የፓሪስ ፓራሊምፒክ ዛሬ ይጠናቀቃል

አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችን ባለፉት ቀናት ሲያወዳድር የቆየው የፓሪስ 2024 ፓራሊምፒክ ዛሬ ማጠቃለያውን የሚያገኝ ይሆናል። ከመላው ዓለም በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ አካላቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ስፖርተኞች ተወጣጥተው እርስ በእርስ የአሸናፊነት ፉክክር የሚያደርጉበት ይህ መድረክ ከኦሊምፒክ መካሄድ በኋላ የሚጀመር ነው። ዛሬ በሚጠናቀቀው 17ኛው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይም ከ170 ሀገራት የተወጣጡ 4ሺ400 የሚሆኑ ስፖርተኞች በ22 የስፖርት ዓይነቶች የሀገራቸውን ሰንደቅ በማውለብለብ የታላቁን መድረክ ሜዳሊያ ለማጥለቅ ሲፋለሙ ቆይተዋል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሳትፈው አካላዊ ጉዳት በገጠማቸው ጥቂት የቀድሞ ወታደሮች እአአ በ1948 የተጀመረው ይህ ስፖርት ዓይነት እንደጊዜው እያደገና እየተጠናከረ በመሄድ በሮም አዘጋጅነት የተካሄደውን የ1960 ኦሊምፒክ ተከትሎ የፓራሊምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ መደረጉን ታሪክ ያወሳል። በወቅቱ ውድድሩ ላይ የተካፈሉት አትሌቶች 400 ብቻ ሲሆኑ ከ64 ዓመታት በኋላ ቁጥሩ በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡን ለመረዳት ይቻላል። ፈረንሳይ በታሪኳ ኦሊምፒክን ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ያሰናዳች ቢሆንም የፓራሊምፒክ ውድድርን በሀገሯ ስታካሂድ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ዛሬ 12ኛ ቀኑን ያስቆጠረው ፓራሊምፒክ የመክፈቻ መርሀ ግብሩን በደማቋ የፓሪስ ከተማ ትልቁ አደባባይ የተከናወነ ሲሆን፤ በኦሊምፒኩ ላይ ከታየውና በብዙዎች ከተተቸው በተለየ ደማቅ ሊባል የሚችል ነበር። 500 የሚሆኑ ዳንሰኞችን ጨምሮ በርካታ የጥበብ ሰዎች ስራዎቻቸውን ባሳዩበት መድረክ የሆንግ ኮንግ ተወላጅና በፊልም ዓለም እጅግ ተወዳጅ የሆነው አክተር ጃኪ ቻን የፓራሊምፒክ ችቦውን ለኩሷል። የዛሬው የመዝጊያ መርሀ ግብርም ከ77ሺ ሰው በላይ የመያዝ አቅም ባለውና የፓራሊምፒክ የመምና ሜዳ ተግባራት ውድድሮች ሲደረጉ በቆዩበት ግዙፉ የፈረንሳይ ስታዲየም ውስጥ የሚከናወን ይሆናል።

አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን የሜዳሊያ ሰንጠረዡን እየመሩ ያሉበት የዘንድሮው ፓራሊምፒክ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 91 ሀገራት የሜዳሊያ ሽሚያውን ተቀላቅለዋል። 64 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ የቻለችው አዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። እጅግ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ውድድሩ 20 በሚጠጉ ውድድሮች የዓለም ክብረወሰን የተሰበረበት ሊሆን ችሏል። በመድረኩ ከተሻሻሉ ክብረወሰኖች መካከል አንዱ በሴቶች 1ሺ500 ሜትር ርቀት (T11) የተወዳደረችው ኢትዮጵያዊቷ ያየሽ ጌቴ አንዷ ናት። አትሌቷ በራሷ ሀገሯን በድል ባስጠራችበት ውድድር ያስመዘገበችው ክብረወሰን በራሷ ተይዞ የቆየውን ሰዓት ከ4 ሰከንድ በላይ በማሻሻልም ነው።

በርካታ አስገራሚና አስደናቂ ክስተቶች በታዩበት በዚህ ውድድር የስደተኞች ቡድንም ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ ሜዳሊያ ሊያስመዘግብ ችሏል። በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ የትውልድ ሀገራቸውን ጥለው ለስደት የተዳረጉ ስፖርተኞች በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ ተወክለው በታላቁ የስፖርት ውድድር እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ይታወቃል። በፓራሊምፒክ ውድድርም በተመሳሳይ የአካል ጉዳት ያለባቸው ስደተኞች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በታሪክ የመጀመሪያው ሜዳሊያ ፓሪስ ላይ ተገኝቷል። ይኸውም በዛኪያ ኩዳዳዲ የሴቶች 47 ኪሎ ግራም የቴኳንዶ ውድድር የተገኘ የነሀስ ሜዳሊያ ነው። በሴቶች የባድሜንተን ውድድር ደግሞ የ7 ወር ነፍሰጡር የሆነችው ተወዳዳሪ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት አነጋጋሪ ልትሆን ችላለች። እንግሊዛዊቷ የቀስት ተወዳዳሪ ጆዲ ግሪንሃም በግሏ የነሀስ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ በቡድን ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ በፓራሊምፒክ ውድድር የመጀመሪያ ሴት አትሌት ልትሰኝ ችላለች።

ሌላኛው አሜሪካዊ ሮድሪክ ታውንሴንድ ደግሞ በከፍታ ዝላይ በተከታታይ ሶስት የፓራሊምፒክ መድረኮች ላይ በማሸነፍ አድናቆትን ሊያተርፍ ችሏል። ይህ አትሌት የአካል ጉዳት ካላገደው ብቃቱ ባለፈ በተለያዩ ቀለማት ባደመቀው ጸጉሩ እንዲሁም በራፕ የሙዚቃ ስልት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የውድድሩ ድምቀት ለመሆንም ችሏል። የፍቅር ከተማ የምትሰኘው ፓሪስ ላለፉት ሳምንታት ስፖርታዊ ውድድር ላይ ብትሆንም ታዋቂው የኤፍል ማማ እና ውብ ጎዳናዎቿ ግን በርካታ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪ ጥንዶች ወደ ትዳር ለመሸጋገር የ‹‹እንጋባ›› ጥያቄዎችን ሲያስተናግዱም ነበር።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You