ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 24 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባሰሙት ንግግር የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሥራ አጥ ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ይፋ አድርገዋል። በመሆኑንም መንግሥት በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት መጨረሻ ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን አስታውቀዋል።
ይህን ተከትሎም አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን መንግሥት ያሉበትን የቤት ሥራዎች መስራት ከቻለ ግቡን ያሳካል የሚል እምነት አላቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር አጥላው አለሙ እንደሚሉት፤ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ማምረት ቢቻል ለብዙ ሥራ አጥ ዜጎች ሥራ መፍጠር ይቻላል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአብዛኛው የሌሎች አገሮችን የኢንዱስትሪ ምርቶች በመግዛት ላይ የተመሰረተ መሆኑ አምራች ኢንዱስትሪው ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር አልቻለም። በመሆኑም ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት ከተቻለ ጥሬ ዕቃ ከማቅረብ ጀምሮ ምርቶቹን እስከ መሸጥ ድረስ ባሉ ሂደቶች ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።
መንግሥት በዋናነት በጥናት ላይ ተመስርቶ አነስተኛ እና ጥቃቅን ማህበራትን በማስፋፋት፣ ለወጣቶቹ ሥልጠና በመስጠት፣ መስሪያና መሸጫ ቦታ ቀድሞ በማዘጋጀት፣ ብድርና የገበያ ትስስር በማመቻቸት ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርበት ይገልፃሉ። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ከውጭ አገር የሚገቡትን ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲያመርቱም ሙያዊ እገዛ መስጠት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም በሥራ አጡ ዜጋና በመንግሥትም ሰርተን መለወጥና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት መተካት እንደሚቻል ማመንይገባል።
የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብና በመስኖ ልማት ላይ በማተኮር ለብዙ ዜጎች ሥራ መፍጠር ይቻላል የሚሉት ዶክተር አጥላው፤ በተለይም የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት የውሃ መሳቢያ ፓምፖችን፣ መሬቱና ማዳበሪያ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ይጠቅሳሉ። እነዚህን ዕቃዎችም ወደፊት በኢትዮጵያ ለማምረት የሚያስችሉ ሥራዎች ሊጀመሩ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
ሥራ ሲፈጠር ዘላቂ ሥራና ለሌሎችም ሥራ የሚፈጥር መሆን አለበት የሚሉት የኢኮኖሚ ምሁሩ፤ ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ለመፍጠር ሲታሰብ በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ መተኮር እንደሚገባው ይናገራሉ። በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተር ፕራይዞች ለሚሰማሩ ወጣቶችም ከዛሬ ጀምሮ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታት፤ የመሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የታክስ ሥርዓቱን ማሻሻልና የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ከመፍትሄዎቹ መካከል እንደሚገኙበት ነው ያመለከቱት።
የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር ገና በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መንግሥት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ ብዛት ያለው የሥራ ዕድል መፈጠር ያለበት በግሉ ሴክተር ነው። ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ከባድ ቢሆንም የማይቻል ነገር የለም። መንግሥት የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ ሲል ብቻውን ሳይሆን ከግሉ ሴክተር ጋር በመተባበር ከሆነ ከወዲሁ መነጋገርና መስማማት ያስፈልጋል።
የግሉ ሴክተር ብዙ የሥራ ዕድል እንዲፈጥርና ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ ታክስ ሥርዓቱ፣ የብድር የወለድ መጠኑ፣ መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል አለበት የሚል ሃሳብ አላቸው። ወጣቱ ራሱን የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ለማድረግም አሰሪ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ወዲያው ወደ ሥራ የሚገባበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ መፍትሄዎችን አመላክተዋል።
እየተበራከተ የመጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ከአሁኑ የተሻለ ኢንቨስትመንትን መሳብና ፈቃድ ያወጡት ደግሞ ቶሎ ወደ ተግባር ማሸጋገር እንዳለበት ያስረዳሉ።
በተጨማሪም በተሻሻለና በተጠና መልኩ የውጭ ኢንቨስትመንት በይበልጥ መሳብ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ክፍለ ኢኮኖሚዎች ቅድሚያ በመስጠት የታቀዱ ፕሮጀክቶችን መተግበር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። የውጭ የሥራ ዕድል ድህነትን ለመቀነስ የመጠቀም አማራጭን መከተል እንደሚገባ ተናግረው፤ ለዚህም ሁሉንም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ማሳተፍ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
«’ከልብ ከአለቀሱ እምባ አይገድም’ እንደሚባለው መንግሥት ከልቡ ከሰራ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥራ መፍጠር አያቅተውም» የሚሉት የጅኒስ ኢንተርፕርነር ሽፕ ሥልጠና ማዕከልና ምክር አገልግሎት ባለቤት ዶክተር ወረታው በዛብህ ናቸው። እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የጉልበትና የሙያ ሠራተኞች በሚል ለይቶ መንቀሳቀስ አለበት። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፉ ብዛት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል።
የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችንም ትኩረት ሰጥቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት በርካታ ዜጎች ሥራ መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ዶክተር ወሮታው፤ ሰው ለዓላማው ታማኝ ከሆነ በግሉ ሥራ መፍጠር እንደሚችል ይናገራሉ። መንግሥትም የወጣቱን በሥራ ላይ ያለውን የተቀጣሪነት አመለካከት ለመለወጥ መስራት እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሥራ ፈጠራ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ መንግሥቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት 11 ወራት 1 ነጥብ 388ሺ 574 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ በ61 በመቶው በቋሚነት የተፈጠረ ነው። በመጪው ዓመትም የታሰበውን ግብ ለማሳካት ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በከተሞች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስት ራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በንግድና በአገልግሎት ላይ ያተኮሩ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው፤ በተለይም በግሉ ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በክልሎች ባሉ ባለሀብቶች ጋር ውይይት ማድረግ መጀመሩን ነው የጠቁሙት።
ለጥቃቅና አነስተኛ ኢንተርፕራየዞች የመሸጫና የመስሪያ ቦታ የሚያቀርበው መንግሥት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ረገድ የአቅርቦት ውስንነትን በመጠኑ ለመፍታት በግል መኖሪያ ቤትና ስፍራ እንዲሰራና እንዲፈቀድ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተደርሶ መመሪያው ለክልሎችም መድረሱን ያመለክታሉ። የገበያ ችግሩን ለመፍታትም ከግዥ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር የመንግሥትን የግዥ መመሪያ እንዲሻሻል የማድረግ ሥራም እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ጌትነት ምህረቴ