– 820 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ በሰው ጉልበት ተሰርቷል
– 252.7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል
አዲስ አበባ ፡- በትግራይ ክልል በ2011 በጀት ዓመት 41 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1ሺ543 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡ በክልሉ ሕዝብ ጉልበት 820 ኪሎ ሜትር መንገድ መሰራቱም ተጠቆመ፡፡
የትግራይ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 16 መደበኛ ጉባዔ የክልሉን መንግሥት የ11 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እንደገለጹት፣ የክልሉን ሕዝብ በበጀት ዓመቱ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ሥራ 41 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ ከ1 ሺህ 543 ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።
የወጪ ንግድን በማጠናከር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በተሰራው ሥራም እንስሳትን ለውጭ ገበያ በመላክ 118 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።
በክልሉ የሚመረቱ የጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ውጤቶች አልባሳትን ወደ ውጭ በመላክ 21 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ዶክተር ደብረፅዮን፣ ከዚህም 9 ሚሊዮን ዶላር በኢንዱስትሪ ፓርክ ከተሰማሩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ የተገኘ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በማዕድን ዘርፍ በተሰራው ሥራም 3 ነጥብ 5 ኩንታል ወርቅ በመሰብሰብ 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል። በተጨማሪም 2 ነጥብ 2 ኩንታል የሳፋየር ማዕድን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱንም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያብራሩት።
በክልሉ ያሉ የቱሪዝም መስኮች በተለያዩ መንገዶች በማስተዋወቅ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር ቱሪስቶች ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ በተሰራው ሥራም ከ98 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍም ቀበሌን ከወረዳ ለማገናኘት ታቅዶ በተከናወነው ሥራ ባለፉት 11 ወራት 820 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ በሕዝብ ጉልበት መሰራቱን ገልጸዋል።
እስካሁን 41 ቀበሌዎች ከዋናው መንገድ እንዳልተገናኙ የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፥ የዚህ ምክንያት ደግሞ የቀበሌዎቹ መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ ምቹ ባለመሆኑ በሰው ጉልበት መስራት የማይቻል በመሆኑ ነው ብለዋል።
ለሥራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች በገጠር እና በከተማ ባሉት የእርሻ እንዲሁም የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ታቅዶ በተሰራው ሥራም እስካሁን ለ261 ሺህ 671 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው የድህነት መጠን 29 በመቶ በመሆኑ ይህንን ለመቀነስ የሚያስችል የሥራ ዕድል በማስፋት ረገድ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ባለፉት 11 ወራት በገጠር በመስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ሥራ 53 ሺ 76 ሄክታር መሬት በማልማት 145 ሺ 730 አባወራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።
የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርትም የመጠጥ ውሃ ሽፋኑ በገጠር 56 በመቶ፤ በከተሞች ደግሞ 60 በመቶ መድረሱን ያስታወቁ ሲሆን፣ በክልል ደረጃ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱ 57 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
ይህ ከተጠቃሚዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ያመላክታል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ በወሊድ ወቅት የሚከሰት የእናቶች እና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በተሰራው ሥራ በበጀት ዓመቱ በሰለጠኑ ባለሙያዎች የማዋለድ ሥራው 75 በመቶ መድረስ መቻሉ አስታውቀዋል። እንዲሁም የቅድመ ወሊድ ክትትል 65 ነጥብ 5 በመቶ፣ የድህረ ወሊድ ክትትል 84 በመቶ እና የቤተሰብ እቅድ 35 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን አንስተዋል።
የበሽታ ቅድመ መከላከል ዘርፍ በተሰራው ሥራም ሁሉንም ዓይነት ክትባት ተደራሽነት 92 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱን አክለው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ