አዲስ ዘመን ድሮ

ታሪክ ራሱን ሲደግም እንመለከትና እንታዘብ ዘንድ፣ ያኔ ምን ሆነ ዛሬስ ምን እየሆነና እየተደረገ እንደሆነ እንመለከት ዘንድ አዲስ ዘመን የማይተካ ድርሻውን ሲወጣ መመልከት እንግዳ ደራሽ አይ ደለም። ልክ እንደ እስከዛሬው ሁሉ፣ ዛሬም የሚለን አለና (በተለይ የግብፅን በሶማሊያ መገኘት) እንደሚከተለው ይነበባል።

የፖለቲካ ድብብቆሽ ጨዋታ

ኢጣሊያኖች በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ገንዘብ ለሶማሊያ አጠፋን የሚሉት የዚህ ገንዘብ መጥፋት የሚመሰክረው አሁን አይደለም። ለሶማሌ ብልፅግና፣ ለሶማሌ ደህንነት የተባለው ይህ ገንዘብ የሶማሌን ጠባይ፣ የሶማሌን ባህል የሶማሌን እውነተኛና ዘላቂ ጥቅም ለማጥፋት የተሰነዘረው ረቂቅ አመራር፣ ከሀገሩ ላይ ጨርሶ የተወገደ ጊዜ ብቻ ነው።

በእውነተኛው መንገድ ገንዘቡ ተገቢ ቦታውን ይዞ ጠፋ ለማለት የሚቻለው ሶማሌዎች ነፃነታቸውን ተረክበው የአስተዳደራቸው ባለቤት በመሆን የውጭ ፖለቲካቸውንና የውስጥ ፖለቲካቸውን አስማምተው የሚራመዱበትን ትክክለኛ መስመር ሲይዙ ነው እንጂ፣ የመልካም ጉርብትናንና የወዳጅ ፍቅርን አጥፍተው ሰላምን ለሚያደፈርሱበት ሁኔታ፣ ወጣ የተባለው ገንዘብ ለጥፋት የወጣ መሆኑን የህሊና አስተያየት ሊስተው አይችልም።

ጠቅላላውንም አስተያየት ብንወስድ፣ እውነት ለሶማሌ ታስቦ ቢሆን፣ እንደ ከንቱ ህልም በሚቆጠር ሃሳብ ውስጥ ሶማሌዎች ገብተው እንዲዋኙ ባልተደረገም ነበር። ኢትዮጵያ ይህንኑ ሁኔታ አርቆ በማሰብና በመመልከት ቀድሞውንም ሶማሊያ በማንም ሞግዚትነት ስር እንዳትደዳር የተቃወመችው ይኸው አሁን በሶማሌ የሚሠራባት ድርጊት እንዳይደርስባት ነበር።

አሁንም ቢሆን ለሶማሌ ነፃነት የኢትዮጵያን ያህል የሚያስብላት እንደሌለ በጥልቅ ሊገነዘቡት የሚችሉት፣ ሶማሌዎች የራሳቸው ጉዳይ ባለቤት የመሆንን እድል ሲያገኙ ብቻ መሆኑ ጥርጥር የሌለበት ስለሆነ፤ በዚህ የተገለጡት ሃሳቦች ምን ያህል መሠረትነት ያላቸው መሆናቸውን በዚያን ጊዜ የበለጠ ይረጋገጣሉ።

ሶማሌዎች ከኢትዮጵያ እንዲጣሉ በመገፋፋት በሚደረገው የፖለቲካ ድብብቆሽ ጨዋታ ውስጥ በመግባታቸው፣ ከጉዳት በቀር አንዳች ጥቅም እንዳላገኙ ለመረዳት እስካሁን የደረሰባቸው በቂ ትምህርት ሊሆናቸው ስለሚችል፤ ለራሳቸው ሲሉ ሶማሌዎች ወደ ፊት በጣም መጠንቀቅ እንዳለባቸው ይዘነጉታል ብለን አንጠራጠርም።

(አሳምነው ገብረ ወልድ፣ አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 1 ቀን 1951 ዓ•ም)

አዲስ መጽሐፍ

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ለሀገራቸው ልማት፣ ለሕዝባቸው እድገት ሲሉ ያለ እረፍት በሀገር ውስጥም ሆነ፣ በውጭ ሀገር ያለ ማቋረጥ የሚያደርጉት ጉብኝት ከፍ ያለ ጥቅም የሚገኝበት መሆኑ አይዘነጋም።

በዚህም መሠረት ከግንቦት 1 ቀን እስከ ግንቦት 18 ቀን 1951 ዓ•ም ድረስ፣ የጎጃምን፣ እንዲሁም የቤገምድርንና የሰሜንን ጠቅላይ ግዛቶች ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ጊዜ የመጀመሪያውን የዓባይን የሃይድሮ ኤሌክትሪክ መሠረት፣ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ ጎጃምና ቤገምድርን የሚያገናኝ አዲስ ድልድይ መስርተዋል። በነዚህም በ 2 ጠቅላይ ግዛቶች ሕዝቦቻቸው መካከል በሰነበቱባቸው እለታት ውስጥ ግርማዊነታቸው ለሕዝባቸው ያደረጉት ሰፊ ልግስና ሕዝባቸው ለግርማዊነታቸው ያደረገው ልባዊ አቀባበል ለትውልድ እንዲወራረስ 199 ገጽ የሆነ ከዚሁ 42ቱ ልዩ ልዩ ሥዕሎች ያሉበት ፣ የዓባይ ውሃ ልማት መጀመሪያ መሠረት፣ የሚል መጽሐፍ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በመልካም አቀራረብ በንግድ ማተሚያ ቤት ታትሞ ወጥቷል። መጻሕፍት ወዳጆችና ታሪክ አጠናቃሪዎች የሆኑ ሁሉ መጽሐፉን እየገዙ ለመጠቀም እንዲችሉ ያሳስባል።

(አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 21 ቀን 1951 ዓ•ም)

ለወላጆች ምክር

አደጋ በህፃኒቱ ላይ ሊደርስ የቻለበት ምክንያት ወላጆች ለልጆቻቸው ገና በቡቃያነታቸው በሚገባ አስደተዳደግ ሳይመሯቸው በመቅረት ካደጉ በኋላ በዱላ ነርተን ልብ እናስገኝላቸዋለን በማለት ሁኔታ የሚፈፀም መሆኑን ይህ አደጋ ደርሶባቸው የሚመጡትን ህፃናት በምንጠይቅበት ጊዜ አረጋግጠው ያስረዱናል።

የሚገባ አይደለም፤ ዱላ ሲበዛ ያደነዝዛል እንጂ ልብ አይሰጥም። በአንዳንዶቹ አንደበት ሲነገር እንደምንሰማው የዱላ ክፋቱ ለሸክላ እንጂ ለሌላ ሁሉ ልብ ይሰጣል በማለት ሲተርቱ ስለምንሰማ ጠባያቸውን እንዲያርሙ ይህ ሁኔታ ባጋጠመን ጊዜ መክረን ለማለፍ አልቦዘንም ነበር።

አሁን ግን እላይ እንዳተትነው ይህ አደጋ የሚደርስበት ከዚሁ ከአንዱ ክፍል ሲሆን፣ ጥፋተኞቹ ወላጆቹ ይሁኑ ወይንም ህፃኖቹ ለመፍረድ አስቸጋሪ ስለሆነ፤ የህፃኖቹን ፋንታ አልፈን ስለ ጥፋተኛነቱ ወላጆቻቸውን ሳንመለከት አልቀረንምና ህፃንን በዱላ ቀጥቅጬ ልብ እሰጠዋለሁ ማለት የውቅያኖስን ውሃ ቀድቼ እጨርሳለሁ ከማለት ጋር እኩል የሚቆጠር በመሆኑ፤ በመጀመሪያ በቡቃያው አኮታኮትን ማሳመር ስለሚያሻ ለህፃናቶችም በሚገባ ቢታሰብላቸው የተሻለ ነው።

(አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 12 ቀን 1951 ዓ•ም)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ውጤት

የኢትዮጵያ ናሲዎናል ቡድን ከሶቪየት ናሲዎናል ኦሎምፒክ ቡድን ጋር ባደረገው ግጥሚያ 12 ለ 3 ተለያይተዋል። ሁለተኛው ግጥሚያ ማክሰኞ ሀምሌ 7 ቀን ዜኒት ሌኒንግራድ ከሚባል ቡድን ጋር ተጋጥመው 2 ለ 1 ተለያይተዋል። ዜኒት ባለፈው ወር ረንስ የተባለውን 8 የፈረንሳይ ናሲዎናል ተጫዋቾች ያሉበትን ቡድን ባሁኑ አመት ለአውሮፓ ሻምፒዮና ፍፃሜ ተካፋይ የነበረውን 3 ለ0 አሸንፎታል።

የጨዋታው ሀተታ እንደደረሰን በሰፊው እናትታለን።

(ፍቅሩ ኪዳኔ፣ አዲስ ዘመን፣ ሐምሌ 10 ቀን 1951 ዓ•ም)

በወ ወ ክ ማ የሚደረግ ንግግር

ነሐሴ 9 ቀን 1951 ዓ•ም ከምሽቱ 1 ሰአት ጀምሮ አቶ ዮሀንስ ወልደ ገሪማ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝብ ጤና ጥበቃና የሕዝብ አገልግሎት ዲሬክተር ፣የሕዝብ አገልግሎት፣ በሚል አርዕስት በወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር አዳራሽ ንግግር ስለሚያደርጉ ማንኛውም ሰው ንግግሩን ሊያዳምጥ ይችላል።

(አዲስ ዘመን፣ ነሀሴ 8 ቀን 1951 ዓ•ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You