“ህብረተሰቡ በአዲሱ ዓመት ይቅር በመባባል መንፈስ ሁለንተናዊ ሰላምን ሊያጸና ይገባል” – ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ

አዲስ አበባ፡- አዲስ ዓመት አዲስ ምዕራፍ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይቅር በመባባል መንፈስ የሀገርን ሁለንተናዊ ሰላም ሊያጸና ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡ በአዲሱ ዓመት ይቅር በመባባል መንፈስ የሀገርን ሁለንተናዊ ሰላም ሊያጸና ይገባል፡፡

ሁሉም ሰው ይህንን ምዕራፍ እንደ አዲስ ጅማሮ በመውሰድ ለመረዳዳት፣ ለመቻቻል እርስ በእርስ ለመግባባት እቅድ መያዝ አለበት ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው፤ በ2017 ዓ.ም በጎ ተግባሩ በማስቀጠልና ከባለፈው ችግር ለመላቀቅ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በአእምሮ መታደስና መለወጥ ከፈጣሪ የተሰጠ ትዕዛዝ በመሆኑ የሰው ልጅ አዲስ ዓመት ሲቀበል በአዲስ ልብስ ከማጌጥና የተለያዩ መብሎች ከማዘጋጀት ባሻገር በሃሳብ መታደስና ለአዲስ እቅድ፣ ሕይወት፣ ተስፋና ትጋት መዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር ተወስኖ ተለክቶና ተቀምሮ የተሰጠው እድሜው በአግባቡ ካልተጠቀመበት በሕይወቱ አንዳች ውድቀት እንዳስመዘገበ የሚቆጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍና ለትውልድ የሚሸጋገር ዐሻራ አኑሮ ማለፍ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ አክለውም ፤ ሰው ያለፈው ዘመኑ በክፋት፣ በምቀኝነት፣ በሰላም እጦች፣ በቂምና በበቀል አሳልፎ ሊሆን ይችላል ነገር ግን አዲስ ዓመትን ሲያከብር በአዲስ ተስፋ በይቅር ባይነት ከባለፈው ውስብስብ ችግር በመሻገር መንፈስ መሆን አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም በእርቅ በሰላም በፍቅር በአንድነት በምህረት በቸርነት በይቃርታ እንዲሁም በመረዳዳትና በመተጋገዝ በኢትዮጵያዊነት እሴት መቀበል አለበትም ብለዋል፡፡

እንደ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ገለጻ፤ ካለፉት ጊዜያት ምን ተማርኩ ምንስ አወቅኩ ምን አሳካው ምንስ ጎደለኝ የሚሉትን ጉዳዮች ማሰናሰልና ከግምት ውስጥ ማስገባትም ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን በሚያረጁና በሚጠፉ ጊዜያቶች የማይደበዝዝ ትልቅ ሥራ ሠርቶ ለማለፍ እድል እንደተሰጠ የሚያስገነዝብ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሰው አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ እድል ተሰጥቶኛል በማለት ለመልካም ሥራ መትጋት አለበት ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ በተሰጠን እድል መጠቀም አለመቻል በራሱ ለቁጭትና ለሃዘን የሚዳርግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አዲስ ዓመት ክረምቱ፣ ጅረቱ፣ ዝናቡና ነጎድጓዱ ሁሉ አልፎ በአበቦች ፍካት እንዲሁም በተስፋ የተሞላ ሰማይ የሚታይበት በመሆኑ ተፈጥሮ በራሱ የሚያስተምርበት ጊዜ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማትም በዚህ ረገድ ለተከታዮቻቸው ተገቢውን ትምህርትና ግሳጼ መስጠት እንዲሁም ምዕመናንም ከየቤተ እምነቱ የሚሰጡ ትምህርቶች በአግባቡ መተግበር አለባቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ቤተ እምነቶች በሰላም ዙሪያ ላይ ያላሳኳቸውና ያልሰሯቸውን ነገሮች መለስ ብለው ለማየት አዲሱ ዓመት እንደ አዲስ የተሰጠ እድል መሆኑን በመገንዘብ በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You