ወጣትነት ትኩስነት ነው። ወጣትነት ብርታት ነው። ወጣትነት ፈጣሪነት ነው። ወጣትነት ጉልበት ነው። ወጣትነት አዋቂነት ነው። ወጣትነት ውበት ነው። ወጣትነት ሁሉ ነገር ነው። ሆኖም የወጣትነት እድሜ በብልሃትና በብልጠት ካልተያዘ ጉዳቱ የዛኑ ያህል ሰፊ ነው። ስለዚህ ወጣትነት ስክነት፣ ብልሃት፣ ስሜትን መቆጠርና ማሸነፍን ይጠይቃል። ይህን ማድረግ ሲቻል ነው ውድ የሆነውን የወጣትነት እድሜ በአግባቡ ተጠቅሞ ወደቀጣዩ የእድሜ ምዕራፍ መሸጋገር የሚቻለው።
ይህን አፍላ እድሜ ታዲያ ወጣቶች ለብቻቸው በራሳቸው ጥረት ብቻ ሊሻገሩት አይችሉም። የቤተሰባቸው፣ የአካባቢያቸው፣ የትምህርት ቤታቸው፣ የወረዳቸው፣ የከተማቸው ከፍ ሲልም የሀገራቸው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። የወጣቶች ጉዳይ ሁሉም ጉዳይ ነው። ስለወጣቶች ጤና ሚኒስቴር፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎችም ድርሻ አለባቸው። መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በወጣቶች ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የወጣቶች ጉዳይ ይመለከታቸዋል።
በወጣትነትና አፍላ ወጣትነት እድሜ ከሚገጥሙ ችግሮች አንዱና ዋነኛው በቶሎ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መጀመር፣ ያልታሰበ እርግዝና መከሰት፣ ይህንንም ተከትሎ ለአባላዘር፣ ኤች አይቪና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ ናቸው። ከነዚህ ችግሮች ለማምለጥ ወጣቶች ከራሳቸው ንቃተ ሕሊና ባሻገር ሌሎች የሥነ ተዋልዶ ጤናና ምክር አግልሎቶችን በጥራት በአካባቢያቸው ማግኘት አለባቸው።
ወጣት ቴዎድሮስ ታደሰ ‹‹ከፍታ›› በተሰኘ ፕሮጀክት የወጣቶች ተኮር ጤና አገልግሎት ሰጪ ባለሙያ ነው። ከፍታ ወጣቶች በሀገራቸው የሚገጥማቸውን በርካታ ችግሮች ለመቅረፍ መፍትሔ ይዞ የመጣ ፕሮጀክት ነው። በከፍታ ፕሮጀክት ወጣቶች በርካታ አገልግሎቶችን ያገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ የጤና አገልግሎት ሲሆን በዚህ አገልግሎት ውስጥ በተለይ እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ ወጣቶች ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በነፃ ያገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የምክር፣ የአጭርና የረጅም ግዜ የወሊድ መከላከያ አገልግሎት በዋናነት ይጠቀሳሉ። በወጣቶች በአመጋገብ ዙሪያም የምክር አገልግሎት በዚህ ፕሮጀክት እንዲያገኙ ይደረጋል።
በአሁኑ ግዜ ደግሞ የአዕምሮ ሕመም በወጣቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ጫና እያደረሰ ከመሆኑ አኳያ ይህን ችግር ለመቅረፍ የከፍታ ፕሮጀክት የጤና አገልግሎት መስጪያ ባሉበት ቦታዎች ሁሉ የሥነ አዕምሮ ምክር አገልግሎት እየተሰጠ ነው። ወጣቶች በነዚህ አገልግሎት መስጪያ ቦታዎች የተለያዩ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ የሚሰማቸው ስሜት ምን እንደሆነና አገልግሎቱን ካገኙ በኋላ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ ተጠይቀው ያሉባቸውን የሥነ ልቦናና የአዕምሮ ችግሮች በተቻለ አቅም መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋል። የአዕምሮ ሕመማቸው ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ወደ አዕምሮ ሐኪሞች በሪፈር እንዲሄዱ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፆታ ተኮር ጥቃቶች ሲያጋጥሙ ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ ወጣቶች የሕክምና አገልግሎትና እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም ሥራ የሚከናወነው ከጤና ጣቢያዎች፣ ከትምህርትና ጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ነው።
በዚህ ፕሮጀክት ወጣቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፕሮጀክቱ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ለወጣቶች ምቹና ሳቢ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን እንዲያውቁና እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው። ባሕላቸውን፣ እውቀታቸውንና አመለካከታቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩም ነው ወጣቶቹ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚደረጉት። አገልግሎቱን ለወጣቶቹ ተደራሽ ለማድረግ ደግሞ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ይከናወናሉ። ወደ ከፍታ ፕሮጀክት ማዕከል ከመጡ ደግሞ አገልግሎቶችን በስፋት ያገኛሉ። አገልግሎቶቹም በጤና ጣቢያዎች፣ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢዎች ላይ ይሰጣሉ።
ወጣት ቴዎድሮስ እንደሚገልፀው፣ አንድ ወጣት የጤና አገልግሎቱን ብቻ አግኝቶ እንዲሄድ አይደለም ዋናው ዓላማው። ሌሎች የከፍታ ፕሮጀክት ፕሮግራሞች ማለትም ለሥራ ፈጠራ የፋይናንስና ሥልጠና አገልግሎቶችንም እንዲያገኙ ይደረጋል። በዚህ ከፍታ ፕሮጀክትም በጤና አገልግሎት ለ2 ሚሊዮን ወጣቶች ተደራሽ ለመሆን እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል። ይህንንም እቅድ ለማሳካት ሙከራ እየተደረገ ነው።
በአምስተኛው የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ጉባኤ ደግሞ በከፍታ ፕሮጀክት ውስጥ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ ለወጣቱ ለማስተዋወቅ ተሞክሯል። በዚሁ አጋጣሚ ወጣቶች በፕሮጀክቱ ያሉ የጤና አገልግሎቶችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል። ይህ ከፍታ የተሰኘው ፕሮጀክት እ.ኤ.ኤ እስከ 2026 ድረስ የሚቆይ ሲሆን ዩ ኤስ አይ ዲ እና አምሬፍ የተሰኙ የውጪ ድርጅቶችና ሌሎች አጋር አካላት ይደግፉታል። ይህንኑ የጤና አገልግሎት ለወጣቶች በስፋት ለማዳረስ ሙከራ እየተደረገ ይገኛል።
ወጣቶች አገልግሎቱ ከዚህ የበለጠ እንዲሻሻልና ከፍ ያለ አገልግሎት እንዲሰጥ ፍላጎቱ አላቸው። በወጣት ስብዕና ግንባታ ማዕከላት ሌሎች አገልግሎቶች ቢሰጡም የጤና አገልግሎቶች እየሰጡ ባለመሆኑና ይህን ክፍተት ከፍታ ፕሮጀክት እየደፈነ በመሆኑ በወጣቶቹ በኩል የሚቀርበው ግብረ መልስ አበረታች ነው። የሚሰጠው አገልግሎትም እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ በመሆኑ ደስተኞች ናቸው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም