‹‹በማህበረሰቡ ውስጥ ነን›› በዩኒቨርሲቲው አርማ ላይ የሚገኝ መሪ ቃል ነው። ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹የማህበረሰብ ችግር ፈቺ›› እየተባሉ ቢጠሩም ይህ ዩኒቨርሲቲ ግን የአርማው መሪ ቃል አድርጎታል-የጅማ ዩኒቨርሲቲ። ‹‹ዩኒቨርሲቲው በመለያው ላይ የተጠቀመውን ቃል በተግባር አውሎት ይሆን?›› የሚለውን ጥያቄ ይመልስልን ዘንድ በጅማ ከተማ ውስጥ አንድ ነገር አስተዋልን።
በአንድ ግቢ ውስጥ ከተለመደው ወጣ ያለ የአትክልት አይነቶች ይታያሉ። በመሬት ላይ የምናውቃቸው የአትክልት አይነቶች በአየር ላይ ተንጠልጥለዋል። ይህ የሆነው ደግሞ ከነሕይወታቸው ነው። አፈርና ውሃ ሳይጎልባቸው ወዛቸው መሬት ላይ ካሉት ጋር እኩል ነው።
እነዚህ በአየር ላይ የተንጠለጠሉ የአትክልት አይነቶች ጠጋ ብሎ ሲታዩ በጄሪካንና በተለያዩ የወዳደቁ ፕላስቲኮች የተተከሉ ናቸው። መሬት ላይ ላሉት ተክሎች በታጠረው አጥር ላይ በገመድ ተንጠልጥለዋል። ከተማ ውስጥ
በቦታ ጥበት ምክንያት ትልልቅ ፎቆች እንደሚሰሩት ሁሉ አታክልትም ቦታ ለመቆጠብ በዚህ መልክ ተዘጋጅተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ግቢ ውስጥ አረጋውያንና ሕጻናትን የሚንከባከቡ የበጎ አድራጊዎች ክፍል ይታያል። ሕጻናቱ ከጎዳና ላይ ለጆሮ በሚከብዱ ነገሮች ተጥለው የተገኙ ናቸው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና እንስሳት ህክምና ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዋሲሁን ሀሰን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከሚሰራቸው ሥራዎች አንዱ ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ነው። አገልግሎቱን ከሚሰጥባቸው ቦታዎች አንዱ በጅማ ከተማ የሚገኘው የ‹‹ሰው ለሰው›› የበጎ አድራጎት ማህበር ነው። ማህበሩ በበጎ ፈቃደኞች የተቋቋመ ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ የባለሙያና የመገልገያ ዕቃዎች ድጋፍ እያደረገለት ይገኛል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ በበጎ አድራጎት ማህበሩ ግቢ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያንና ሕጻናት የሚመገቡት የአትክልት ምግብ የሚመረተው በዚያው ግቢ ውስጥ ነው። አረጋውያኑ መንቀሳቀስ ካስፈለጋቸውም በአትክልት ሥራዎች ውስጥ መንቀሳቀስና መንከባከብ ይችላሉ፤ ለጤናቸውም ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
ግቢው ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደ ምርምር ማዕከልም እያገለገለ ነው፤ የዶሮ እርባታ ይደረግበታል፤ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የዶሮ እርባታውንና የአትክልት ማምረቱን ሥራ ያከናውኑበታል። ከአንደኛ ዓመት ጀምሮ ያሉ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ ሲወጡ በአትክልቶችና ዶሮዎች ላይ ይሰራሉ። የዶሮዎች ኩስ ለማዳበሪያነት እያገለገለ ነው። አረጋውያኑ፤ በማረም፣ በመኮትኮት የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፤ ሕጻናቱም የተመጣጠነ ምግብ ያገኛሉ።
በግብርና ምርምር በኩልም በአንድ ቦታ ላይ ብዙ ምርት ማምረት እንደሚቻል የሚያመለክት መሆኑን መምህር ዋሲሁን ይናገራሉ። በተለይም በከተማ አካባቢ የዚህ አይነት ዘዴ መለመድ እንዳለበት ያሳስባሉ። ለምግብነት የሚያገለግሉ የአትክልት አይነቶች በፍጥነት ስለሚደርሱ የተጣሉ ዕቃዎች የቆመ እንጨት ላይ በማንጠልጠል ምንም የመሬት ቦታ ሳይዙ በማፈራረቅ ማምረት ይቻላል፤ የምግብ ይዘታቸውም መሬት ላይ ከበቀሉት ያላነሰ መሆኑ ተረጋግጧል።
አትክልቶቹ ከሌላ ቦታ መጥተው ሲተከሉም ሆነ እዚያው ሲመረቱ ጥራታቸው በምርምር የተረጋገጠ ነው። ይህ አይነት አሰራር በበለጸጉት አገራት በስፋት እንደሚሰራበት ተመራማሪው ያስረዳሉ።
በበጎ አድራጎት ማህበሩ ውስጥ ህክምና እና ክብካቤ የሚደርግላቸው ሕጻናት ከጎዳና ላይ እና ከሆስፒታል ተጥለው እንደተገኙ የሚናገሩት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎች መገልገያ ክፍል ሰራተኛ የሆኑት ሲስተር መንበረ ኃይሉ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ሕጻናቱ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ይደረግላቸዋል፤ የማያስፈልጋቸውም አስፈላጊው ክብካቤ ይደረግላቸዋል። ሕጻናቱ ጎዳና ላይ ይኖሩ ከነበረው ሕይወት በስነ ልቦና እና በአካላዊ ጤንነታቸው የተሻለ ለውጥ ተገኝቶባቸዋል።
እንደ ሲስተር መንበረ ገለጻ፤ አንዳንዶቹ ሕጻናት የተገኙት ከሆስፒታል ውስጥ እናቶቻቸው ጥለዋቸው ሄደው ነው። ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕጻናት እናቶቻቸው ሆስፒታል ይወልዱና መጸዳጃ ቤት የሄዱ መስለው ተደብቀው ይጠፋሉ። ሆስፒታሉ ጉዳዩን ለዚህ በጎ አድራጎት ማህበር ያሳውቃል፤ ማህበሩ ተቀብሎ ያሳድጋል።
ወይዘሮ ዘመናይ አስፋው ደግሞ የሰው ለሰው የበጎ አድራጎት ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በ1970ዎቹ ገና የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ይሄ ሀሳብ እንደነበራቸው ይናገራሉ። ጎዳና ላይ ሕጻናት ተርበው ሲያዩ አንጀታቸው እንደሚላወስ ይገልፃሉ። የገንዘብ አቅም ማጣት ያሰቡትን እንዳያደርጉ መሰናክል ሆኗቸው ዓመታትን መዝለቃቸውን ይጠቁማሉ።
ከረጅም ዓመታት ምኞት በኋላ ግን ዕቁብ ገብተው ባጠራቀሙት ገንዘብ አሁን በጅማ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የበጎ አድራጎት ማህበር ለመመሥረት ቤት ተከራዩ። ወዲያውኑም የጅማ ዩኒቨርሲቲ አልጋ፣ አንሶላና ብርድ ልብስ የመሳሰሉትን ጨምሮ የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ አደረገላቸው። አሁን የሰው ለሰው የበጎ አድራጎት ማህበር ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የአካባቢውን ማህበረሰብ እያገለገለ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ዋለልኝ አየለ
9900560 OXOFENIL SOLUTION 2 where to buy priligy in malaysia I started taking Arimidex in July of 2014, after a second diagnosis of Breast Cancer