– ስድስት የስኳር ፋብሪካዎች በቀጣይ ዓመት ወደግል ይዛወራሉ
አዲስ አበባ፡- በመንግሥት ይዞታ ስር የሚገኙ ተቋማትን ወደግል ለማዞር በሚደረገው ጥረት ኢትዮ ቴሌኮምን ለሁለት በመክፈል 49 በመቶው ወደግል ድርጅት ለማዞርና በተጨማሪ ሁለት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎች እንዲሰማሩ አቅጣጫ መቀመጡን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በስኳር ልማት ዘርፉ ከ13 ፋብሪካዎች ስድስቱን በቀጣይ ዓመት ወደግል ለማዞር የሚያስችል ሥራ እንደሚከናወን ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ትናንትና በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም አንድ ኩባንያ ሆኖ የተወሰነው ድርሻው ወደግል ሲዞር አደረጃጀቱ በአገልግሎት እና በመሰረተ ልማት (መስመር ዝርጋታ) ዘርፍ ይከፈላል። በተጨማሪ ደግሞ ጨረታ በማውጣት ሁለት ኩባንያዎች ብቻ እራሳቸውን ችለው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ የሚሰጥ አሠራር ይዘረጋል።
እንደ ዶክተር ኢዮብ ገለጻ፤ ኢትዮ ቴሌኮም በሁለት ሲከፈል የመስመር ዝርጋታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ መገናኛዎችን፤ ሀገር አቀፍ ፋይበር ኦፕቲክ፣ የኔትወርክ ማማ የመሳሰሉ ግንባታዎችን የመከወን ድርሻ አለው። የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ የሁሉንም የስልክ፣ የኢንተርኔት እና ተጨማሪ አገልግሎቶችን የችርቻሮ ሽያጭ ኃላፊነት ይሰጠዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ከሚሰራው የግል ኩባንያ በተጨማሪ ሁለት የግል ተቋማትን ብቻ የሚጋብዝ የገበያ አመራር እንዲተገበር የተፈለገው ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የዘርፉ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ተገቢውን ክትትል ለማድረግ ነው።
በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት እና የተለያዩ አገራትን ተሞክሮ እና ስህተቶችን በመቀመር ለኢትዮጵያ አዋጭ የሆነውን የገበያ መዋቅር ለመለየት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል። በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም ብቻውን ሲሰራበት የቆየውን ዘርፍ አዳዲስ ኩባንያዎች በሚመጡበት ወቅት መሠረተ ልማቱን እያካፈለ የሚሰራበት በመንገድ ይተገበራል።
በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ኩባንያዎች ከቀጣይ ወር ጀምሮ ጨረታ በማውጣት ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም ሦስተኛው ሩብ ዓመት ላይ ሥራው እንደሚጠናቀቅ ዶክተር ኢዮብ ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ብሩክ ተስፋዬ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ እንደ ቴሌኮም ዘርፉ ሁሉ የስኳር ዘርፉም ወደግል ድርጅቶች ለማዞር በሚደረገው ጥረት ስድስት የስኳር ፋብሪካዎችን በቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደግል ለማዞር ታቅዷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 13 የስኳር ፋብሪካዎች ስድስት ብቻ ለማዞር የተፈለገው ሥራውን ከፋፍሎ ለመከወን በመታሰቡ ነው። ሁሉንም በአንድ ጊዜ ይዙሩ ቢባል ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ የተወሰኑት ላይ ብቻ በመጀመሪያ ይከናወናል። ይሁንና የትኛዎቹ የስኳር ፋብሪካዎች በቅድሚያ ወደግል ይዛወራሉ የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ጊዜያት የሚታወቅ ይሆናል።
እንደ ዶክተር ብሩክ ከሆነ፤ በ40 ቀናት ውስጥ በተሰበሰበ የፍላጎት መለያ ቅጽ (መረጃ) መሠረት በኬንያ፣ በምዕራብ እና ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም በሩቅ ምሥራቅ የሚገኙ 10 ድርጅቶች የተለያዩ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል።
እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ፤ በቴሌኮም ዘርፉ የሚሰማሩ ድርጅቶች የዋጋ ትርፍ ብቻ ሳይሆን ተደራሽነታቸውንም የሚከታተል አሠራር ይተገበራል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ጌትነት ተስፋማርያም