አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ሰላም የሚረጋገጥበት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን የኃይማኖት አባቶች

አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱን ዓመት ተቀብለናል። በዘመን ቆጠራ አዲስ የሚያሰኘው ማክሰኞ ከረቡዕ ተለይቶ ሳይሆን የሰው ልጅ የሚሠራቸው ሥራዎች ናቸው። በአዲስ ዓመት ዋዜማ እና በእለቱ መካከል ያለው ልዩነት በሰው ልጅ እቅድና እንቅስቀሴ የሚወሰን ነው። የሰው ልጅ እቅድና ተግባር ደግሞ ከራስ በዘለለ ለሌሎችና ለሀገር ሊጠቅም የሚገባ፤ ብሎም ሰላምን ያስቀደመ ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።

በአዲሱ ዓመት ስለራሳችን እቅድ ስናወጣ ሀገራችንና በአካባቢችንም ሰላም እንዲሰፍን በማሰብ ሊሆን ይገባል። ዛሬ ላይ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ሁላችንንም የሚነኩ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። በመሆኑም እቅዳችንም ተግባራችንም ሰላምን ያዘለ ሰላምን የተላበሰ እንዲሆን ይጠበቃል። ሰላም በመደፍረሱ በሰላም ከቦታ ወደቦታ መንቀሳቀስ የሚያዳግትበት ሁኔታ ሲፈጠር ችግሩ ሁሉንም የሚነኳ ሆኗል። እንደ ሰው በማህበር እየኖርን ለብቻ ታስቦ ለብቻ ተሠርቶ የሚሳካ ነገር ባለመኖሩ ለሌሎችም ሰላም ልንጸልይ፤ ልንሠራ ስለ ሰላም ልንመክር ይገባል።

እንደ ሀገር ያለፉት ጥቂት ዓመታት ጥሩ አልነበሩም። በእነዚህ ዓመታት የነበሩ ስህተቶቻችንን ልንደግም አይገባም። ለዚህም አዲሱን ዓመት ስንቀበለው በአዲስ መንፈስ በየሃሳባችን ፤በየእቅዳችን ሁሉ ሰላምን አካተን ሊሆን ይገባል። እልህ በመጋባት ብዙ ጥፋት ደርሶ አይተናል፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እስከማለፍ የደረሱ አጋጣሚዎችን በቅርብ ጊዜያት በሀገራችን አስተናግደናል። አሁን መገንዘብ ያለብን ሁሉንም ነገር ከይቅርታ ውጪ ከሆነ አደጋው ለሁላችንም ነው፡፡ እልህ መጋባት አብሮ ያጠፋናል፡፡የራሳችን ሀሳብ አመለካካት እንዲከበር እንዲደመጥ እንደምንፈልግ ሁሉ የሌሎችንም ሀሳብ ማክበር ማድመጥ ይጠበቅብናል። ከእልህ አመለካከትና ተግባር መላቀቅ አለብን።

በተጨማሪ ለአዲሱ አመት እንደ ግለሰብም ሌሎች እንዲቀየሩ ሌሎች እንዲለወጡ ከማሰብ በፊት ራሳችንን ለመለወጥ ልንዘጋጅ ይገባል። ሌሎች ሰዎች እኛ የምንፈልገውን ላይሆኑ ይችላሉ በቁጥጥራችን ስር ባለመሆናቸውም ልንኮንናቸው አንችልም። እኛ ራሳችንን ግን ማረም ማስተካከል እንችላለን። ከሁሉም በፊት ራሳችንን ለማደስ ራሳችንን ለመቀየር ልንጥር ይገባል። አሁን አሁን በስፋት እንደምናስተውለው ብዙ ነገራችን ትላንት ለይ የቆመ ነው። በርግጥ ትናንትን የተሰሩ ነገሮች ጎጂም ጠቃሚም ቢሆኑ የራሳችን ታሪክ አካል ናቸው። እነዚህም በታሪክነታቸው ቢወጡና ብናውቃቸው ይጠቅሙናል እንጂ አይጎዱንም ። ነገር ግን ትናንትን እያነሳን ለጭቅጭቅ እና ለግጭት መነሻ መነሻ ልናገደርጋቸው አይገባም።

በሌላ በኩል ካለምክንያት ጎራ ለይቶ እርስ በእርስ ከመተቻቸት መውጣትም ይኖርብናል። ዛሬ ዛሬ የተለመደ አካሄድ አለ፡፡ ለምሳሌ ሰላሳና አርባ ኪሎ ሜትር መንገድ ተሠርቶ አንድ ቦታ ጎርፍ ሲገጥም ብዙዎቻችን ይቺን አጉልተን ሁሉም መንገድ እንደጠፋ አድርገን ስንገልጽ ይስተዋላል። ይሄ ለምን ሆነ ብለን ራሳችንን ልንፈትሽ ይገባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከመናናቅ ወጥተን መከባበር መዋደድ አለብን ፡፡የሌላውን ባህል ፤ሃይማኖት፤ እምነት መናቅ ማንቋሸሽ የለብንም። ሰው ራሱን ሲሆን በተለያየ ማንነት ከመፈረጅ ወጥተን ሁላችንም ራሳችንን የምንመረምርበት የምንፈትሽበትና ለሰላምና ለፍቅር ቅድሚያ የምንሰጥበት ሊሆን ይገባል።

በአዲሱ አመት የሁሉም ሰው እቅድና ተግባር ከሀገር ሰላም ጋር የተገናኘ መሆን አለበት። ካለንበት ሁኔታ አንጻር ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል። በእስልምና አስተምህሮ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ሰላም ከሆነ፤ አካሉ ጤነኛ ከሆነ ዓለምን በእጁ አውሏል ይባላል። ለእያንዳንዳችን የአንድ ቀን ሰላም ብዙ ጥቅም አላት፡፡ ትናንት አልፏል፤ ነገ አይታወቅም የዛሬ የአንዷ ቀን ሰላም ግን በለሰው ልጅ ዘንድ ትልቅ ቦታ አላት። ስለዚህም ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ በተለያዩ ሃላፊነት ቦታ ለይ ያሉ ግለሰቦችም እለት በእለት ስለ ሰላም ሊያስተምሩ የተግባር መምህርም ሊሆኑ ይገባል።

የውስጥ ሰላማችንን ከማስጠበቅ ባለፈ እንደ ሀገር ያንዣበበብንን ሰላም ለመመከትም መዘጋጀት አለብን። የውስጣችን ሰላም አስጠብቀን አንድነትና ህብረታችንን ማጠናከር ከቻልን ከውጪ የሚመጡ ጠላቶች የትም ሊደርሱ ምንምም ሊያመጡ አይችሉም። ካለፈው ታሪካችን እንደምናየው ብዙ ጊዜ የውጪ ጠላት ለእኛ አስቸጋሪ ሆኖብን አያውቅም። በጦርነትና በእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ያለፉ ሀገራት የደረሰባቸውን ችግር አይተናል። እንኳን ከጎረቤት ሀገራት ቀርቶ ከሶሪያ በግጭት የተፈናቀሉ ሀገራችን ድረስ መጥተው ሲንከራተቱና ለችግር ሲዳረጉ እየተመለከትን ነው። እኛ ከዚህ ብዙ ልንማር ይገባል። እኛ መሸሻ ሀገር ያለን ሕዝቦች አይደለንም ፡፡ ስለዚህ የሀገራችንን ሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ልንጠብቅ ይገባል። በመሆኑም በአዲሱ አመት ማሰብም መሥራትም ያለብን ከችግር ወጥተን ወደ ልማት አንዴት እንደምንሸጋገር ነው።

ሌላው የአዲሱ ዓመት ዓላማችን ልናደርገው የሚገባው የመረዳዳት ጉዳይ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በተፈጥሮና ሰው ሠራሸ አደጋዎች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል። ለእነዚህ መድረስ ከሁላችን ይጠበቃል። ይህ አብሮነታችንን መተሳሰባችንን የሚያጠናክር ነው። በቅርቡ በጎፋ ለደረሰው ችግር መጅሊሱ ርዳታ ይዞ በሄደበት ወቅት ይህንን በግልጽ አይተናል። የችግሩ ሰለባዎች ከተደረገላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ይልቅ የእናንተ መምጣት ወገን ደጋፊ አለሁ ባይ እንዳለን እንዲሰማን አድርጎናል ብለውናል። አሁን ባለው ሁኔታ የኑሮ ውድነት ሕዝቡን እያማረረው እንደሆነ ይታወቃል።’ በዚህ ረገድም ከንግዱ ማህበረሰብ ብዙ ይጠበቃል። ነጋዴ ለሕዝብ የቆመ ሊሆን ይገባል። መንግሥትም በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉና ለችግር የተዳረጉትን በየጊዜው ሊያስባቸው ይገባል።

ሌላው የዓመቱ ጉዳያችን መንግሥት የጀመራቸው የባህር በር ጉዳይና የዓባይ ግድብ ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳይ ግብጽና ሌሎች ሀገራትም ጣታቸውን መቀሰር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እኛም ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ገንብታ አጠናቃ ለልማት አስክታውልና ለህልውና መሠረት የሆነውን የባህር በር ተጠቃሚነት አስክታደርግ ድረስ ከመንግሥት ጎን ልንቆም ይገባል።

እያንዳንዱ ሰው ለአመቱ የሚያዘጋጀው እቅድ ሰላምን ያካተተ መሆን አለበት። ከቤተሰብ ጀምሮ እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት ልንፈትሽ ይገባል። ከቤተሰብ የሚጀምር ሰላም ለአካባቢም ለሀገርም የሚተርፍ ይሆናል። የአመቱ እቅዳችን የእኛን ዓላማ የእኛን ሃሳብ ብቻ የተሸከመ መሆን የለበትም። እንደ ሀገር ስለሰላም ማሰብ ብቻ ሳይሆን የሰላም አርአያ መሆንም ይጠበቅብናል። ያሰብነው ያለምነው ሊሳካና ከግብ ሊደርስ የሚችለው እኛ ብቻ ሳንሆን በአካባቢያችን ያሉትና መላው ሀገራችንም ሰላም ሲሆን ነው።

ሰላም ባለመኖሩ ብዙ ነገሮች አጥተናል። ዛሬ ለይ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም ሰላም በምንፈልገው መጠን ባለመሆኑ ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውና። ይህንን ጉዳት ለማስቀረትና ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ባጠቃለይ ለሀገርና ለሕዝብ ስንል የሰላም መሣሪያ ለመሆን፤ ከእኔ ምን ይጠበቃል ብለን ልናስብም ልንሠራም ይገባል። በካቶሊክ እምነት የሰላም ጸሎት የሚባል አለ። በእሱም ጥል ባለበት ፍቅር ፤ በደል ባለበት ይቅርታ ፤ ክርክር ባለበት ስምምነት፤ ጥርጣሬ ባለበት እምነት፤ ስህተት ባለበት እውነት፤ ተስፋ መቁረጥ ባለበት መጽናናት፤ ኀዘን ባለበት ደስታ ፤ ጨለማ ባለበት ብርሃን እንድናደርግ አብቃን እንላለን። በዚህ መሠረት ለይቅርታ፤ ለፍቅር ፤ ለመስማማት የምንተጋ ልንሆን ይገባል።

የተሰጠን ሶስት መቶ ስላሳ አምስት ቀን ፈጣሪ የሚደሰትበት ፤ ሁላችን የምንባረክበት ሊሆን ይገባል። አዲስ ዓመት አዲስ ስጦታ በመሆኑ ስላለፈው ዓመት የምናመሰግንበት ራሳችንን ገምግመን የምናስተካክለውን አስተካክለን አዲስ እቅድ የምንናስቀምጥበትና የምንተገብርበትም መሆን አለበት። ይህም ሆኖ አዲስ ዓመትን አዲስ የሚያሰኘው በሰዎች ዘንድ የሚኖረው ሰላም፤ ፍቅርና ደስታ ነው። ሰው መሆን መልካም መሆን ነው። ሌሎች ሰዎችን በመውደድ፤ ይቅርታ በመስጠት አዲስ ዓመትን ለመቀበል መዘጋጀት ይጠበቃል። አዲስ ዓመት የተሰጠንም ልንጠቀምብትም የሚገባው ለራሳችን ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ከሚለው ተሻግረን ለቤተሰባችን በአካባቢያችን ላሉና ለሀገራችንም ጥሩ የምንሆንበት ደግ ደጉን የምንሠራበት ሊሆን ይገባል።

ሌሎች ሰዎችንም ስንቀበል ከነማንነታቸው፤ ከነባህላቸው፤ ከነሃይማኖታቸው በክብር ሊሆን ይገባል። በዚህ ሂደት የሃይማኖት አባቶች ሚና ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ሁሉም ሳይታክቱ ስለፍቅር መስበክ አለባቸው። ዛሬ በአንዳንድ ቦታዎች የምናያቸው ጸብና ግጭቶች ትናንት ተዘርተው የነበሩ ናቸው። በተመሳሳይ ዛሬ የምንሰብከው ሰላምና ፍቅር ውጤቱን ፍሬውን የምናገኘው ነገ ነው። ስለዚህ የሃይማኖት አባቶች ከማስተማር ከማሳየት ከመምከር ባለፈ በጸሎት መትጋትና የቃል ብቻ ሳይሆን የተግባርም አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ሰላም ያሳጣን ችግር፤ አለመግባባትና ግጭት የጋራ ድምር ውጤት ቢሆንም ከግለሰብ የሚጀምር ነው። አሁን ያለንበት የሰላም እጦት የተፈጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርሱ እየተጣላ የጀመረው አይደለም። ችግሩን እዚህ ያደረሱት የተወሰኑ ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው በመነጋገር ሊፈቱት የሚችሉትን መፍታት ባለመቻላቻው የተከሰተ ነው፡፡ በመሆኑም ሰው በቤቱ ፤ በአካባቢው ካለ ሰው ጋር የሚኖረው ጤናማ ግንኙነት ድምር ውጤት ኢትዮጵያን ሰላም ያደርጋታል። ሀገር የመንግሥትና የተወሰኑ ፖለቲከኞች ብቻ አይደለችም። ይልቁንም የህልውና አደጋ ሲገጥም የጥፋቱ ሰለባ የሚሆኑ የሃይማኖት ተቋማትና ተከታዮቻቸውም ናቸው። ጦርነትና ግጭት እንደተፈጥሮ አደጋ ሁሉ ማንነትን አይቶ የሚምር አይደለም። ስለ ሰላም የሚሠሩ ሥራዎች ለሌሎች ተብሎ ሳይሆን ለራስ ነው። በጥላቻ ንግግር መለያየትን መጠፋፋትን መስበክ ሀጢያት ነው። ይህንን በማህበራዊ ሚድያ የሚያስተላልፉትን መገሰጽም የሃይማኖት አባቶች ግዴታ ነው።

ሌላው በዓመቱ የሚጠበቀው ከሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን በመቅረጽ ረገድ የሰላም መልእክተኛ መሆን ነው። ይህን የሚያደርጉት የሃይማኖት ተልእኮ ሰላም መስበክ በመሆኑና በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸው ተሰሚነት ተቀባይነት መጠቀም ስለሚኖርባቸው ነው። ለሰላም የሚሠራ ሥራ በጊዜ መገደብ አይኖርበትም የሁል ጊዜ ሥራችን መሆን አለበት።

ዛሬ ሰላማችን ችግር የተጋረጠበትና ህብረታችንና አንድነታችን የተፈተነበት ወቅት ነው። በአዲሱ ዓመት አብሮነታችንን የሚያጠናክር ረዥም መንገድ የሚያስጉዘን የጋራ ሀገራዊ እቅድም ሊኖረን ይገባል። ለዚህም በሚያቀራርቡን ጉዳዮች ለይ እየመከርን እስከ ዛሬ በምንታወቅበት ኢትዮጵያዊ አንድነት ለይ ማተኮር አለብን። የውስጥ ችግሮቻችንን ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን ልንሠራ ይገባል። አለመስማማትና ግጭት ተፈጥሯዊ በመሆናቸው መቼም ሊከሰቱ የሚችሉና የሚከሰቱም ነገሮች ናቸው። ችግሩ የተፈጠረው እነዚህ ነገሮች እንዴት እናስተናግዳቸው በሚለው ለይ ክፍተት በመኖሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ንግግር ዘመኑ የሚጠይቀው ብቸኛው መንገድ ነው። በመሆኑም በራችንን ዘግተን አሉ በሚባሉ ችግሮቻችንን ለይ ራሳችን ሌሎችን ጣልቃ ሳናስገባ ልንመክር ይገባል። ለዚህ ደግሞ የምክክር ኮሚሽኑ ትልቅ እድል ይዞልን የመጣ ነው።

የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በሁለት ምክንያቶች እድሉን ከሰጠናቸውና አብረናቸው ከሠራን ውጤታማ ልንሆን እንችላለን። አንደኛው የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ትክክለኛው የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ ሁለተኛው ይህንን ነገር እንዲያደርጉ የተቀመጡት ሰዎች ከእድሜም ከልምድም ከሥነ ምግባርም አንጻር ብቁና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚመጥኑ መሆናቸው ነው ። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊ፤ ነፍጥ ያነሱትንም ጨምሮ ቆም ብለው በማሰብ ከመንግሥትም ከሕዝብም ጋር ለመወያየት ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You