አዲስ አበባ፡- የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደሮች ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በ2017 ዓ.ም የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም ትጋት፣ አንድነትና ትብብራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መጪው ዓመት ተባብረን ራዕያችንን እውን የምናደርግበት፣ እቅዳችንን የምንፈጽምበት ይሁንልን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በአዲሱ ዓመት በተለያዩ መስኮች ስኬትና ሰላምን የምናረጋግጥበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል። ዘመኑን በተሻለ ጥረትና አንድነታችን በማጠናከር የበለጠ ስኬትና ልማት የምናስመዘግብበት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ በሕዝባችን ሰላም ፈላጊነት፤ በአመራራችን ቁርጠኝነት ባሳለፍነው ዓመት የገጠሙንን አይነተ ብዙ እና ተለዋዋጭ ፈተናዎች በጽናትና በትዕግስት አልፈናል ብለዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት ሁላችንም በአንድነትና በሕብረት በመቆም ለመጪው ትውልድ መልካም ነገር በመሥራት ከእዳ ወደ ምንዳ የምንሸጋገርበት የስኬት እና የብልጽግና ዓመት ይሆን ዘንድ ከልብ እመኛለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፤ አዲሱ ዓመት የክልሉ ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ የሚሸጋገርበት እንዲሁም ህብረ ብሄራዊ አንድነት የሚያብብበት የስኬት ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል።
በአዲሱ ዓመት ይበልጥ በማገልገል የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመንባት የተጣለውን ግብ ለማሳካት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፤ በ2017 አዲሱ ዓመት የክልሉን ሠላም በማጽናት የህብረተሰቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በሙሉ አቅም እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም በሀገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ወደፊት የሚያራምዱ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል፡፡
ወደ አዲሱ ዓመት ስንሸጋገር አዲስ ተስፋ ሰንቀን፣ አዳዲስ ዕቅዶችን ይዘን፣ ለአዳዲስ ውጤቶች ለመብቃት ብርታታችንን፣ ፅናታችንን፣ ትጋታችንን ከፍ በማድረግ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ናቸው፡፡
አዲሱ ዓመት አቅሞቻችንንና ፀጋዎቻችንን አስተባብረን በማንቀሳቀስ አዳዲስ ውጤቶችን እውን ለማድረግ በጋራ የምንተጋበት ዓመት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን አጠናክረን፣ ሰላማችንን ጠብቀን፣ ሙሉ አቅማችንና ጊዜያችን ለልማትና ለእድገት የምናውልበት ዓመት ይሁንልን ብለዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ የውጭ ፖለቲካ ጫናዎችን በጥበብና በበሳል ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች አልፈናል፤ አዲሱ ዓመትም ውጥናችንን የምናሳካበት የደስታ ዘመን እንዲሆንልን እመኛለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የአብሮነትና አንድነት ይበልጥ እንዲጎለብት ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ለመጪው ትውልድ ዐሻራ ያሳረፍንበት ግድብ አብዛኛው ሥራ የተጠናቀቀበት እና ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ የጀመሩበት ለሕዝቡ ታላቅ ብስራት የተበሰረበት ዓመት መሆኑንም ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን በማጠናከር አዳዲስ አስተሳሰቦችን እና የልማት ውጥኖችን በመያዝ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
አዲሱ ዓመት የሰላም የብልጽግና የመተሳሰብና በህብረት የምናድግበት እንዲሆንልን እመኛለሁ ያሉት ደግሞ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሐጂ አወል አርባ ናቸው፡፡
ሁሌም ቢሆን ዕድገትና ብልጽግና ሁለንተናዊ መሆን ስለሚገባው በተለያዩ አካባቢዎችና ዘርፎች የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሱ ዓመትን ለነገው ትውልድ ዐሻራ አስቀምጠን ማለፍ የምንችልበት እንዲሆን ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት የአስተዳደሩን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ከመጠበቅ ጎን ለጎን የሕዝብን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነት እና በጥራት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ ዓመት የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ ባስተላለፉት መልእክት፤ የክልሉን ሕዝብ ከተረጂነት ለማላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ የስንዴና ሩዝ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
በክልሉ የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት በማጠናከር በአሸባሪ ሃይሎች ሊፈጸሙ የሚችሉ ትንኮሳዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የፀጥታ መዋቀሩ ከሕዝብ ጋር የሚያደርገው ትብብርም በትኩረት እንደሚሠራ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
አዲሱ ዓመት በአዲስ መነሳሳትና አስተሳሰብ የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሊሆን እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል፡፡
መጪው አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ መቻቻል፣ መከባበርና መፈቃቀድ የሰፈነበት እንዲሆንም ተመኝተዋል።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በዓሉን አቅመ ደካሞችና ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች በመደገፍ ማክበር ጥሪ አቅርበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም