በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃር የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከምንለው በላይ ትልቅ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ፤ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ መታገዝ የግድ ሆኗል።
በተለይ በምግብ እራስን ችሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የማገዝ ጉዳይ ከልማዳዊ አሠራር ሥርዓት ማላቀቅ መቻል እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ ወጣት የሰው ኃይል ባለበት ሀገር ውስጥ በምግብ ዕጦት መቸገር መብቃት ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል።
ወጣት አዜብ የማነህ ትበላለች ውልደትና ዕድገቷ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ነው። ከመጀመሪያው እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቷን በአደገችበት አካባቢ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተከታተለችው አዜብ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች።
ወጣት አዜብ ከከፍተኛ ትምህርት ቆይታዋ በኋላ ወደ ሥራው ዓለም ስትሰማራ የመጀመሪያ ሥራዋን የጀመረችው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ኤጀንሲ የፅዳት አስተዳደር ኃላፊ በመሆን ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች በሥራው መቀጠል ባትችልም ይህ ሥራዋ ለዛሬ የፈጠራ ግኝቷ መነሻ ስለመሆኑ ትናገራለች።
ከደረቅ ቆሻሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምራት የቻለችው ወጣት አዜብ ለዚህ የፈጠራ ሥራዋ መነሻ ስለሆናት ነገር ስትናገር፤ ‹‹በልጅነታችን ለምግብነት የሚውሉ የእህል ዓይነቶችን የምንገዘበት ዋጋ በጣም ዝቅተኛ ነበር። ለአብነት ጤፍ ከሀምሳ እስከ መቶ ብር ይገዛ ነበር’’ የምትለው አዜብ፤ በአሁኑ ወቅት ግን የእህል ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ መጥቶ አነስተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ዋጋውን መቋቋም የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ይህ እንደ አንድ ዜጋ በእጅጉ ያሳስበኛል ትላለች።
የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሁልጊዜ ዘርተው ካጨዱ በኋላ ለቀጣይ ዓመት ለዘር የሚሆናቸው እህል ያስቀምጣሉ የምትለው አዜብ፤ ታዲያ የምርታማነት ችግሩ ከምን የመነጨ ነው? በሚል በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ መረጃዎችን ለማየት ጥረት በምታደርግበት ወቅት የምርታማነት ችግሩ መነሻ በሀገሪቱ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ የኬሚካል ማዳበሪያ በመጠቀማቸው መሬቱ በከፍተኛ ደረጃ በአሲዳማነት በመጠቃቱ የተፈጠረ ችግር ስለመሆኑ እንደተረዳች ትናገራለች።
አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት 80ኪሎ የኬሚካል ማዳበሪያ ቢጠቀሙ በሚቀጥለው ዓመት በተመሳሳይ መሬት ላይ ቢያንስ አንድ ሶስተኛ ተጨማሪ ማዳበሪያ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል የምትለው አዜብ፤ ይህ ከልሆነ መሬቱ ምርት መስጠት አይችልም። ይህ እንደ ሀገር እየተስፋፋ ለመጣው የአፈር አሲዳማነት የራሱን ሚና ተጫውቷል ትላለች።
በዚህ መነሻ አርሶ አደሩ እራሱ በስጋት ላይ ነው ያለው የምትለው የፈጠራ ባለሙያዋ አዜብ፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ከፍተኛ የኬሚካል ማዳበሪያ ዕጥረት አለ፤ አርሶ አደሩ ክረምት በመጣ ቁጥር የኬሚካል ማዳበሪያውን በወቅቱ ካላገኘ መሬቱ ፆሙን አደረ ማለት ነው። ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ላይ ጥላ ያጠላ በመሆኑ ይህንን ለመቅረፍ በማሰብ ነው ወደ ፈጠራ ሥራው የገባሁት ትላለች።
በአሁኑ ወቅት በብዛት አገልግሎት ላይ የሚውለው የኬሚካል ማዳበሪያ ከአየር ንብረት፣ ከዋጋ፣ ከአርሶ አደር ተደራሽነት አንፃር ያለው ችግር የሚታይና ጉልህ ነው የምትለው ወጣት አዜብ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ገበሬው መግዛት በሚችለው ተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል ማዳበሪያ እሷና ጓደኞቿ ይዘው እንደመጡ ትናገራለች።
‹‹የተፈጥሮ ማዳበሪያን ለማምራት የምንጠቀመው ከቤት ውስጥ የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን ነው›› የምትለው አዜብ፤ ‹‹የሰው ልጅ እስካለ ድረስ ተጠቅሞ የሚያስወግዳቸው ተረፈ ምርቶች ይኖራሉ፤ ይሄንን በአግባቡ ሰብስበን ፕሮሰስ አድርገን ስናወጣ መንግሥት ለማዳበሪያ ግዢ በየዓመቱ የሚያወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ ዜጎች ጤናማ ምግብ መመገብ እንዲችሉ ማድረግ እንደሚቻል›› ትናገራለች።
በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት በየዓመቱ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት የሀብት ብክነት እያደረሰ እንደሚገኝ የምትናገረው ወጣት አዜብ፤ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ መስጠት ያለበትን ጥቅም ሳይሰጥ በአፈር አሲዳማነት ምክንያት ይባክናል። ይህ እንደ ሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ትላለች።
እንደ ወጣት አዜብ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ እየታረሰ ካለው 16 ሚሊየን ሄክታር መሬት መካከል 6.5 ሄክታር መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ደግሞ 3.7 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነው በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ነው። ይህም ጥቅም ላይ የዋለውን የእርሻ መሬት 40 በመቶ ድርሻ የሚሸፍን ነው ትላለች።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ በፈሳሽ መልክ ብሎም የተለያዩ ተረፈ ምርቶችን በኮንቴነር በማድረግና ለ61 ቀናት በማብላለት እንዲደርቅ በማድረግ ኮምፖስት የሚያመርቱ አካላት አሉ የምትለው አዜብ፤ ‘’እኛ የምናመርተውን ማዳበሪያ ልዩ የሚያደርገው ብዙ ነገሮች አሉት። ለአብነት በኮንቴነር 61 ቀናት ቆይቶ የሚወጣው ኮምፖስት እንደ ሀገር ችግርን ሊፈታ ስለማይችል በጥቂት ጊዜ በብዛት ማምራት መቻላችን ነው’’ ትላለች።
በከተማዋ በተለያዩ አካበቢዎች የተዘጋጁ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች በመሄድ የሚሰበሰቡ የቆሻሻ ዓይነቶች በተለያየ ዓይነት የሚለዩ የሚያደርቁና የሚያሞቁ ማሽኖች አሉ የምትለው አዜብ፤ እነዚህ ማሽኖች የተፈጥሮ ማዳበሪያው በብዛትና በጥራት ማምረት እንዲቻል እንደሚያደርጉ ትናገራለች።
የማዳበሪያ ምርቱን በአንድ ኪሎ፣ በሁለት ኪሎ፣ በአምስት ኪሎ፣ በአስር ኪሎ፣ በሃያ አምስት ኪሎ፣ በሃምሳና በመቶ ኪሎ በማዘጋጀት ለገበያ የማቅረብ ውጥን እንዳላት የምትናገረው አዜብ፤ በዚህ መልኩ ለገበያ እንዲቀርብ የታሰበው በግብርና ሥራ የተሰማራ ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን የማዳበሪያ መጠን ገዝቶ መጠቀም እንዲችል መሆኑን ትናገራለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2017/18 የምርት ዘመን 20 ሚሊየን ኩንታል በላይ የኬሚካል ማዳበሪያ ለመግዛት እቅድ የነበረው ቢሆንም የቀረበለት 15 ሚሊየን ኩንታል ነው የምትለው አዜብ፤ ለዚህ ግዥ 15.5 ቢሊዮን ብር ወይም ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይደረጋል። ይህ እንደ ሀገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳድር ስለመሆኑ ታስረዳለች።
‘’እኛ የምናመርተውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ አንድ ኩንታል በ885 ብር እንሸጣለን’’ የምትለው አዜብ፤ የኬሚካል ማዳበሪያ በመንግሥት ድጎማ ቀርቦ 2800 ብር ነው የሚሸጠው ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት አለው። ከዋጋው ተመጣጣኝነት ባለፈ የመሬቱን ጤናማነት ከመጠበቅ አንፃር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው’’ ትላለች።
የኬሚካል ማዳበሪያ የእርሻ ማሳ ላይ አምና ከተጠቀምነው ሩብ ያህል ተጨማሪ ማዳበሪያ መጠቀም ያስፈልጋል የምትለው አዜብ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ስንጠቀም ግን አንድ ጊዜ ከተጠቀምን ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ያለ ተጨማሪ ማዳበሪያ ምርት መስጠት እንደሚችል ትናገራለች።
ሥራው ሰፊ እንደመሆኑ በመላው ሀገሪቱ ለማስፋፋት እቅድ አለኝ የምትለው አዜብ፤ ይህንን ህልም እውን ለማድረግ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰደች ስለመሆኑ ተናግራ፤ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ከቻለች ቴክኖሎጂውን በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዳረስ ለግብርና ሴክተሩ ምርታማነት የራሷን ሚና ለመወጣት እንደምትፈልግ ትገልጻለች።
‹‹የሰው ልጅ መኖር ካለበት መብላት አለበት›› የምትለው አዜብ፤ በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚያጋጥሙ የበሽታ ዓይነቶች ከአመጋገብ ጋር የተያያዘ መሆኑን ትናገራለች። ኢትዮጵያ የኬሚካል ማዳበሪያን ተጠቅማ ስለማምርት አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን እህል አይጠቀሙም። ይሄ ማዳበሪያ በራሱ በዜጎች ጤና ላይ እያሳደረ ያለው ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ስለዚህ ወደ ተፈጥሮ መመለስ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት ትላለች።
‹‹መንግሥት በራሱ የግድ ምርት መመረት ስላለበት በማሰብ የኬሚካል ማዳበሪያ በከፍተኛ ወጪ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባል። ሆኖም የማዳበሪያ ምርቱ በዜጎች ጤና ላይ በረዥም ጊዜ ሂደት የሚፈጥረው ችግር ትኩረት የተሰጠው አይደለም የምትለው›› አዜብ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ትናገራለች።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማምረት ሥራው በጥናትና ፋይናንስ ቢደገፍ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት የሚቻልበት መስክ ስለመሆኑ የምትናገረው አዜብ፤ የመንግሥት ድጋፍ ባለው መልኩ ከተሰራ የኬሚካል ማዳበሪያውን ሙሉ በሙሉ ከገበያ በማስወጣት የገበሬውን የማዳበሪያ ፍላጐት ከማሟላት ባሻገር ጤናማ ምርት በማምረት የአመጋገብ ሥርዓታችንም ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ትላለች።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትብብር እና አብሮ የመሥራት ፍቃደኝነትን በተመለከተ ወጣት አዜብ ስትናገር፤ ‹‹ተቋማት አብሮ የመሥራት ፍላጐት ቢኖርም መሟላት በሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ዙርያ ለሁሉም የሥራ ዓይነት ተመሳሳይ መመዘኛ ስለሚኖር ረዥም የቢሮክራሲ ሂደት ማለፍ ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣል። ስለዚህ የቴክኖሎጂ ሃሳብ ላላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች አመቺ አሰራር ቢኖር የበለጠ ውጤታማ መሆን ይቻል ነበር›› ትላለች።
የብድር አቅርቦትን በተመለከተ እንደ ስታርት አፕ ሃሳብ ይዘን ነው የምንነሳው የምትለው አዜብ፤ ያንን ሃሳብ አይቶ ወይም የአዕምሮ ንብረት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት አይቶ ብድር የሚሰጥ ባንክ ቢኖር በሂደት ሥራው እየተሰራ ብድሩን መመለስ እንደሚቻል ተናግራ፤ ነገር ግን ይህ አሰራር አለመኖሩ እንደ ቴክኖሎጂ ኩባንያ በፈለግነው ልክ ወደፊት መራመድ እንዳንችል እያደረገ ነው ትላለች።
የመሥሪያ ቦታ ችግር ሥራዬን በፈለኩት መጠን መሥራት እንዳልችል አድርጎኛል የምትለው አዜብ፤ የፈጠራ ሃሳቡ ጠቃሚ ነው ወይስ አይደለም? ተግባራዊ መሆን ይችላል አይችልም? ለብዙ ሰው የሥራ ዕድል ይፈጥራል አይፈጥርም? የሚለው እንደ ሀገር በአግባቡ ታይቶ፤ የመሥሪያ ቦታ ችግሩ ቢፈታ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ መሆን እንድንችል ያግዘናል ትላለች።
‘’በ2017 ዓ.ም እራሴን አጠናክሬ የመንግሥት ድጋፍ ተጨምሮበት ቴክኖሎጂውን ወደ ተለያዩ ክልሎች በማስፋትና ወጣቶችን በማሰልጠን ምርቱን በስፋት የማምረት እቅድ አለኝ’’ የምትለው አዜብ፤ በረዥም ጊዜ ሂደት ደግሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ደረጃውን ጠብቆ በማዘጋጀት ወደ ውጭ የመላክ ሃሳብ እንዳላት ተናግራለች።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 1 /2016 ዓ.ም