አዲስ ዓመት ሁልጊዜም አዲስ ነው፤ ዘመን አልፎ ዘመን ቢተካም አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሉም የትናንቱን የጨለማ ወቅትና የመከራ ጊዜ ረስቶ ለአዲስ ነገር፤ ለአዲስ ተስፋ ልቡን አስፍቶ በተስፋ የሚጠብቅበት የመልካም ብስራት ማሳያ ነው። ብዙዎች አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ ያሳለፉትን መጥፎ ትዝታ፤ ቁርሾና ጥላቻ ሁሉ ወደኋላ ጥለው እርስበርስ ይቅር የሚባባሉበት፤ ያለው ለሌላው ማዕዱን በማጋራትና ድጋፍ በማድረግ ፍቅሩንና ውግንናውን የሚገልፅበት በዓል በመሆኑ ሁሉም በጉጉት ይጠብቀዋል።
ኢትዮጵያውያን በችግር ጊዜ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባሕላቸው ዘመናትን ያስቆጠረ እንቁ የሚባል እሴት ቢሆንም ቅሉ እንደ ዘመን መለወጫ ያሉ በዓላት ወቅት ከወትሮ በተለየ መልኩ ድጋፋቸውና መረዳዳታቸው ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ ይበልጥ ደማቅ ያደርገዋል። ይህ በዓላትን ጠብቆ የሚደረገው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባሕል ታዲያ ኅብረተሰቡ ጋር ብቻ የቀረ አይደለም፤ በተለይ አሁን አሁን መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለያዩ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በማስታወስ ማዕድ የማጋራትና ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ የፋይናንስ ተቋማት እንደ ኢትዮ- ቴሌኮም ያሉ መንግስሥ ድርጅቶች በዚህ ረገድ አብነት ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው። ዘንድሮም የተለያዩ ተቋማት ለእነዚህ ዜጎች ያላቸውን ፍቅር በሚገልፅ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። መንግሥትም ዜጎቹ ያሳለፉትን ችግርና ክፉ ጊዜ ሁሉ ወደኋላ ጥለው ወደፊት አዲስ ራዕይ ሰንቀው እንዲሻገሩ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም የመሻገር ቀን ‹‹የመሻገር ጥሪቶች፤ የአዲስ ብርሃን ወረቶች ” በሚል የተሰየመ ሲሆን፤ ሁሉም ዜጋ አዳፋውን ጥሎ አዲስ ተስፋን ሰንቆ መጪውንና ብሩሁን አዲስ ዓመት እንዲሻገር የማድረጉ ሥራ ተጠቃሽ ነው።
በተመሳሳይ የተለያዩ የግል ተቋማት ከትርፋቸውም ሆነ ካለቸው እሴት ላይ በመቀነስ ለሌሎች በማካፈል ችግር ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ እንዲቀበሉ የማድረግ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ካሉበት ሁኔታ ለማውጣት በቋሚነት ድጋፍ ከሚያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት መካከል ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ተጠቃሽ ነው። ባንኩ የ2017 ዓ.ም ዘመን መለዋጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከሰሞኑ ለልብ ህሙማን ሕፃናት ማዕከል የበዓል ማክበሪያ 200 ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል።
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እመቤት መለሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባንኩ የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ በተቋቋመለት ዋነኛ ተግባር መስክ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ እንደ ሀገርም እንደ ከተማም የተለያዩ አበርክቶዎችን እያኖረ ይገኛል። ከዚሁ ቀዳሚ ተግባሩ ባልተናነሰ በተለያዩ ሀገራዊ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ እገዛው በተፈለገበት ጊዜ ሁሉ አለሁ ባይነቱን በተግባር የሚያሳይ ነው።
ለባንኩ ለውጥ የሚያመጡ የበጎ አድራጎት ማህበራዊ አጀንዳዎች ትልቅ አጋጣሚዎች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ጠቅሰው፤ ‹‹ከዚህ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ልበ ቀና ሰዎች በሙሉ እጃቸውን ከሚዘረጉለት ማዕከል ጋር ለበርካታ ዓመታት የቆየ ግንኙነት አለው›› ይላሉ። ማዕከሉ አሁን የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝበት ማዕከል ከ16 ዓመት በፊት በሚገነባበት ወቅት ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል አንዱ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ መሆኑንም አመልክተዋል።
ማዕከሉ አሁን ላይ ለታካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝበት የልብ አልትራሳውንድ ምርምር መስጫ ማሽን ከአራት ዓመታት በፊት ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ለማዕከሉ ድጋፍ ማድረጉንም ያስረዳሉ። በዚህ ድጋፍ በየወሩ በአማካይ ከ700 በላይ የልብ ህሙማን ህፃነት የነፃ የምርመራ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። በርካታ የባንኩ ሠራተኞችም በአሁኑ ወቅት በግላቸው የማዕከሉ ደጋፊ ሆነው አጋርነታቸውን እያሳዩ ሲሆን በደጋፊ አባልነትና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።
ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራ እንደሚሰራ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ይናገራሉ። በተለይም በማህበረሰቡ ሕይወት ላይ አወንታዊ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሕዝብ አጋርነቱን በተጨባጭ ማረጋገጥ መቻሉን ያስረዳሉ። ከእነዚህ መካከል ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ኬሮድ ኢትዮጵያ የተባለና የኢትዮጵያ ታላቅ ሯጫን ያቀፈ ማህበርን እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሙያቸው ሀገራቸውን ሕዝባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ አሁን ላይ ደግሞ ችግር ውስጥ የወደቁ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ከፍተኛ በጀት መድበን ድጋፍ እያደረግን ነው›› ይላሉ።
በተጨማሪ እንደ ሜሪጆይ፣ የልብ ህሙማን ሕፃናት ማዕከል፤ የአዛውንቶችን ማዕከላት ከሚደግፋቸው ተቋማት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ችግኝ በመትከልና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በልማቱም ዘርፍ ተሳትፎውን አስመስክሯል። እንዲሁም አሁን ላይ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማትም የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ ስለመሆኑ ይገልፃሉ። ‹‹አሁን ላይ በከተማችን የሚታዩት ስማርት ፖሎች ላይ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት አድርገናል›› ይላሉ።
ይህም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የፋይናንስ ተቋማት ያለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህም ባሻገር ከማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች ጋር በመሆን ኃላፊነቶችን ለመወጣት ከተያዙ በጀቶች ላይ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ኖሯቸው በፋይናንስ እጥረት ቤታቸው ቁጭ ያሉ ሥራ ፈጣሪዎችንም የማይመለስ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ይገልፃሉ። ባንኩ ችግር ውስጥ ያሉ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያደረገ ያለው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
አቶ ህሩይ አሊ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ሕፃነት መርጃ ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ማዕከሉ ከ34 ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት ንግሥት ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ የልብ ህሙማን ሕፃናትን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ አከናውኗል። ይሁንና በረጅም ጊዜ ዓላማው አራት እቅዶች የነበሩት ሲሆን፤ እነዚህም የራሱን ሆስፒታል መገንባት፣ መሳሪያዎችና የሰው ኃይል ማሟላት እንዲሁም ዘላቂነቱን ማረጋገጥ ናቸው። በዚህም መሠረት ከ16 ዓመት በፊት ‹‹አንድ ብር ለአንድ ልብ›› በሚል በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰብ በመቻሉ የራሱን ሆስፒታል እውን ማድረግ ቻለ።
ጎን ለጎንም መሳሪያውን በማሟላት ወደ ውጭ በመላክ የሚደረገውን የህክምና አገልግሎት ሀገር ውስጥ ማከናወን መቻሉን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስረዳሉ። ‹‹ሆስፒታሉ ሥራ ከጀመረበት ከዛሬ 16 ዓመት ጀምሮ ከስድስት ሺ በላይ የልብ ህሙማንን በነፃ ማከም ችሏል›› ይላሉ። ይሁንና የመጀመሪያዎቹን ስድስት ዓመታት ከውጭ በሚመጡ ባለሙያዎች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ዘላቂነት ለማምጣት የማያስችል እንደነበረ ይገልፃሉ። በመሆኑም በራስ አቅም ህክምናውን መስጠት ያስችል ዘንደ ሐኪሞችን ወደ ውጭ በመላክ በልብ ህክምና ዘርፍ ሰልጥነው እንዲመጡ በማድረግ ላለፉት አስር ዓመታት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በኢትዮጵውያን ብቻ ህክምናውን መስጠት መቻሉን ነው ያብራሩት።
ከእነዚህም መካከል ከዓመታት በፊት የልብ ህመምተኛ የነበረና ታክሞ አሁን ደግሞ የልብ ሐኪም በመሆን ማዕከሉን እየደገፈ ያለ ወጣት መኖሩን ይጠቅሳሉ። በተመሳሳይ በፋርማሲስትና በሌሎችም ሙያዎች ተሰማርተው ተቋሙንም ሆነ ሀገራቸውን በመደገፍ ላይ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን አመልክተው ይህም የሆነው በመላው በጎ አድራጊ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ መሆኑን ያስገነዝባሉ። ‹‹ትውልዱ ካለበት ችግር ተላቆ አምራች ዜጋ የማድረግን ያህል ትልቅ ሥራ የለም፤ ማዕከሉም ሆነ ህሙማኑ ካሰቡበት ለመድረስ የበጎዎችን ድጋፍ ይሻሉ፤ ለዚህም ነው እዚህ መድረስ የተቻለው›› ይላሉ።
የልብ ህክምና ሥራ በአንድ ጊዜ ተሟልቶ የሚያበቃ አለመሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀው፤ በተለይም የሰው ኃይሉንና መሳሪያ የማሟላት ጉዳይ ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚሻ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ይህ መደረጉ ደግሞ በእየለቱ የህክምና አገልግሎቱን ለህፃናቱ ለመስጠት እንዲቻል መሆኑን አስረድተው፤ ለዚህም የፋይናንስ አቅም ውስንነት ፈታኝ እንደሆነ ያመለክታሉ። ‹‹በእነዚህ ዓመታት ማዕከሉ የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት እንዲቀጥል መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል›› የሚሉት አቶ ህሩይ፤ በተለይ ማዕከሉ ምንም ዓይነት የበጀት ድጎማ የማይደረግበት በመሆኑ ለጋሾች የሚያደርጉለት ድጋፍ ህልውና ለማስቀጠል እንዳስቻለው ያስገነዝባሉ።
ማዕከሉ ራሱን ችሎ እንዲቆም ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ሲያደርጉ ከነበሩ የፋይናንስ ተቋማት መካከልም አንዱ የንብ ባንክ ዋነኛው እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ያስረዳሉ። ‹‹ሆስፒታሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርግልን ቆይቷል›› ይላሉ። ማዕከሉ በእነዚህ ዓመታት ለስድስት ሺ ሕፃናት ህክምና መስጠት ቢችልም ከችግሩ ስፋት አንፃር ገና ብዙ መሥራት የሚያስፈልግ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ‹‹የሌሎቹን ሆስፒታሎች ሳንጨምር በእኛ ሆስፒታል ብቻ ከሰባት ሺ በላይ ሕፃናት ወረፈ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ፤ ይህም የሚያሳየው ምንም እንኳን ስንታገዝ ብንቆይም ከችግሩ ጋር ስናነፃፀረው ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን ነው፤ አሁንም በፍላጎትና በአገልግሎቱ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ›› ሲሉም ያብራራሉ።
በመሆኑም እንደ ንብ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት በዓልን አስመልክተው በሚያዘጋጇቸው መርሃ ግብሮች ሁሉ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ያሉ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችን በማሰብ ሊደገፍ እንደሚገባም ይናገራሉ። ‹‹እርዳታ የአንድ ጊዜ ብቻ የሚያቆም አይደለም፤ ችግሩ ሰፊ እንደመሆኑ ሁላችንም በያለንበት ልንደገፍ ይገባል›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ ረገድ በተለይ ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ዓመታት በአጭር የስልክ መልዕክት ኅብረተሰቡን ለመድረስና በየጊዜው አቅሙን እንዲያሳድግ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑ አብነት አድርገው ይጠቅሳሉ።
ንብ ባንክ ያደረገው ድጋፍ ከባንኩ ባሻገር በርካታ የዘርፉ ተዋናዮችንም ኅብረተሰቡንም ጭምር የሚያነቃቃ መሆኑን ያነሱት። በተለይ የፋይናንስ ተቋማት ትርፍ የሚያገኙት ከኅብረተሰቡ በመሆኑ፤ ኅብረተሰቡ ጤነኛ በሆነ ቁጥር የተሻለ ደንበኛ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ተረድተው ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ‹‹ሁልጊዜ ከትርፍ አንስቶ መስጠትን ብቻ ሳይሆን እነዚህ ልጆች የእነሱም ኃላፊነት መሆናቸውን ተገንዝበው ልክ ምርታቸውን ለኅብረተሰቡ እንደሚያቀርቡት ሁሉ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለልብ ህሙማን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል›› ይላሉ። የልብ ህሙማን እንደማንኛውም ዜጋ ከታከሙ በኋላ አምራች ዜጋ መሆኑን ኅብረተሰቡም በማዕከሉ እየተሰራ ያለውን ሥራ በመጎብኘትና ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን እንዲያረጋግጥ፤ የበርካታ እናቶችንም እንባ እንዲያብሱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዝግጅት ክፍሉም የማዕከሉን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሃሳብ ይጋራል፤ በተለይም በተለያዩ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች አዲሱን ዓመት በተስፋና በሃሴት እንዲሁም በሙሉ ጤንነት ያከብሩት ዘንድ ዘመን አሻጋሪ የሆነ በጎነትና ፍቅር ልንለግሳቸው ይገባል በማለት ለማስገንዘብ ይወዳል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም