አዲስ ዘመን ድሮ

እያዝናና የሚያስተምረውን፤ ታሪክን የኋሊት የሚተርከውን፣ የጊዜን ዥረት ኩልል አድርጎ የሚያስቃኘውን፤ የዘመንን እድገትና ሥልጣኔ ዓይን ከሰበከት እያገላበጠ የሚያሳየውን ወዘተ ″አዲስ ዘመን ድሮ″ ዓምድን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናልና መልካም የኋሊት ምናባዊ ጉዞ።

አንጐልና አልኮል

አንጎል የተባለው የእግዚአብሔር ታላቅ ስጦታ ደማዊት ፍጡር ላላቸው ሰዎች የታደለ ሲሆን፣ የበለጠው የሀሳብ ማፍለቂያ የጥበብ ምንጭ የሆነው አንጎል በአምሳለ ሥላሴ ለተፈጠረ ሰው ለተባለው ፍጡር የተሰጠ መሆኑን አንዘነጋም።

አንጎል የብልቶች ጠቅላይ ቢሮ ስለሆነ እንደ ትልቅ የስልክ ቸንትራል ብዙ የደም መዘዋወሪያ መስመሮች ስላሉበት ከሰውነት አንድ ብልት እክል ያገኘው እንደ ሆነ ወዲያውኑ በስልክ ለአንጎል ያስታውቅና በአንጎል ከፍ ያለ ሀሳብ ተደርጎበት አስፈላጊው ሕክምና ይደረግለታል።

እንዲሁም የአንጎል ደጋፊ ልብ የተባለ አስተዋሽ ስላለ፤ መቸም ፍጡር ሆኖ የማይሳሳት የለምና አንጎል የዘነጋው ነገር ቢገኝ ልብ አስታውሶ አዕምሮ በተባለው ንቁ ተላላኪ አማካኝነት ለአንጎል ያስታውቅና ጉዳዩ በልብ መዝገብ ተፅፎ ወጪና ገቢ ሆኖ አስፈላጊው እንዲፈፀም ይታዘዛል።

በጠቅላላው የሰው አንጎል በበታቹ ለሚተዳደሩ ብልቶች ከክፉ ነገር ተጠብቀው እንዲኖሩ በጥብቅ እየተቆጣጠረ አስተዳዳሪ ከመሆኑ በላይ ላገሩና ለወገኑ አሳቢ ከአልኮል ርቆ በትክክል የሠራ እንደሆነ ወገኑንና አገሩን አኩሪ ጠላት አሳፋሪ የማይደፈር ምሽግ ቦታ የሃሳብ ባሕር የካልቸርና የኢንዱስትሪ ምንጭ ተብሎ በተሰየመ ነበር።

አልኮል የተባለው መጠጥ ግን የአንጎል ጠንቀኛ ተቃራኒ ለሰው ልጅ ተምሮ እንዳልተማረ፣ ሠልጥኖ እንዳልሠጠነ፤ ተፈጥሮ እንዳልተፈጠረ፤ የሰው ሀብት ዕድለ ቢስ አድርጎ በብርቱ ገመድ እየሳበ ወደ ጥፋት የሚመራ ትልቅ በሽታው ነው።

ስለዚህ አንጎልና አልኮል ይህን ያህል መራራቅና ጠብ ያላቸው መሆኑን እያወቅን ሁለቱ ጠበኞች እንደ መለያየት ፈንታ ልናቀራርባቸው ይገባናልን?

(ገብረ መድኅን ባሕታ፣ አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 22 ቀን 1951 ዓ·ም)

የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት የሚያደርጉት ልዩ ስብሰባ

ባለፈው ማክሰኞ በኒውዮርክ በተሰጠው ማስታወቂያ መሠረት የአፍሪቃ ነፃ መንግሥታት መልእክተኞች፤ እየመነመነ ስለሚሄደው ስለ አልጄሪያ ሁናቴ ለመነጋገር በሚመጣው ነሐሴ ወር ቀደም ብለው በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞኖሮቪያ ልዩ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ማስታወቂያውንም ያሰሙት በአሜሪካ የቱኒዚያ አምባሳደርና የተባበሩት መንግሥታት መልእክተኛ የሆኑት ሙሴ ሞንጊ ስሊም ነበሩ። ሙሴ ስሊምም ማስታወቂያውን ያሰሙት በአሜሪካ ተቀማጭ ከሆኑት ከአፍሪቃ መንግሥታት እንደራሴዎች ጋር ለሁለት ሰዓት ያህል ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።

እርሳቸውም ለጠያቂዎች መልስ ሲሰጡ፣ የአልጄሪያ ሁኔታ እየተናቀና እየመነመነ በመሄዱ፤ የአፍሪቃ መንግሥታት በጥልቅ እንዲያስቡበት አስፈላጊ መስሎ ታይቶናል። ስለዚህ በዚህ ስፍራ ሠላም እንደገና የሚመሠረትበትን መንገድ ለመመካከር እንዲሰበሰቡ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ሚስተር ስሊም እንዳሉት የሙሴ ፌርሃት አባስ የአልጄሪያ ነፃ መንግሥት አባል የሠራተኞች ክፍል ሙሉ አባል ነበር። የአፍሪቃ ነፃ መንግሥታት ስለአልጄሪያ የሚያደርጉት ስብሰባ ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ ሲሆን፣ ስብሰባው አልጄሪያ በሚመጣው መስከረም የሚደረገው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ተካፋይ እንድትሆን በአፍሪቃና በእሲያ የተባበሩት መንግሥታት መልእክተኞች መካከል የነበረውን ክርክር እንደማይነካ የታወቀ ነው።

በዚህ ስለ አልጄሪያ ጉዳይ በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞኖሮቪያ በሚደረገው ልዩ ስብሰባ የሚገኙት የአፍሪቃ ነፃ መንግሥታት ጋና፣ ጊኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሊቢያ፣ ላይቤሪያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒሲያ፣ ሱዳንና የዓረብ አንድነት ሪፐብሊክ ናቸው።

(አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 20 ቀን 1951 ዓ·ም)

የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ሊለወጥ የቻለባቸው ምክንያቶች

የትምህርት ፖሊሲው [የደርግ] ሊቀየር የቻለው:-

በይዘቱ በቀለምና በቲዎሪ ላይ ማዘንበሉ፤ በአቀራረቡ ቃለ-ነቢብና ስንኩል በመሆኑ፤ በትምህርት፣ በሥልጠና፣ በምርምርና በልማት እንቅስቃሴዎች መካከል ተገቢው ተስተጋብሮት የሌለው በመሆኑ፤ ችግሮችን የመፍታት አቅም ባለማጎልበቱ፤ የመመራመርና የፈጠራ ዝንባሌዎችን ባለማበረታቱ፤ ጥራትና ብቃት ያለው ዜጋን ከማፍራት ይልቅ የተማረ ሥራ አጥነት እንዲስፋፋ በማድረጉ ነው።

(አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 11 ቀን 1986 ዓ·ም)

የቀይ መስቀል በዓል የጃንሆይ ሜዳን ያደምቃል

ግንቦት 22 እና 23 ቀን 1951 ዓ·ም አዲስ አበባ የሚገኘው የጃንሆይ ሜዳ በአንድ ልዩ ጥበብ እንደ ተደረገ ሁሉ ወደ አንድ ደማቅ መደሰቻነት ይለወጣል። ይህ ልዩ ጥበብ ግን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና በአዲስ አበባ የሚገኙ የልዩ ልዩ ዓለም ነገድ ሕዝቦች ትጋትና ጥንካሬ የመላበት ሥራ ነው።

በዚህ ቦታ ስለ ቀይ መስቀል ጥቅም ለሚደረገው ኢንተርናሺናላዊ ሥነ-በዓል ሁለቱንም ቀናት ከቀኑ በ5 ሰዓት ሁለቱም በሮች ክፍት ይሆናሉ።

የኢትዮጵያና የውጭ አሕጉር እቃዎች እንደዚሁም የሥነ-በዓሉን አክባሪዎች ድካም የሚያበረታታ ጣፋጭ ምግብና ጥማቸውንም የሚያረካ መጠጥ የሚሸጥባቸው ልዩ ልዩ የሆኑ 12 ዳሶች በጃንሆይ ሜዳ ላይ በተለይ ተሠርተው ይዘጋጃሉ።

በብዙዎቹም ዳሶች ውስጥ ዘወትር የታወቀ የዕድል መሞከሪያ ዕጣዎች ይገኛሉ። የዳንማርክ ሰዎች የሆኑት የከተማው ነዋሪዎች በዕጣዎቹ ውስጥ በቆርቆሮ የተዘጋጁ የዳንማርክ ምግቦች ያገባሉ። ለዚህ የሚያገለግሉት ዕጣዎች የዳንማርክ ሀገር ሰዎች በሆነው በሥነ-በዓሉ ላይ በሚገኘው ዳስ ውስጥ ይገኛሉ። በዕጣው የሚገኘው እቃ የሚወሰደው እሁድ ከቀትር በኋላ በ11 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ነው። እድለኛው ባለ ዕጣ ለጊዜው በቦታው ባይገኝም ዳንማርክ ቆንስላ በስልክ ቁጥር 4513 ጠይቆ ያገኘውንም እቃ ከዚያው ከቆንስላው ሊወስድ ይችላል።

እንደዚሁም ሌላ የዕድል መሞከሪያ ዕጣ በግሪኮች ዳስ ውስጥ ይገኛል። በእነዚህ ዕጣዎች የሚገኙትን እቃዎች ከሕንድ ቤተ ሰቦች ዳስ ውስጥ ሊወስዱ ይችላሉ።

(አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 15 ቀን 1951 ዓ·ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You