-የቻይና የቴክኒክና ሙያ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እያገዙ ነው
ለግብርና መዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት ታሳቢ በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ፣ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ያካተተና ተሞክሮን ባገናዘበ መንገድ የግብርና ባለሙያዎች የትምህርትና ስልጠና መጽሃፎችን የመከለስ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ፤ ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር የሚተገበረው ስራ ስድስት የግብርና ባለሙያዎች የትምህርትና ስልጠና መጽሃፎችን ጥራትና ይዘታቸውን ማሳደግ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም ሁለቱ ታትመው ለስርጭት ዝግጁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የመጽሃፎቹ ህትመት በግብርና ስራ ትምህርት የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ጥራት ያለው ስልጠና ለመስጠት አስተዋጽኦው የላቀ ይሆናል ሲሉም ተስፋቸውን ተናግረዋል፡፡
መጽሃፎቹን በመገምገም ማሳደግ እንዳለበት በመታመኑ ወደ ስራ ተገብቷል ያሉት አቶ ሳኒ፤ ለዚህ አስፈላጊውን የቴክኒክ፣ የባለሙያ፣ የህትመትና ስራው ቻይና አገር እንዲታተም የሚያስፈልገው ወጪ በቻይና መንግስት ተሸፍኗል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚያስፈልጉ የታክስና ሌሎች ወጪዎችን ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈኗል ብለዋል፡፡
ቻይናውያን የተሻሉ የሚባሉ የኮሌጅ መምህራኖችን ልከው በግብርና ኮሌጆች ተመድበው እየሰሩ እንደሚገኙ በመጠቆምም፤ የግብርና ባለሙያዎቹ ዘመናዊ የግብርና ስራ ለማካሄድ መሰረቱ የግብርና ባለሙያዎች ክህሎትና ዕውቀት ነው የሚል ግንዛቤ በመጨበጣቸው ከኢትዮጵያ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እየተሰጠ ያለውን የትምህርትና ስልጠና መጽሃፎችን የመከለስ ስራ ሰርተዋል ብለዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ፣ዓለም አቀፍ ልምዶችን ያካተተና ተሞክሮን ያገናዘበ እንዲሆን የሚያስችል ስራ በትብብር ለመስራት ከቻይና መንግስት ጋር በመግባባት አስፈላጊውን ገንዘብ በመመደብ በሰብል ልማት፣ በእስሳት ሃብት ልማትና በተፈጥሮ ሃብት በመከፋፈል መጽሃፎቹን የመከለስ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ይህ ለግብርና መዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ግብርና መዘመኑ ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል፣ የግብርና ምርት ጥራት እንዲሻሻል ያደርጋል፣ በዓለም ገበያ የሚፈለግ ምርት እንዲያመርት ያስችላል፡፡
ወደፊት የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች መዳረሻ ከሚሆኑ አገራት ቻይና አንዷ ትሆናለች ብለን እንገምታለን የሚሉት አቶ ሳኒ፤ የቻይና ህዝብ ቁጥርና የመግዛት አቅም እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወደፊት ለምርቶቻችን የተሻለ ዋጋ የሚከፍል ገበያ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
አሁንም ሰሊጥ ወደ ውጭ በመላክ ቻይና በገዢነት ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ጠቁመዋል፡፡ ስለዚህ ምርቶች እንዲያድጉና እንዲሻሻሉ የሚያደርጉት እገዛ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ የግብርና ኮሌጅ ላይ መሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ ውጤቱም የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያመጣ ነው የተናገሩት፡፡
ቻይና በግብርና አደጉ ከሚባሉ አገራት አንዷ ናት፡፡ በአነስተኛ ማሳ ላይ የተመሰረተውን ግብርናን በማዘመን በአለም ከሚታወቁ አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡ በኢትዮጵያ ግብርና 95 በመቶ የተመሰረተው በአነስተኛ አርሶ አደር ማሳ ላይ ነው፡፡ ሰፊ የመንግስት የኤክስቴንሽንና የክህሎት አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
በመንግስት እጅ ያሉ የግብርና ማሰልጠኛ ኮሌጆች ብቃት ያለው ስልጠና እና ትምህርት እንዲሰጡ በመደገፍ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ከ15 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ለቻይና መንግስት ጥያቄ አቅርቦ ነበርም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና የኢኮኖሚ እና የንግድ አማካሪዋ ሊዮ፤ ቻይና ለግብርና እና ለገጠር ልማት የምትሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፤ የግብርና እና የገጠር ልማት ጉዳይ ቻይና ከተለያየ አገራት ጋር በምታደርጋቸው ትብብሮች አስፈላጊ፣ አንዱ እና ወሳኝ መስክ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በተለያየ መስክ ትብብር እየተደረገ ይገኛል ያሉት ሊዮ፤ በግብርና መስክ የሚካሄደው የግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና መጽሃፍ በዘርፉ ብቃት ያላቸው 20 የቻይና የቴክኒክና ሙያ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያግዙ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የቻይና መንግስት የፌዴራልና የክልል የግብርና ዘርፍ ሃላፊዎችን እና ባለሙያዎችን ወደ ቻይና በመጋበዝ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በአጫጭር ስልጠናዎች፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ በማሰልጠን ላይ እንደምትገኝ አስታውሰዋል፡፡
በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያ ለገጠማት ድርቅና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የቻይና መንግት እገዛ ማድረጉንም አማካሪዋ ተናግረዋል፡፡ ድርቅና የተለያዮ ስጋቶችን በመቋቋም ረገድ በግብርና መስክ አገሪቱን እያገዘች መሆኗንም ነው የጠቆሙት፡፡ ኤልኒኖ ከተከሰተበት ከ2015 ጀምሮ እስካሁን 300 ሚሊዮን ዮአን እና በአለም አቀፍ የምግብ ድርጅት አማካኝነት በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 14 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉንም አማካሪዋ ሊዮ አመልክተዋል፡፡
የቻይና ባለሃብቶች በግብርና ዘርፍ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰማሩ እና ዘርፉን እንዲያሳድጉ እያበረታታች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በግብርና እና በተለያየ መስኩ ቻይና ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል፡፡ በግብርናው መስክ የሁለቱ አገራት የትብብር መስክ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷልም ብለዋል፡፡
ቻይና ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ የወሰዷቸውን የለውጥ እርምጃዎችን በመደገፍ ላይ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
ዘላለም ግዛው