ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ስኬታማነት

የለውጡ መንግሥት ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ ያስችላሉ ያላቸውን ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም ኢኮኖሚው ወደ ተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር አዲስ ተስፋ የሰጡ የፖሊሲና የሕግጋት ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ሕጋዊ ማዕቀፎቹን መሰረት በማድረግም ተግባራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል።

መፍትሄዎቹን በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ አሰራር ለመተግበርም ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም የሚተገበረው የ10 ዓመት ብሔራዊ የልማት እቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ዕቅዱ የሀገሪቱን ርዕይ፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲን፣ ሀገራዊና የሴክተር ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን፣ የባለፉትን አስር ዓመታት ዕቅድ አፈጻጸም፣ ሀገሪቱ የተስማማችባቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉዳዮችን እና ዓለም አቀፍና ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን እንደ ዋና መነሻ በመውሰድ የተዘጋጀ ነው። የልማት ዕቅዱ ዓላማ የታለመውን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ሀገራዊ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ለማሳካት ጉልህ ሚና መጫወት ነው።

በ2011 የበጀት ዓመት ወደ ትገበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ብዙ የፖሊሲ ሀሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር። ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት ዐቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች መገኘታቸውን መንግሥት ገልጿል። በቅርቡ የጸደቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ግብዓት እንደሚሆን ታምኖበታል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ትግበራ መግባቷ ይታወሳል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ በአራት ምሦሦዎች ላይ የተገነባ ነው። እነዚህም ምሦሦዎች የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማከሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማእቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን ዐቅም ማሳደግ ናቸው።

በመንግሥት ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ማብራሪያ እንደሚያሳየው፣ የፕሮግራሙ ዋና ዋና ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፤ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፤ የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ ዐቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፤ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።

ማሻሻያው ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ ለሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት እንዲሆን ታቅዷል። ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ባለ ነጠላ አሀዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። ከዚህ በተጨማሪም የማሻሻያው ትግበራ የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባትን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት እንደሚያስችል ተገልጿል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋና ዋና የፖሊሲ እርምጃዎች በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፣ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፣ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፣ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደር ማሻሻያ ናቸው። የማሻሻያ መርሃ ግብሩ በእነዚህ የፖሊሲ እርምጃዎች አማካኝነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ታምኖበታል።

ለአብነት ያህልም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ ተደርጓል። ይህ አዲስ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት፣ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አንዱ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደሆነ መንግሥት ገልጿል። አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ስርዓት የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና ክምችትን ሊጨምሩ የሚችሉ ልዩ ልዩ አሰራሮችን አስተዋውቋል። ለውጭ ኢንቨስተሮች ማነቆ ሆኖ የቆየውን አሠራር ያስወግዳል። በዚህም የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ፣ የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት ከአጎራባችና ከአቻ ሀገራት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በሌላ በኩል ይህ ማሻሻያ የገንዘብ ፖሊሲ ማእቀፉን በማዘመን ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ንረት እንዲኖር ያስችላል። የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን እንዲቀንሱ ያደርጋል። የመንግሥት ገቢን ማሳደግ፤ የመንግሥት ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የመንግሥት ብድር አስተዳደር ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ እንዲኖር ያስችላል። እነዚህ እርምጃዎች የበጀት አስተዳደር ውጤታማነትን እና የመንግሥት ዕዳ ተጋላጭነትን በማሻሻል የልማት ፋይናንስ አማራጮች እንዲበራከቱ ያደርጋሉ። ከዚህ በተጨማሪም የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በተለይም ከዓለም ባንክ፣ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ባንኮች እና ከሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል።

በዓለም የገንዘብ ድርጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ መሠረት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አማካኝነት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በስምንት በመቶ ያህል ያድጋል፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ የተጠጋ ይሆናል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ ይደርሳል፣ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ይላል፤ የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ያድጋል፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ይላል፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ (የ3.3 ወራት የገቢ ሸቀጦችን ወጪ ለመሸፈን የሚበቃ) ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ማሻሻያውን በተመለከተ ‹‹በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የግሉ ዘርፍ በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማራ በር የሚከፍት ነው። የምንዛሬ ገበያው እንዲስተካከል እያደረገ እንዲሁም ብዙ ሕገ ወጥ ስራዎችን ወደ ሕጋዊነት እያመጣ ነው። በዶላርና በብር መካከል ያለውን ያልተገባ ዝምድና ለማረቅ የሚያግዝ ነው። ኤክስፖርት በማድረግ፣ ገቢን በማስገባትና በማስፋት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) በሕጋዊ መንገድ እንዲመጣ በማድረግ ኢኮኖሚያችንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ ይጠበቃል። በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየ ነው›› በማለት ተናግረው ነበር።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ትልቅ እርምጃ ነው። ‹‹ይህ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ትርጉም ባለው መልኩ ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሻግረው የታመነበት እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መከናወን ያለባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?›› የሚለው ጥያቄ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በብቃት እና በውጤታማነት ለመተግበር መንግሥት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ገልጿል። እነዚህ አቅጣጫዎች በላቀ አፈፃፀም እንዲተገበሩ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ከእያንዳንዱ ዜጋ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የግልና የመንግሥት ተቋማት ብርቱ ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ዓይነቱ መርሃ ግብር በሙያና በሀገር ፍቅር የተቃኘ ከፍተኛ የማስፈፀም አቅም ይጠይቃል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጠንካራ የመፈፀም ብቃት ያላቸው ተቋማትን ይፈልጋል። እነዚህ ተቋማት ከሙስና የፀዱና በብቁ ሰው ኃይል የተደራጁ ሆነው እንዲሰሩ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪም የኅብረተሰቡንና የባለሙያዎችን ሃሳብ ማዳመጥ እንዲሁም ማሻሻያው ስኬታማ እንዳይሆን ችግር በሚፈጥሩ ተቋማትና ግለሰቦች (ለምሳሌ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችና ከነጋዴዎች ጋር የሚመሳጠሩ አስፈፃሚዎች) ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል፣ መንግሥት የነቃ ቁጥጥር በማድረግ ርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።

መገናኛ ብዙኃን ከቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማት ጋር በመተባበር ስለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መረጃና ማብራሪያዎችን የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማትም ለዚህ ትብብር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ ማሻሻያው ምን ዓይነት ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ማሳወቅ፣ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮና ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ማሳየት፣ ማሻሻያውን ለመተግበር ቀደም ሲል ዝግጅቶች ሲደረጉ እንደቆዩ ማስገንዘብ፣ ኅብረተሰቡ ማሻሻያው ውጤታማ እንዲሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ (ለአሉባልታዎች ጆሮ እንዳይሰጥ፣ ሕገ ወጥ ግለሰቦችንና ተቋማትን እንዲያጋልጥ…) ግንዛቤ መፍጠር ይኖርባቸዋል።

የሀገር ውስጥ ተቋማትን ማጠናከር እና ባለድርሻ አካላትን በፖሊሲ ማሻሻያ አተገባበሩ ላይ ማሳተፍ አስፈላጊ ተግባር ነው። ሀገሪቱ ከፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጋር ተያይዘው የሚመጡት አዳዲስ የልማት ፋይናንስ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በአግባቡ እንድትጠቀም ማድረግ ይገባል። ለግሉ ዘርፍ የሚፈጠሩ መጠነ ሰፊ ዕድሎች እንዳይባክኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶች ጋር ተጣጥመው እንዲከወኑ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበሩ መንግሥት ጥብቅ የክትትልና የድጋፍ ማዕቀፎችን መዘርጋት ይኖርበታል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ በመተግበር እንዲሁም ተጽዕኗቸውን በመከታተልና በመገምገም ረገድ ወሳኝ ሚና ላላቸው ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማት (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር) ድጋፍ በማድረግ ተቋማዊ ዐቅምን ማጠናከርም አስፈላጊ ነው።

ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር ግልጽነት ያለው ግንኙነት መፍጠር እና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ከፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን (ለምሳሌ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች እና ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች ድጎማ ማድረግ፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መደጎም…) ያስፈልጋል። መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ቀጣይነት ያለው ግምገማ ማድረግ አለበት። ለዚህም በወቅታዊ መረጃ ላይ በመመሥረት በፕሮግራሙ ላይ ወቅታዊ፣ አስፈላጊ እና ተገማች የፖሊሲ ማስተካከያዎችን ሊያደርግ ይገባል።

ሰላምን ማስፈን ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬት ግንባር ቀደም ሚና እንዳለው ከማንም የተሰወረ አይደለም። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንፃራዊ ስኬት እንኳ ሊያስመዘግብ የሚችለው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ አግኝተው ሕዝብና መንግሥት ዋና ትኩረታቸውን ወደ ኢኮኖሚ ሲያዞሩ እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም።

ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You