ባንዳነት የጠላቶቻችን እኛን ጠልፎ የመጣል ያልተለወጠ የሴራ መንገድ ነው

ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ለነፃነታቸው እና ለብሔራዊ ክብራቸው ባደረጓቸው ከፍ ያለ ተጋድሎ የጠየቁ መራራ ትግሎች ባንዳ እና ባንዳነት ያስከፈሏቸው ዋጋ በብዙ መልኩ የከፋ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመላክታሉ። መልከ ብዙ የሆነው የባንዳነት ትርክት በዚህ ዘመን /ዛሬ ላይ/ ሀገርን ተመሳሳይ ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑም እለት እለት የምንሰማቸው ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ታሪኮች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።

ባንዳነት በመሠረታዊነት ከሀገር እና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራስ ጥቅም በተቃርኖ /በጠላትነት/ መቆምን፤ ከሀገር እና ከሕዝብ ጥቅም ጋር በግልጽ ይሁን በስውር ከጠላት ጋር ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር ማበርን፤ የጠላት ሁለንተናዊ መሣሪያ ሆኖ መሰለፍን፤ በብዙ መልኩ ከራስ ማኅበረሰባዊ ስሪት ጋር በተቃርኖ መቆምን የሚያመላክት ነው።

ይህ በአብዛኛው ከአስተዳደግ ጋር በተያያዘ ከሚፈጠር ራስ ወዳድነት የሚመነጭ፤ ከማኅበረሰብ ማኅበራዊ እሴቶች አፈንግጦ መገኘትን የሚያመላክት፤ ሀገር በአስቻጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምትገኝበት ወቅት አቅም ገዝቶ፣ ከፍ ላሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ምንጭ መሆን የሚችል ማኅበረሰባዊ መርገምት ነው።

ይህ እውነታ የሩቁን እንኳን ትተን የቅርቡን የስድስት አስርት ዓመታት ሀገራዊ ታሪካችንን ስንመለከት የብዙ ውድቀታችን ምንጭ ነው፤ በነዚህ ጊዜያት ውስጥ አንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች፤ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ዓላማቸውን ለማሳካት ሀገርን እንደሀገር የሕልውና አደጋ ውስጥ በጣሉ የባንዳነት ተግባር ተሰልፈው በአደባባይ ያለእፍረት ሲተጉ አይተናል፤ ይህን ተግባራቸውን በወርቅ መጋረጃ ለመጋረድ ሲጥሩ አስተውለናል።

በሕዝብ እና በሀገር ስም የሕዝብ እና የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራትን ሲፈጽሙ፤ በሕዝብ ተስፋ ሆኖ የመገኘት ሕልም ላይ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ሳይቀር በአደባባይ ሲያመነዝሩ አይተናል፤ ሰምተናል። በዚህም እንደሀገር የከፈልነው ዋጋ ጠላቶቻችን ፊት ለፊት ብንገጥም ልንከፍል ከምንችለው የበለጠ እንጂ ያነሰ እንደማይሆን ይታመናል።

ጠላቶቻችን እንደሀገር እኛን ፊት ለፊት ገጥመው ማሸነፍ እንደማይችሉ ከትናንት ታሪካችን ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ከሆነው ተሞክሯቸው ተረድተዋል፤ በኛ ላይ አቅም ሊገዙ የሚችሉት ባንዳዎች በሚፈጥሩት ሀገራዊ ግራ መጋባት እና ትርምስ እንደሆነ፤ ባንዳነት በታሪካችን ካስከፈለን ዋጋ ከኛ ይልቅ እነሱ በብዙ መማር ችለዋል።

ይህ ለጠላቶቻችን አቅም የሆነ ማኅበራዊ መርገምት ዛሬም ይህን ትውልድ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለው፤ እየፈተነውም ይገኛል። የሀገራችን ብሩህ ዕጣ ፈንታ ሁሌም የሚያስጨንቃቸው አካላት የብሔራዊ ጥቅማቸው አደጋ አድርገው ለሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ በመሆን፤ በአዲስ የፉከራና የቀረርቶ ዜማ ከተኙበት ተነስተው እንዲንጠራሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

እንደሀገር ከትናንት የድህነት እና የኋላቀርነት ትርክት ወጥተን የራሳችንን ዕጣ ፈንታ በራሳችን ለመወሰን የጀመርነውን ዘመኑን የሚመጥን የለውጥ መነቃቃት በማደብዘዝ፤ በብዙ ተስፋ እና የተስፋ ዜማ የጀመርነውን ለውጥ እንደቀደሙት የለውጥ መነሳሳቶች በግራ መጋባት እና በግጭት ወዳልተፈለገ የጥፋት መንገድ ለመግፋት ቀንና ሌሊት እየሠሩ ነው።

ለዚህም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የገባንበት ፈተና በየትኛውም መመዘኛ የሕዝባችን መሻት እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በየትኛውም አቅጣጫ ያለ የሀገሪቱ ሕዝብ ከግጭት እና ከጦርነት አተርፋለሁ ብሎ የሚያስብ አይደለም። ለዚህ የሚሆን የሥነልቦና መሠረት የለውም። የሕዝባችን መሻት ሰላም እና ልማት ነው። ይህ የዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የቀደሙ ትውልዶች በዘመናት ውስጥ የተሰናሰለ ያልተሳካ ፍላጎት ነው።

በነዚህ አምስት ዓመታት ፈተና ሆነው ዋጋ ያስከፈሉን፤ ዛሬም ዋጋ እያስከፈሉን ያሉ ችግሮቻችን በአንድም ይሁን በሌላ ሀገራዊ ሠላም እና መረጋጋት ሊያመጣ የሚችለው ሁለንተናዊ ሀገራዊ ልማት የሚያሳስባቸው ኃይሎች እና የነሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሆኑ ባንዳዎች የቀን ከሌሊት ፋታ የለሽ ሴራ ውጤት ነው። የታሪካዊ ጠላቶቻችን የዘመናት ፍላጎታቸው መገለጫ አሁናዊ እውነታ ነው።

በመላው ዓለም ተበትነው ሀገርን በሟርት እና በእርግማን፤ በክፋት እና በጥፋት ትርክት ሕዝባችንን ግራ በማጋባት ከጀመረው የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል የሚደረግ፤ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የተቀናጀ ዘመቻም ዛሬ ላይ የተጀመረ ሳይሆን ዘመናትን ያስቆጠረ የጠላቶቻችን እኛን ጠልፎ የመጣል ያልተለወጠ የሴራ መንገድ ነው። የባንዳዎች አሁናዊ የባንዳነት ተግባር የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው።

አዲስ ዘመን  ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You