አዲስ አበባ፡- ጽንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት፣ ግጭቶችና መዘዛቸው፣ ደካማና ውስን የዴሞክራሲና የፖለቲካ ባህል በመኖሩ ምክንያት በአገራዊ ለውጡ ላይ የተደቀኑ ችግሮችን የሲቪል ማኅበረሰቡ ተሳትፎ ሊያቃናው እንደሚገባ ተጠቆመ። «የሪፎርም እርምጃዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች»በሚል መሪ ሀሳብ የሲቪል ማኅበረሰቡን ያካተተ ውይይት ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የፌዴራል ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንዳሉት፤ ሕዝባዊ አመጽና ግፊት፣ የፖለቲካ ቀውስና መሽመድመድ እንዲሁም የመርህ ጉዳይ አሁን ላይ ያለው ለውጥ እንዲጀመር ምክንያት ቢሆኑም፤ ጽንፈኛ የፖለቲካ ዝንባሌዎችን ጨምሮ በአገሪቷ የተከሰቱ ግጭቶችና ደካማ የዴሞክራሲ ባህል መኖራቸው በለውጡ ቀጣይነት ላይ ተግዳሮት ሆነዋል።
የሲቪል ማኅበረሰቡም የመንግሥት የማሻሻያ የለውጥ መርሆዎችን በመከተል የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማስቀጠል ሚናውን መወጣት ይኖርበታል።
እንደ ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ማብራሪያ፤ የለውጡ ዓላማ የመንግሥት ሥልጣን በሕግ የተገራ እንዲሆን፣ የዜጎች መሠረታዊ ነፃነትና መብቶች እንዲከበሩ፣ ፍትህ፣ ሠላምና ብልጽግና የሰፈነበት «ሀገረ መንግሥት» እና ማኅበረሰብ መገንባት ሲሆን፤ በሂደቱም አሳታፊና በጥናት ላይ የተመሰረተ የአመራር ለውጥ፣ የሕግና አስተዳደራዊ ማሻሻያ በማድረግ ተቋማዊ ለውጦች ተደርገዋል።
ነገር ግን ለውጡን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ ቢፈለግም ማነቆ የሆኑ ጉዳዮች ገጥመዋል። የሲቪል ማህበረሰቡ ለውጡ በጊዜ፣ በጥራትና በሚፈለገው ደረጃ እንዲጓዝ ተጽእኖውን በመቋቋም መንግሥትን በመደገፍ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይገባል።
የጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት ህብረት ለተቀናጀ ሥነ ሕዝብ ጤና አካባቢ ጥበቃ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ ተክሉ በበኩላቸው፤ አገሪቷ ምንም እንኳን በሁሉም መስክ ለውጥ ላይ ብትሆንም በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠሙ መሆኑን የሲቪል ማኅበረሰቡ እንደሚገነዘበው ጠቅሰው፤ ቁልፍ የተባሉ ችግሮች በሲቪል ማኅበረሰቡ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በኅብረተሰቡና በመንግሥት የዴሞክራሲ ግንዛቤ ችግር የተፈጠሩ መሆናቸውን፤ የሲቪል ማህበረሰቡ ውግንናን ለሕዝቡ በማድረግ ረገድ፤ በልማት፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ በተገቢው መንገድ እየሰራ አለመሆኑን፤ በውስጡም የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል አለመኖሩን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ነጋሽ ገለጻ፤ ክፍተቶች የታዩት ሲቪል ማኅበረሰቡ ራሱን እንዲያበቃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሰራ ድጋፍ ባለማግኘቱ ነው። በመሆኑም አገሪቷ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ እንድታመጣ ከታሰበ የሲቪል ማህበረሰቡን የሚያሳትፍ የንቅናቄ ሥራ ያስፈልጋል። የሲቪል ማህበረሰብ በባህሪው ለፖለቲካው ያልወገነ በመሆኑ በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየታየ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመቅረፍ ቁልፍ ቦታ ሊሰጠው ይገባል።
መንግሥት የለውጥ ሥራዎችን ሲያካሂድ ብቻውን መሆን የለበትም የሚሉት አቶ ነጋሽ፤ በተለይ የሲቪል ማኅበረሰቡን ያላካተተ እንቅስቃሴ ለውጡን ዳር ለማድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል። ጠያቂ ኅብረተሰብና ለሕዝብ የወገኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመፍጠር፤ እንዲሁም ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ እንዲያዳብሩ የሲቪል ማህበረሰቡ ሚና ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ስም ያልታወቀ ክርክር ከማድረግ ወጥተው ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጉም የሲቪል ማህበረሰቡ ያግዛል ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት፤ መንግሥት በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞው ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሴክተርን የማሻሻል ሥራ ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው ገዳቢ አዋጅ ተሽሮ አዲስ አዋጅ ወጥቷል።
ይህም በአገሪቷ የፖለቲካ ዴሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያለ ገደብ ለመንቀሳቀስ የሚፈቅድ በመሆኑ የታዩ አገራዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግሮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን ያስችላል። የሲቪል ማህበረሰቡ የዳር ተመልካች ሳይሆን በተከሰቱ ማንኛውም ቀውስ ላይ የጋራ ርብርብ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
አዲሱ ገረመው