ማኅበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ መረጃ መለዋወጫ መድረክ፤ ልምድ ማግኛ ሥርዓት፤ ዲሞክራሲ ማጎልበቻና ሀሳብ ማካፈያ ማዕድ ነው። ይህም ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ በጎ ሚና ይጫወታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋሉ የእርስ በእርስ ግጭትን እንዲከሰትም ምክንያትም ይሆናል። ጥላቻ ይሰበክበታል፤ የስድብ ናዳ ይወርድበታል፣ የቃላት ስንጠቃና የሐሜት መድረክ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህም በሀገርና በትውልድ አሉታዊ ጫና ይፈጥራል ይላሉ የዘርፉ ምሑራን ፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያን በአውንታዊ ጎኑ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ በርካታ የሐሰት ዜናዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች የሚለቁ አካላት አሉ፡፡ ከሥርዓት ያፈነገጠ ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዳይፈራ ከማድረጉም ባሻገር የሰዎችን የመኖር መብት ሲጋፉ፣ ሥነ-ልቦናን ሲጎዳ እንዲሁም ሀገርን አደጋ ውስጥ ሲጥል ይስተዋላል፡፡
ለመሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት መቀነስ ይቻላል? ለመቆጣጠርስ ምን መደረግ ይኖርበታል? በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎችን ጠይቀን ሃሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡
በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች በማንኛውም ቦታ ሆነው የተለያዩ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ሰዎች ደስታቸውን፣ ኅዘናቸውን እንዲሁም ሊያገኙት የሚፈልጉትን እውቀት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በቦታና በጊዜ ሳይገደቡ ማንፀባረቅና ማግኘት መቻላቸው ማኅበራዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
መምህር ጌታቸው (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ማኅበራዊ አንቂዎች የተፈጠረውን ዕድል ለጥፋት ከማዋል ይልቅ አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ብሔራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ሰዎችን ማንቃትና አሉታዊ ተፅዕኖውን መቀነስ ይችላሉ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት እያጋጠመ ያለውን ችግር ለመቀነስ ለዜጎች ስለምንነቱና አጠቃቀሙ ማስተማር (ግንዛቤ መፍጠር) እንደ መጀመሪያ ደረጃ መፍትሔ ተድርጎ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ሰዎች ስለ መረጃው ምንጭና ዓላማ በሚገባ ስለሚያውቁ ጉዳቱን መቆጣጠርና መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡
አቶ መልካሙ መኮንን በእንጂባራ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ እሳቸውም የመምህር ጌታቸውን(ዶ/ር) ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ማኅበረሰቡን ማስተማርና ማሠልጠን ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተለያዩ አካባቢዎች አጫጭር የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥልጠና እየሰጡ መሆናቸውን የሚገልጹት መምህር መልካሙ፤ ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመከላከል መሰል ሥልጠናዎችን አጠናክሮ መስጠት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል ወጣቶች ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውን እንዲሁም እራሳቸውን ሊጠቅሙ በሚችሉበት ሁኔታ ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም እንደሚችሉ አውስተው፤ በዚህም እንደ ሀገር ብዙ ጉዳቶችን ማስቀረት እንደሚቻል መምህር ጌታቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
መምህር ጌታቸው (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፤ አሁን ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ከጠቀሜታው በተጻረረና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እየዋለ ጥፋት እያስከተለ ይገኛል፡፡ በዚህም ለዘመናት ተገንብቶ የቆየውን የሕዝቦች ማኅበራዊ ትስስር እንዲሁም የጨዋነት ባሕልን ሲሸረሽርና ገደል እየከተተው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሕዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ የቴሌቪዥን ሚዲያዎች አጀንዳዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ መቀበል የለባቸውም›› የሚሉት መምህር መልካሙ፤ ባላቸው የይዘት ሥራዎቻቸው ላይ የሕዝብን ፍላጎትና ቅሬታ መሠረት ያደረገ አጀንዳ ቀርጸው በመሥራት ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
‹‹ማኅበራዊ ሚዲያ ለዜጎች የሃሳብ ነፃነትን አጎናጽፏል›› የሚሉት መምህር ጌታቸው (ዶ/ር) ነገር ግን ነፃነት ማለት ሠላማዊ ሰዎችንና ሀገርን መጉዳት ማለት አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
በኑሮ ደረጃ፣ በጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ደረጃ እራሳቸውን ወይንም ቤተሰባቸውን መደገፍ በሚቻልበትና ለውጥን በሚያመጣ መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያን ያለ እውቀት መጠቀም ከራስ ባሻገር በሌሎች ላይ ብዙ ጉዳቶችን እንደሚያስከትልም የሚገልጹት መምህር መልካሙ፤ በመሆኑም ለበጎ ዓላማ መጠቀም ይገባል የሚል መልዕክት አላቸው፡፡
በተጨማሪም የሃሳብ ነፃነትን በማይጋፋ ሁኔታ የጥላቻ ንግግርና የሐሰት መረጃ የሚያስተላለፉ ግለሰቦችን በወጣው ሕግ መሠረት መቆጣጠርና ማስተማር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በእውቀትና በግንዛቤ ላይ የተመሠረተ የአጠቃቀም ባሕል በማዳበር ማኅበራዊ ሚዲያን ሌሎችን ሳይጎዳ በአውንታዊ ጎኑ ለበጎ ተግባር መጠቀም እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙት መምህር መልካሙ፤ ዜጎች የሐሰት መረጃዎች ሲደርሳቸው ቆም ብለው ስለጉዳዩ ምንነት ማጣራትና ትክክለኝነት መረዳትና ሃሳቡን መቀበል እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሚለቀቁ መረጃዎችን የመንግሥት ሚዲያዎች እንዲሁም ሌሎች ሚዲያዎች በፍጥነት የመረጃውን ሐሰተኝነት በማስረጃ በማቅረብ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ መሥራትና ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ መምህር ጌታቸው (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ተጠቃሚው የመረጃውን ሐሰትነት ተረድቶ ከመታለልና ለሌሎች ከማጋራት እንደሚቆጠብ ያስገነዝባሉ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን የመከላከል ሥራ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻሉን ማኅበራዊ ሚዲያ ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ በማዋል የሚፈለገው ሁለተናዊ ብልፅግና መሳካት ቀላል ይሆናል፡፡
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30 ቀን 2016 ዓ.ም