ሚኒስቴሩ ከዲፕሎማሲያዊ ሥራው በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ

አዲስ አበባ፦ ሚኒስቴሩ ከዲፕሎማሲ ሥራው በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ፡፡

ተቋሙ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለሚያሳድጋቸው 33 ህፃናትና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞቹ የበዓል ስጦታና የማዕድ ማጋራት ሥነ-ሥርዓት አከናውኗል።

በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፤ ሚኒስቴሩ ከዲፕሎማሲያዊ ሥራ በተጨማር ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ይህም ዲፕሎማሲያችን በሠብዓዊ ተግባራት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ማመላከቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደሀገር የማህበረሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍታት እየተከናወነ በሚገኘው ሥራ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም የተቀናጀ የክረምት ሠብዓዊና ማህበረሰባዊ አገልግሎት ተነሳሽነትን በመወጠን የ2016 ዓ.ም የበጎ አድራጎት መርሀ-ግብር መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ፤ ተቋም የአቅም ደካሞችን ቤት የማደስና ማዕድ የማጋራት ተግባራትን አከናውኗል። በተጨማሪ በአርባ ምንጭና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ድጋፍ ለሚሹ ከ400 በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍና ለአራት አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ደረጃውን የጠበቀ የቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ሥራ አከናውኗል፡፡

በሁለቱ ከተሞች የተቋሙ ሠራተኞችን በማስተባበር በሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ማስተከል ችሏል ሲሉ አስረድተዋል።

ተቋሙ 33 ሕፃናትን ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡ ህፃናትን ማሳደጉና መደገፉ ለእኛ ትልቅ ፀጋ በመሆኑ እንደመታደል እንወስወደዋለን ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም ተቋሙ ለማህበራዊ ደህንነት ያለውን ቁርጠኝነት ከማጉላት ባሻገር የኢትዮጵያውያንን አንድነትና ርህራሄ ማሳያ የሆነው የአብሮነትና የመደመር መርህ የሚገልጽ ነው ብለዋል።

ድጋፍ የሚደረግላቸው ህፃናት ደህንነት ከሀገራችን ደህንነት ጋር በቀጥታ የተሳሰረና የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የመቅረፅ ዓላማ ያለው መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ መሳተፍ የዜግነት ግዴታ መሆኑን አምባሳደር ታዬ ጠቁመው፤ የተቋሙ ሠራተኞች እያከናወኑ ያሉትን የበጎ አድራጎት ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሀ-ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You