) አንዲት ቀንን ከሁለተኛው ወራቸው ቀንሰው ስምንተኛው ወራቸው ላይ ጨምረው ዘመኑንም AUC (Anno Urbis Conditae) በማለት የሮም ከተማን ከመሠረቱበት ከጌታ ልደት በፊት 753 ጀምሮ ከጌታ ልደት በኋላ እስከ 284 ዓ.ም.) ድረስ በዚህ ስያሜ ሲጠሩበት ኖረዋል። ከ284 ዓ.ም.) ጀምረው ዘመኑን AUC ማለትን በመተው ዓመቱንም እንደ አዲስ ከታች ጀምረው አንድ ብለው በመቁጠርና ዘመኑንም ዓመተ ዲዮቅልጥያኖስ (Anno Diocletian) በማለት ተኩት።
በመቀጠልም በ525 በአሁኑ ጊዜ አውሮፓውያን የሚጠቀሙበትን AD (Anno Domini) የጌታ ዓመት የተሰኘውን አቆጣጠር ዲዮኒሲዩስ ኤክሲጉስ የተሰኘ የሮማን ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ (Dionysius Exiguus) ሐሳብ አመጣ፤ በዚሁም ሐሳብ መሠረት ከ247 Anno Diocletian ቀጥሎ ያለውን ዘመን 532 (Anno Domini) የጌታ ዓመት በማለት በነበረው ዘመን ላይ ሰባት ዓመት በመጨመራቸው በእኛና በአውሮፓውያን ዘመን መሃከል በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ላይ የሰባት ዓመት ልዩነት አመጣ።
የታሪክ ተመራማሪዎችም የሮማው መነኩሴ ዲዮኒሲዩስ (Dionysius Exiguus) ካሰላው ሰባት ዓመት በፊት (7BC) ኢየሱስ መወለዱንና ሄሮድስ የሞተውና አርኬላዎስ የነገሠው ከዚሁ ስሌት አራት ዓመት በፊት (4BC) መሆኑን አረጋግጠዋል። (World History- A chronological Dictionary of Dates; by Rodney Castleden London 1994 PARRAGON Book Service Ltd) ከዚህና ከመሳሰሉት የታሪክና የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች አንጻር የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ሰባት ዓመት ከድርጊት የቀደመ መሆኑን ራሳቸው አውሮፓውያን አምነዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ባሕረ ሐሳብ በሚለው መጽሀፋቸው እንዳስቀመጡት የዘመን አቆጣጠር መለያየትን መነሻ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ «ክብ የሆነ ነገር ሲከብ ከየትኛውም ቦታ መጀመር ይቻላል፤ የዘመን አቆጣጠር /ዓውደ ዓመትም/ ይኸው ነው። ዋናው ነገር አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው፤ የዘመን አቆጣጠሮቹም ልዩነት መንስኤው ይኸው ነው» ይላሉ።
ጌታቸው ኃይሌ፣ ገጽ.65/ ለምሳሌነትም ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን/ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደ ነበር ይጠቅሳሉ። የነበዩ መሐመድና ተከታዮች ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው።
የአይሁድን አቆጣጠር ትተን ከላይ ያየናቸው ሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች /የምዕራባውያኑ የጁልየስ ጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠርና የኢትዮጵያና የግብጽ አቆጣጠር/ ሁለቱም ዘመንን የሚቆጥሩት የኢየሱስ ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው። ይሁን እንጂ እኛ ዛሬ 2002 ዓ.ም ነው ስንል እነርሱ ደግሞ 2009 ዓ.ም ነው ይላሉ።
በዓለም ላይ የራሳቸው ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ካሏቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት። የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ብዙዎች ይናገራሉ፤ የዘመን ቀመሩን የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ትውልዱ ከልጅነት ጀምሮ እየተማሩት እንዲያድጉ ሊደረግ እንደሚገባ ይታመናል።
የዘመን አቆጣጠሩን ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅና እንዲገለገሉበት ማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያ የራሷን ባህል፣ ትውፊት፣ ሥርዓት እና ማንነት መጠበቅ ስትችል ነው። አንዲት ሀገር ከራሷ የሚተርፈውን ማንኛውም ነገር ለሌሎች ሀገራት ማሳወቅ የምትችለው ከፍ ብላ መታየት ስትጀምር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በመተጋገዝ የዘመን ቀመሩን ማሳወቅ ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ባለመካተቱ ትውልዱ ከልጅነት ጀምሮ እየተማረ እንዳያድግ፣ ምሁራን ለሌሎች ሀገራት እንዳያሳውቁ እና ኢትዮጵያውያን የሌላ ሀገር ዘመን አቆጣጠር እንዲከተሉ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ብዙዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ቀመር ከጁሊያንም ሆነ ከጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በስሌትና በቀመር የተለየ ስለመሆኑ ይገለጻል። የኢትዮጵያ ዘመን መቆጠር የጀመረው ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን፤ መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ እና ጥንተ ፍጥረት መነሻ ያደረገም ነው።
የጁሊያን ብሎም የጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመሮች መነሻቸው ዕምነትን ሳይሆን ታሪክን ታሳቢ ያደረገ ነው። የኢትዮጵያውያን ከሌሎች በተለየ አዲስ ዓመታቸውን በወርሃ መስከረም የሚጀምር ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የግሪጎሪያን የዘመን ቀመር ከሚጠቀሙ ሀገራት ጋር ከመስከረም እስከ ጥር ወራት በሰባት፤ እንዲሁም ከየካቲት እስከ ነሐሴ በስምንት ዓመት እንደሚለያይ ያብራራሉ ይለያየል።
ኢትዮጵያ የ13 ወር ባለቤት መሆኗ ልዩ ያደርጋታል። ከመስከረም እስከ ነሐሴ ያሉ ወራቶች በ30 ቀናት የተከፈሉና ኢትዮጵያዊ ስምና ስያሜ ያላቸው ናቸው። ጳጉሜን ወር ግን በየዓመቱ አምስት ቀናትን ስትይዝ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስድስት ቀን እና በየ700 ዓመቱ ሰባት ቀን እንደምትሆን አስረድተው፤ የዘመን አቆጣጠሩን ጠብቆ ለማስቀጠል፣ ትውልዱን ለማሳወቅ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች ሀገራት እንዲገለገሉበት ለማድረግ በሙያው የሚያገለግሉ በርካታ መምህራንን ማፍራት ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ።
እኛም አዲሱን ዓመት መነሻ በማድረግ በዚህ ለሀገርና ሕዝባቸው የላቀ አበርክቶ ማኖር የቻሉ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት በሚመሰገኑበት የባለውለታዎቻችን አምድ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር መነሻ በማውሳት ይህ ጥበብ እስከዛሬ ተጠብቆ እንዲኖር ያደረጉ አካለትን አመሰገንን. ሰላም!
ጽሁፉን ለማዘጋጀት በመረጃ ምንጭነት የተለያያ ማህበራዊ ድረ ገጾችን ተጠቅመናል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም