አዲስ አበባ፡- በበዓላት እርድ ወቅት ለቆዳና ሌጦ ጥራት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአምራች ኢንዱስትሪ የቆዳ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቢሻሞ ዋካሶ እንደገለፁት፤ ለሀገራችን ቆዳና ሌጦ ትልቅ ሀብት በመሆኑ በዕርድ ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሀገራዊ ምርት ማሳደግ ይገባል፡፡
በዓልን ምክንያት በሚጸፈም ዕርድ የሚገኙ የቆዳ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኙ ጠቁመው፤ ለሀገር ጥቅም ሲባል ህብረተሰቡ ቆዳና ሌጦን በባለሙያ በጥንቃቄ በማስገፈፍ ወደቆዳ መሰብሰብያ ቦታ የማድረስ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድልና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ በመሆኑ፤ በኮንደሚኒየም አካባቢ የሚደረጉ ዕርዶች ላይ ቆዳን ቆፍሮ መሬት ውስጥ መቅበር የአካባቢ ብክለት የሚያስከትልና የሀብት ብክነት በመሆኑ ከዚህ አይነት ድርጊት መታቀብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢንዱስትሪው ያልተጠቀመውን ከፍተኛ አቅም ለመጠቀም ስትራቴጂ መነደፉን ጠቅሰው፤ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በፋይናንስ ለማሳደግ የአፍሪካ ገበያ ላይ በማተኮር ከጂቡቲ፣ ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን በተለይ የተማሪዎች ጫማ የማምረት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዘርፉ በ2017 ዓ.ም ትልቅ ዕቅድ መቀመጡን አመላክተው፤ የአካባቢ ብክለት ለመከላከል የተፅእኖ መጠናቸው ቀላል የሆኑ ኬሚካሎች በመጠቀም ብክለትን የመከላከል ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ዘርፉ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የቆዳ ምርቶች ሙሉ በሙሉ ማስቀሩቱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የሚሊተሪ እና የተማሪዎች ጫማ በሀገር ውስጥ መመረቱ ትልቅ እምርታ በመሆኑ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ሌዘር ኢንዱስትሪ ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ወሰኑ በበኩላቸው፤ ለቆዳ ጥቅም ያለን አመለካከት ትኩረት ሰጥተን የሀገራችን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጥራቱን የጠበቀ ቆዳ ወደ ተገቢው ቦታ በማድረስ ኢንዱስትሪውን ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም