ትናንት በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የሠላምና አንድነት ኮንፈረንስ በተካሄደበት ወቅት የተገኙት ሼህ ያሲን አማን በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንደ እምነት አባትም ሆነ እንደ አንድ ዜጋ ብዙ ኃላፊነት አለብን ይላሉ። በተለይም ደግሞ አገሪቱ ወደ ሥልጣኔ መንበር ለማሸጋገር ብዙ ጥረት ይጠይቃል።
በፀሎትና በሥራ መንግሥትን ማገዝ፣ ሰላማችንን መጠበቅ ግድ ይለናል። ስለ ሰላም እና አንድነት ማንም እንዲነግረን መጠበቅ የለብንም፤ ጥቅሙ የራሳችን ስለሆነም ይላሉ። መንግሥትም የሚጠበቅበትን እንዲሠራም አደራ እንላለን። ችግሮች ቢኖሩም በመመካከር እልባት እናበጃለን ባይ ናቸው።
አቶ ዳኜ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የአካባቢን ሠላምና አንድነት መጠበቅ የዜግነት ግዴታ መሆኑንም ልንገነዘብ ይገባል። የልማት መንገዳችንን የሚዘጉትም ሕጋዊ መስመር መያዝ አለባቸው።
የሕግ የበላይነት እንዲከበርም ሁሉም ሰው ከቤቱ ጀምሮ ለሠላም ሊተጋ ይገባል። በአሁኑ ወቅት የገበያው ሁኔታ እጅጉን እየናረ ነው። ይህ ደግሞ የምርት እጥረት ወይንም ደግሞ የተለየ ችግር ሆኖ አይደለም። ይሁንና አገሪቱ ወደ ምጣኔ ሀብት ቀውስ እንድትገባ እና ዜጎች እይታቸውን ወደ ፖለቲካ እንዲያዞሩ የታሰበ ሴራ ነው ይላሉ።
የወጣቶች ሥራ አጥነት ተበራክቷል። ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲጠቀሙ ቢፈቅድም ካርታ አስይዙ እየተባለ ነው። በአካባቢው ደግሞ ካርታ እየተሰጠ አይደለም። ይህ ሊስተካከል ይገባል።
በሌላ መንገድ ደግሞ በውሸት መረጃ የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን ላይ መንግሥት ሊቆጣጠራቸው ይገባል የሚል እምነት አላቸው። ከዚህ በተረፈ «ቄሮ፣ ቃሬ፣ ጃርሳ እና ጃርቲ» ወይንም ወጣቶችና አዛውንቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
የለገጣፎ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርሃኔ መገርሳ ሠላም ሲኖር ነው ሁሉ ነገር ሊኖር የሚችለው የሚል አቋም አላቸው። በተለይ ደግሞ በሊግ የተደራጁ ሴቶች ይመካከሩ ነበር።
ሴቶች ሥራ አጥ ሆነዋል። ቢደራጁም ሥራ አይሰጣቸውም። ከላይ የሚመጡ ትዕዛዞች እና አሰራሮች በአግባቡ አይተገበሩም። በከተማዋም ብዙ ቤቶች በራቸው ተዘግተው ተቀምጠዋል። ይህ ለምን ለድሃ አይሰጥም ሲሉ ይጠይቃሉ። የውሃ እና መብራት ችግርም ልማት እያደናቀፈ መሆኑን ይናገራሉ።
በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልቾ በቀለ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ በዕለቱ በለገጣፎ የተካሄደው የሠላምና አንድነት ኮንፈረንስ በመላ ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች የሚከናወን ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ በክልል የገጠር ቀበሌዎች የሚከናወን ይሆናል።
አቶ ጫልቾ እንደሚሉት፤ የለውጥ ኃይል ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከመጣ በኋላ በርካታ ድሎች ተገኝተዋል። ይህን ደግሞ በምጣኔ ሀብት አስደግፎ ማጠናከር ይገባል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን አሻራ ማኖሩን ጠቁመዋል። ከአንድ ዓመት በፊት በተጀመረው የለውጥ ጉዞ የኦሮሞ ሕዝብ በተወሰነ መንገድም ቢሆን ተጠቃሚ ሆኗል።
ለአብነትም በአሁኑ ወቅት መንግሥትን የሚገዳደሩ አካላትን ጨምሮ ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ከ45ሺ በላይ ታራሚዎች ከእስር ነፃ የወጡት አገሪቱን በለውጥ ጉዞ እየመራ ያለው መንግሥት ነው። በዲፕሎማሲ ረገድም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ከኤርትራ ጋር የነበረው የጦርነት ቀጣና በሠላም እንዲታደስ ተደርጓል። ከአረብ፣ ኤዥያ፣ አውሮፓ እና ሌሎች አህጉራትና አገራት ጋር ያለው ወዳጅነትና የተጀመረው ግንኙነት በእጅጉ የሚያኮራ ነው። ሰብዓዊ መብት እንዲከበርም ትልቅ አበርክቶ መኖሩን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በአገሪቱ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ በበቂ ደረጃ ምላሽ ባያገኝም ለውጦች መኖራቸውን ያብራራሉ። ይህም የሆነው አንድነት ማጣት፣ በምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ላይ ተመሳሳይ አቋም ማጣት እና በተለያዩ የፖለቲካ እይታ ላይ ተመስርቶ መከፋፈል፣ ጠላትን ከመመከት ይልቅ እርስ በእርስ ጥቃት ማድረስ፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ አለመስጠትና የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸውን ይናገራሉ። አሁንም ቢሆን በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መሰራት አለበት ይላሉ።
በሌላ መንገድ ደግሞ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በእምነት ተቋማት መካከል ግጭቶችን መፍጠር፣ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ መሞከር፣ የለውጥ መሪዎችን መግደል፣ ከቦታ ቦታ ዜጎችን ማፈናቀልና የመሳሰሉ ድርጊቶች ለውጡን ለመቀልበስ የተዘረጉ መረቦች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በክልሉ ውስጥም የሕዝቡን ጥቅም ሳያስከብሩ ለግል ጥቅም እርስ በእርስ መጋጨትና የሽፍታ ደርዞችን መከተል አደገኛ አካሄዶች መሆናቸውን አብራርተዋል። ለውጦቹንም ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገርም የሕዝቡ ጥረትና ድጋፍ ትልቅ ሚና እንዳለው በመጠቆም ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ የሠላምና የልማት ኮንፈረንሱ አገሪቱን መፃኢ ዕድል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታስቦ የተከናወነ ነው። በዚህም ሂደት ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ሆኖም ለውጡን ያልተዋጠላቸው ችግር እየፈጠሩ ነው ይላሉ።
ይህንንም ጠንካራ አቋም በመያዝና ሕዝቡን ከለውጥ አመራሩ ጎን በማሰለፍ ማስተካከል ይገባል ባይ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች፣ ሴቶችና መላው የከተማ ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ትኩረት ያደርጋል። በከተማዋ የሚስተዋሉ ሕገወጥነቶች፣ የመሬት ወረራ እና የመልካም አስተዳደር እጦት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር