“ኢትዮጵያ የመስኖ ልማትን የትኩረት ማዕከሏ ማድረግ አለባት”በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የመስኖ ኤክስፐርት

የዛሬው የዘመን እንግዳችን በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር) ናቸው፤ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእርሻ ምህንድስና ትምህርት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው ተመርቀዋል፤ ከተመረቁም በኋላ አነስተኛ ግድቦችን ሰርቶ ለመስኖ ልማት ማዋል ላይ ተግባራዊ አድርገዋል። ዲግሪያቸውን እንደያዙም በአማራ ክልል በዘርፉ የጥናትና ዲዛይን ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል። በስምንት አነስተኛ ግድቦች ጥናት ላይ ተሳትፈዋል። በዛው በአማራ ክልል በወሎ የሲሪንቃ ምርምር ማዕከል በውሃ መስኖ ልማት ምርምር ላይ ለሶስት ዓመት ያህል ሰርተዋል።

እንግዳችን፣ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ ወደ ሕንድ አቅንተው ከውሃ ጋር በተያያዘ ሩርኪ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃ ፍሰት ምህንድስና (በሃይድሮሎጂካል ኢንጂነሪንግ) ተምረዋል። ከሕንድ ከተመለሱ በኋላ በወቅቱ በውሃ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ገብተው ለሁለት ዓመት ያህል አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ የመስኖ ጥናቶችና የልማት ሥራዎች ላይ ከሰሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የማስተማር ስራን ተቀላቅለው እስካሁንም በማስተማር ላይ ናቸው። ዩኒቨርሲቲ የመምጣታቸው ምስጢር ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት ጭምር በመሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ኢንጂነሪንግ ምህንድስና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ሰሩ – የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር በለጠ ብርሃኑ።

በተለይ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ ገለልተኛ የሆነ የሳይንሳዊ ቡድን በየሀገራቱ ሲቋቋም የዚያ ቡድን መሪ ሆነው ስራ የጀመሩ ናቸው። እኤአ ከ2017 ጀምሮ እስካሁን ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ሲሆኑ፣ የድርድሩም አባል ሆነው አገልግለዋል። ታድያ በተለይ ከመስኖ ልማት አኳያ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለው ጅምር ሥራ እንዴት ይገለጻል? በዘርፉ ያላትስ ምቹ ሁኔታ ምን ይመስላል? ስንል ከእኚሁ ጉምቱ ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በመስኖ ማልማት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እና ሀብት አላት ይባላል፤ በዚህ ምቹ ሁኔታና ሀብት መጠቀም ያለባት እንዴት ነው?

በለጠ (ዶ/ር)፡- በመጀመሪ ደረጃ ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት አበክራ ካልሰራች በስተቀር ሕዝቧን በትክክል መመገብም ተሻጋሪ በሆኑ መልኩ ማደግም አትችልም። መሰረታዊ ከሚባሉት ከየትኞቹም አገሮች ከሰሩትና ካደጉት አንጻር የመጀመሪያ ትኩረታቸው የምግብ ሰብል ማምረት ነው። ለዚያ ደግሞ በመስኖ ማልማት ወሳኝ ነው።

እስከ ዛሬ ድረስ እንደ አገር ግብርናችን ሲከተል የነበረው በዝናብ ማብቀልን ነው። አሁን ያለው የአየር ንብረት መለዋወጥ ደግሞ በዝናብ ብቻ ተንጠላጥሎ ለማደግ የሚያስችል አይደለም። ሰለዚህ በዝናቡ ብቻ እያበቀልን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እያረስን መኖር ወደማንችልበት ሁኔታ ደርሰናል። ሕዝባችንም አድጓል። በዝናብ የሚመረተው ምርታማነትም በአንጻሩ ቀንሷል። ስለዚህ የግድ ወደመስኖ ልማት መምጣት ያስፈልገናል።

ወደመስኖ ልማት እንምጣ ሲባል መታየት ያለበት አንዱና ዋናው ነገር ምቹ ሁኔታ ነው። የመጀመሪያውና ቀዳሚው ምቹ ሁኔታ ደግሞ መሬት ነው። ምክንያቱም መስኖ እናልማ ሲባል የሚለማበት መሬት ነው። ኢትዮጵያ ለመስኖ ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚነገረው ለመስኖ የሚመች ቦታ የላትም በሚል ነው። ይህ ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።

ምክንያቱም መስኖ ምንድን ነው? ስንል የሚመረትበት ቦታ፣ እርሻ የሚሰራበት ቦታ ውሃ ሲኖር ነው፡። ውሃ የምናደርስበት ቴክኖሎጂ ካሰብን ሁሉም የእርሻ መሬት የመስኖ መሬት መሆን ይችላል። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ስንወስደው ተዳፋቱ፣ ጉብታው ይለያያል እንጂ የግብርና ሚኒስቴር የሚያወጣው መረጃ ወደ 74 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማለትም በአጠቃላይ ገጸ ምድራችንን ስንመለከተው ወደ 112 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ነው። ከዚያ ውስጥ 74 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወይም ደግሞ 70 በመቶ አካባቢ የሚለማ ለእርሻ የሚሆን መሬት ነው ማለት ነው። በዝናቡም እንኳ እስካሁን ሙሉ በሙሉ አላረስነውም። የየዓመቱ ሪፖርቶች መለያየቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ግን እስከ ዛሬ ያሉት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ ከ16 እስከ 20 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማታችንን ነው። ይህ ከ74 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ገና ብዙ ያላለማነው መሬት እንዳለ የሚሳይ ነው።

ስለዚህ ከመስኖ ልማት አንጻር ስንመለከት ይህን ሁሉ መሆን ይችላል። ግን ቴክኖሎጂው ይወሳሰባል። እንዲያው ቀለል ያለ ቴክኖሎጂ የምንለው በቀጥታ ሊለማ የሚችለው ሲሆን፣ በዚህ ስንሔድ እስከ ሃያ ሚሊዮን ሔክታር መሬት እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት የገመትነው እስከ 21 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ብለን ነው። በዚህ መልኩ የተለያዩ ጥናቶች የገመቱ አሉ። ይህ ማለት በጣም ትልቅ የቴክኖሎጂ ጉዳይ ሳንጠየቅ የሚለማ መሬት ማለት ነው። ይህ ከመሬት አንጻር በመደበኛ የውሃ ፍሰት ሊለማ የሚችል መሬት ነው። በዚህ መልኩ እስከ 20 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ማልማት እንችላለን። ይህ ከመሬት አንጻር ነው። በመሰረቱ ሁልጊዜ የመስኖ ልማት ሲነሳ ግራና ቀኝ የሚታዩት ሁለቱ መሬትና ውሃ ናቸው። ከዚህ አንጻር ሁለተኛ ምቹ ሁኔታ መታየት ያለበት ውሃ ነው። ኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ የሚገለጽ የውሃ ሀብት አላት።

በእርግጥ የተለያየ እሳቤ አለ። አሁን ባለው ሁኔታ ከሆነ የውሃ ምንጭ እንጂ የውሃ ሀብት አይደለም የሚኖረን የሚል እይታ አለ። ምክንያቱም ስላላጠራቀምነው፣ ስላልያዝነውና ስላልተቆጣጠርነው ማለት ነው። በአብዛኛው ውሃችን የሚፈሰው በክረምት ወቅት ነው። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የውሃ ምንጭ በክረምት ወቅት የሚገኝ ነው፡። በበጋ ወቅት የምናገኘው አነስተኛ ውሃ ነው። ስለዚህ በየጊዜው መጠቀም አንችልም ማለት ነው።

ሁለተኛው አብዛኛው ወንዞቻችን ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። ስለዚህ ውሃን ካላቆርን፣ ካልያዝን በግድብ ካልተቆጣጠርን በስተቀር ውሃችንን የውሃ ሀብት አይሆነንም። ውሃ ሀብት እንዲሆን በግድብ መያዝ አለበት። በግድብ ከያዝነው አንጻር ሲታይ በጣም አናሳ ነን። አሁን ባለን አነስተኛ መለስተኛ ግድቦች (በየዓመቱ ታዳሽ የሚሆነው ማለት ነው) በግድብ የያዝነው ወደ 40 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ብቻ ነው። በአጠቃላይ በገጸ ምድር ወደ 122ም 134ም ቢሊዮን ሜትር ኪየብ ውሃ አለን የሚሉ መረጃዎችና ማስረጃዎች አሉ። በትንሹ በተነገረው ማለትም በ122ቱ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንውሰድና ከዚህ ውስጥ ደግሞ አጠራቅመን እኛ በፈለግነው መንገድና በፈለግነው ሰዓት ልንጠቀምበት የምንችለው ብለን ያስቀመጥነው 40 ሚሊዮኑን ብቻ ነው። ስለዚህ በብቃት ሀብት አለን ማለት አያሰኝም እንጂ ሀብታችንን ማደራጀት ከቻልን ለመስኖ ልማት ለማሳደግ የውሃ ሀብትም አለን። ነገር ግን የመገደብና የመሰብሰብ ጥያቄ አለበት እንጂ ውሃማ አለን። ስለዚህ ውሃ እና መሬት ካለ መስኖ አለ። የመስኖ ልማት ለማልማት የሚያስፈልጉት ምቹ ሁኔታዎች አሉን።

ከዚያ በተጨማሪ ወጣ አድርገን ስንሄድ ሌላ የሚያስፈልገው ምቹ ሁኔታ ምንድን ነው? ሲባል የሰው ኃይል ነው። እኛ ደግሞ የሰው ኃይል አለን። የእርሻ ልማት ስራችንን በተለይ በመስኖ ስናደርገው በጣም በርካታ ሰራተኞችን የሚይዝ ይሆናል። አንድ አነስተኛ የግለሰብን የመስኖ ቦታ ብንወስድ በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ነው። ለምሳሌ መሬቱን ከሚመርጠው ባለሙያው ጀምሮ ዘር የሚመርጠው የአግሮኖሚ ባለሙያ፣ ስለአፈር የሚያጠናው ባለሙያ፣ የውሃውን ፍሰት የሚቆጣጠረው ባለሙያ ከዚያ ደግሞ ወደገበያ የሚወስደው የገበያ ባለሙያን ጨምሮ በርከት ያሉ አካላትን የሚያሳትፍ በመሆኑ ሰፊ የስራ እድል ያለው መስክ ነው። ይህ ሁሉ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት አገር ናት። እነዚህን ባለሙያዎች ዩኒቨርሲቲዎቻችን በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ። በብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የመስኖና ተያያዥነት ያለውን ባለሙያ ያስመርቃሉ፡። ስለዚህ ሌላው ምቹ ሁኔታ የሰው ኃይል ነው። ነገር ግን ትልቁ ችግር የሚባለው በአግባቡ ያለውን የሰው ኃይል ማሰማራት ላይ ነው።

በሕዝብ ስርጭት አንጻር ስንመለከተው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጣት ገና በጉልምስና የእድሜ ክልል ውስጥ ያለ ነው። አሁን ያለንበት አማካይ እድሜ ስታቲስቲክ እንደሚያመለክተው፤ ወደ 18 ዓመት ነው። ይህ ማለት ደግሞ አብዛኞቻችን ልጆች ነን ማለት ነው። ብዙ ወጣቶች አሉ ማለት በብዙ ማምረት እንችላለን ማለት ነው። ይህ አንዱ መታየት የሚችል ምቹ ሁኔታ ነው።

በሶስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ሊያሰሩ የሚችሉ ፖሊሲዎች አሏት። ከሕገ መንግስቱ ጀምረን እየወረድን ብንሄድ እንድናለማና በምግብ ራስን መቻል እንድናመጣ የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች ናቸው። የበጀት ቀመር ሲደለደል ሁሉ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል ነው። ብዙ ጊዜ ከጤና ቀጥሎ ትኩረት የሚሰጠው የምግብ ሰብል ማምረት ነው። ይህን ሁሉ ስንመለከት ምቹ ሁኔታዎች ብዙ ናቸው የሚያስብለናል። ከእነዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት ምቹ ናት።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ያላትን የመስኖ ምቹ ሁኔታ በአግባቡ እየተጠቀመች ነው ማለት ይቻላል? ካልሆነስ ያለባት ተግዳሮት ምንድን ነው? መፍትሔውስ?

በለጠ (ዶ/ር)፡– ኢትዮጵያ ውስጥ በመስኖ ማልማት የሚያስችል ትልቅ እድል እያለ አልተጠቀመችበትም። የሚጠበቅብንን ያህል አላመጣነውም። እስከዛሬ የነበረን አመለካከት ከውጭም የሚመጡ አማካሪዎቻችን ጭምር የእኛን ውሃ ለመጠቀም እንዳንችል ከመፈለግ አንጻር የሚመክሩን በአብዛኛው በዝናብ እንድናመርት እንጂ ወደ መስኖ ልማት ስራ ውስጥ እንድንገባ አይደለም። ወይም እዚያ መስመር ውስጥ እንድንገባ አልገፉንም። እኛም መረዳታችንን አስፍተን የመስኖ ልማታችንን የአመለካከት፣ የግንዛቤ አቅጣጫ መቀየር እና ማስተካከያ ስላላደረግን ነው። በአብዛኛው በእኛም ዘንድ ያለው ግንዛቤ ኢትዮጵያ በዝናብ ውሃ መልማት ትችላለች የሚል ነው። ስዘሊህ ዝግጅት አድርጎ መስኖን ማልማት እስካሁን ድረስ አልተቻለም። ይህ የአመለካከት ችግር መኖሩን የሚያሳይ አንደኛው ጉድለት ነው። አመለካከታችን በተሳሳተ መረጃ ተዛብቷል። ከዚህ የተነሳ ጠንክረን አልሄድንበትም።

በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው አስቀድመን እንዳልነው የውሃ ምንጫችን ዝናብ ነው። መስኖ ልናለማ የምንችለው ደግሞ በአብዛኛው በግድብ ነው። እኛ ግን የመስኖ ፕሮጀክቶቻችንን እያለማንበት ያለው በወንዝ በጠለፋ ነው። በወንዝ ጠለፋ ደግሞ ጠንካራ የሆነ እና ትልቅ ልማት ማልማት አይቻልም፤ ስለዚህ ማልማት የምንችለው በግድብ ውሃውን ይዘነው ነው እንጂ ግድብ ሳንሰራ፣ በክረምት የሚዘንበውን ውሃ ሳንይዘው ፈስሶ ካለፈ በኋላ ምንም ማድረግ አይቻልም። ምክንያቱም የመስኖ ልማት በዋናነት የምናጠጣው በበጋ ወቅት ነው። በበጋ ወቅት ደግሞ ያለንን ውሃ ትንሽ ነው። በዚያን ወቅት ያለን 30 በመቶ የሚሆን ውሃ ነው። እሱም ቢሆን በተለያየ ቦታ ተሰራጭቶ የሚገኝ ነው። 70 በመቶ የሚሆነው ውሃችን በክረምት ወቅት ፈስሶ ሄዷል። ውሃውን ስላልያዝነው መስኗችንን አቀላጥፈን ማልማት አልቻልንም።

አሁንም አለን የምንለው የመስኖ ልማት ጠንካራ ሆኖ ቀጣይነት የያዘው ግድቦች ያሉበት ቦታ ነው እንጂ በወንዝ ጠለፋ የሰራናቸው ለአንድ ቢበዛ ለሁለት ዓመት ያገለግሉ እንደሆን እንጂ በቀጣይ የሚጠፉ ናቸው። ምክንያቱም የውሃው ፍሰት ተለዋዋጭ ነው። ቋሚ ነገር የለውም። በወንዝ ላይ ደግሞ የምናለማው ልማት ከላይኛውና ከታችው የማኅብረሰብ ክፍል ተጠቃሚነት አንጻር ግጭት ይፈጥራል። ከዚያ የተነሳ አንደኛው የላይኛው ተጠቃሚ የታችኛውን መጥለፊ መሳሪያ መጥቶ ያፈርሰዋል። በማኅበረሰባችንም አካባቢ እየፈጠረ ያለው ግጭት ነው። ይህ በራሱ አንደኛው ተግዳሮት ነውና ግድብ መስራት የሚለው አንድ እይታ ያስፈልገዋል። ስለሆነም በዋናነት መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ግድብ መስራት ነው።

ግድብ መስራት ስንል የቀደሙት አነስተኛ ልምዶቻችን ፈተና ውስጥ ጥለውናል፤ የብዙ ሰዎችን ስሜትም አወላግዷል። ላለፉት 15 ዓመታት አካባቢ ወደኋላ ተመልሰን ስንመለከት ወደ አስር የሚሆኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች የግድብ ስራቸው በአንድም በሌላም መልኩ ሳይጠናቀቅ ውሳኔ ሰጪዎችንም ሆነ ባለሙያዎችን ትንሽ ተስፋ አስቆርጧል። ከዚህ የተነሳ ወደፊት ለመቀጠል ተግዳሮት ሆኗል። ትክክለኛ መፍትሔ እና ትክክለኛ ስራ ናቸው፤ ነገር ግን በአሰራር፣ ክፍተት የፈጠርንባቸው ናቸው፤ ዝም ብለን ስንመለከታቸው ለትምህርት የሚሆነን እንጂ ሲጀመር በቂ ጥናትና በቂ ትምህርት አላደረግንበትም። ትንሽ የችኮላም የዘመቻም ውሳኔዎች የታየበት ነበር። ከቦታ አመራረጥ ጀምሮ የሚሰራው ምን አይነት ግድብ ነው ከሚለው አንጻር እና ከማኅበረሰቡ ጋር የመዋሃድ ችግር የነበረባቸው ናቸው።

ከዚህ የተነሳ ፕሮጀክቶቹ በታሰበላቸው ጊዜ እና በታሰበበት መልኩ መጠናቀቅ አልቻሉም። አለመጠናቀቃቸው ከጊዜ ወደጊዜ በጀት የሚመድበውን የመንግስት አካል ተስፋ እያስቆረጠው የሔደ ከመሆኑም በተጨማሪ በፓርላማ አባላትም ለብክነት ተዳርጓል የሚል ወቀሳ አምጥቷል። ይህ በወቅቱ ባሉ ባለሙያዎች በአንድም በሌላም የተፈጠረ ክፍተት ነው እንጂ ኢትዮጵያ መስኖን በግድብ ከማልማት ውጪ አማራጭ የላትም። አሁን በእዛ ተስፋ ቆርጠን ያለግድብ የሚለውን አማራጭ መከተል አንችልም። ያንን የምናደርግ ከሆነ መልሰን የመስኖ ልማታችንን ማዳከም ነው። ተስፋ ማስቆረጥም ነው። በተስፋ መቁረጥ ውስጥ መሻገር አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የመስኖ ግድቦች ዛሬ ነገ ይመረቃሉ እየተባለ በነበረበት የውሃ ሽታ ሆነው ከርመዋል፤ ዛሬስ በምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

በለጠ (ዶ/ር)፡– እነሱ ክለሳ ተሰርቶላቸዋል። እንዲያውም መገጭ ጥሩ የክለሳ ዲዛይን ተሰርቶለት በበጀት ምክንያት ሳይቀጥል ቆየ እንጂ በዚህ ዓመት በጀት ከተሰጣቸው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያስቀጥለዋል የሚል እምነት አለኝ። ሁሉም ካላቸው የውሃ አቅም አንጻር ምቹ ናቸው። ቀጣይነትም ያላቸው ናቸው። ክስተቱ የተፈጠረው ከአሰራር ስህተት ነው። ይህ መፈጠሩ ግን የሚያስደንቅ አይሆንም፤ ከስራችን መማር መቻል አንዱ ጉዳይ ነው፤ በተለያዩ አገራትም ሊጋጥም የሚችል ክስተት ነው። ከትናንት እየተማሩ መሔድ ነው እንጂ በወቅቱ በነበረው መረጃና ግንዛቤ የተሳሳተ ነገር አይኖርም ብለን ልንደመድም አንችልም። ከስህተት መታረም ግን ወሳኙ ተግባር ነው። ከልሰን ግን ወደ ሥራ ማስገባት አለብን። ከመካከላቸውም ወደ አገልግሎት የገባ አለ።

ፈጣን የሆነ ለነር ለጊዜው ያስፈልገናል ከተባለ ደግሞ ሁሉንም ሰብሰብ አድርጎ መያዝ የሚችል ተለቅ ያለ ወጥ ግድብ መስራት ይቻላል። ለዚህ ሥራ ደግሞ ተጠንተው የተቀመጡ አማራጭ ቦታዎች አሉ። ወጥ ግድብ በመስራት ከቦታ ቦታ በካናል ማዳረስ ይቻላል። በርከት ያሉ አገራት የሚጠቀሙትም ይህኛውን መንገድ ነው። ልክ በመንገዱ ሴክተር ፈጣን መንገድ እንደሚሰራ ሁሉ የመስኖ ካናልም ከአገር አገር ሊዘረጋ ይችላል። የሚዘረጋው የመስኖ ካናል የውሃ ላይ ትራንስፖርት አገልግሎትም መስጠት ይችላል። በየአካባቢውም የዓሳ ልማት መስሪያም ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የሌሎችን አገራት መስኖን በካናል የማዘዋወር ተሞክሮ ቢጠቅሱልን?

በለጠ (ዶ/ር)፡– በርካታ አገራት የዚህ ተሞክሮ አላቸው፤ ከአፍሪካ አገራትም በዚህ ስልት የሚጠሙ ለምሳሌ ግብጽን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፤ ከአስዋን ግድብ በኋላ ከአንዱ ክፍለ አገር ወደሌላው ክፍለ አገር ውሃውን ስታዞር የቆችው በመስኖ ካናል (ቦይ) ነው። እስከ ሲና መዳረሻም እየወሰደችው በካናል ነው። ያላት አንድ አስዋን ግድብ ነው። ግድቡ አንድ ቦታ ይሁን እንጂ ብዙ ቦታ መገኘት የሚችል ነው።

የመስኖ ልማት በጣም ውጤታማ የሚሆነው በዚህ መልኩ ሲሆን ነው። ማለትም ቦዩን ለተለያየ ጥቅም እየተጠቀምንበት ማለት ነው። እግረ መንገዱን ለመካከለኛ ከተሞቻችን ለመጠጥ ውሃም ጭምር ማገልገል የሚችል ይሆናል። ሌላ ምሳሌ ሕንድ መውሰድ እንችላለን፤ ሕንድ ከአንድ ግድብ ብቻ ተነስቶ የሚሄድ አገር አቋራጭ የሚሆኑ አንድ ሺ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚሄድ ካናል አላት። ሌላውን ልተወውና ቴሩ የሚባል ግድቧን በማሳያነት ልውሰድ። ቴሩ ግድብ፣ ቴሩ ከሚባል ወንዝ ላይ የተገደበ ግድብ ነው። በዚያ ግድብ በቀላሉ የመስኖ ካናሉ ብቻ ወደ 640 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። በመጀመሪያ ግድቡ ሲሰራ ከታች ያለችውን የቴሩ ከተማ ጎርፍ እንዳያጠቃት ታስቦ ነው። ሰለዚህ ግድቡ ጎርፍ በመከላከል ረገድ የራሱ ሚና አለው። ዋናው ነገር ከግድቡ በካናል የሚጓጓዘው ውሃ ወደ 600 ሺ ሔክታር መሬት ድረስ መስኖ ያለማል።

ከዚያ አልፎ ሔዶ ለኒውዴልሂ ከተማ ለመጠጥ ውሃ ፍጆታ ይውላል። ወደ ሁለት ሺ 400 ሜጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። ስለዚህ እንዲህ አይነቶችን ትልልቅ እና ሁለገብ የሆኑ ግድቦች ስንሰራ በዚህ ልኩ ውጤታማ ያደርጉናል፤ ቶሎም ያሻግሩናል። ስለዚህ ቀደም ሲል የነበሩ ልምምዶቻችን ስኬታማ ባለመሆናቸው እንደ ድካም ባይቆጠሩና እንደተሞክሮ ቢወሰዱ መልካም ነው። የውሳኔ አቅጣጫ ማስቀየሪያ ሆነው ባይወሰዱ መልካም ነው። ግድብ እየሰራን መስኖ ማልማት ያስፈልገናል።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያከናወነች ያለውን ተግባር እንዴት ያዩታል? ትክክለኛውን መስመር ይዛለች ይላሉ?

በለጠ (ዶ/ር)፡– ጅምሩና ሐሳቡ አለ፤ በቂ ነው ማለት ግን አይቻልም። ምክንያቱም ጅምርና ሐሳብ ስንል በአሁኑ ወቅት የበጋ ስንዴ ብሎ እንደ ፕሮጀክት የተጀመረው አንድ ትልቅ ሒደት ነው። ምክንያቱም የበጋ ስንዴ የሚለማው በመስኖ ነው፤ መስኖን መሰረት አድርጎ የተነሳ ነው። በእርግጥ የተወሰኑ የበልግ ዝናብ ያላቸው በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። ነገር ግን በዋናነት የበጋ ስንዴ ፕሮጀክት እንደ ፕሮግራም የተያዘው በመስኖ ነው። ይህ አንድ አቅጣጫ ነው። ነገር ግን አሁን በተያዘበት በተበጣጠሰ የመሬት ሁኔታ ሳይሆን እንደ አገር ሰፋ አድርገን እያመረትን አይደለም።

ሁለተኛው ከሚያስፈልገን ፍላጎት አንጻር ሕዝባችን በብዛት እያደገ ነው። ስለዚህ በዓመት የምናለማው የምርት መጠን ከፍ ሊል የግድ ነው። ስለሆነም ጠንከር አድርጎ መተግበር ይፈልጋል እንጂ ሐሳብ አለ፤ የፖሊሲ አቅጣጫም አለ፤ ተሞክሮዎችም አሉን። እነዚህ ደግሞ መንገድ ላይ እንደሆንን የሚያሳዩ ናቸው። ይሁንና በእነዚህ ላይ ብቻ መቆም አንችልም። ሰፋ አድርገን ጠንክረን መሔድ አለብን።

በነገራችን ላይ በየትኛውም አገር ያለውን ተሞክሮ ወደኋላ መልሰን ብናስተውል የተለወጡትና ወደ እድገት ጎዳና ውስጥ መግባት የቻሉት በመጀመሪያ በምግብ ራሳቸውን ችለው ነው። በሕዝብ ብዛት ከእኛ በላይ የሆኑ አገሮች ሁሉ ሕዝባቸውን ይመግባሉ። የተመገበ አካል ደግሞ ብዙ መስራት ይችላል። ምክንያቱም አንዱ የሀሳባችን ደካማነት የሚመጣው ከአመመጋገባችን ስለሆነ ነው። እውነት ለመናገር ደግሞ ኢትዮጵያውያን በብቃት እየተመገብን ነው ማለት አንችልም። ከዚህ የተነሳ ሀሳባችንም የጎለበተ አይደለም። ለአዳዲስ ሀሳብ የሚያነሳሳ አይደለም። ለመኖር ያህል በልተናል። ከዚህ የተነሳ አመለካከታችንም ሆነ አስተሳሰባችን የሚሆነው አናሳ ነው። ስለዚህ በምግብ ራስን መቻል መሰረታዊ ነገር ነው። ጅምር አለን፤ መንገድ ላይም ነን። ልክ እንደ ሕዳሴ ግድብ አጠንክረነው በሕብረት ተሻጋሪ የሚያደርግ ሥራ መስራት አለብን። ሕዝቡን ሁሉ የሚያስተባብር ፕሮጀክት ያስፈልገናል የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- የውሃ ሀብት አጠቃቀማችን ምን ይመስላል? ምንስ መሆን አለበት ይላሉ?

በለጠ (ዶ/ር)፡– በልማድ የመጣ አባባል አለ፤ ይኸውም “ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት” እዚህ አባባል ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ሰዓት ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን ጉዳይ በተለያየ አጋጣሚ እና ባገኘሁት መድረክ ላይ ሁሉ እንደ ባለሙያ ለማስረዳት እየሞከርኩ ነው። ይህን የምልበት ምክንያት ልክ ነው ኢትዮጵያ ጥሩ የሆነ የውሃ ምንጭ አላት። ጥሩ የውሃ ሀብት ግን የላትም።

የውሃ ምንጭ ስንል አብዛኛው በኢትዮጵያ ገጸ ምድር ላይ የሚዘንብ ወደ አንድ ትሪሊዮን ሜትር ኪዩብ ወይም ደግሞ አንድ ሺ ቢሊዮን ሜትር ኪየብ ውሃ ከሚዘንበው አለን። ይህን የሚዘንበውን ውሃ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠርና ማስቀረት አይቻልም። ምክንያቱም ተፈጥሮም በራሱ በትነት የሚወስደው መጠን አለ። የውሃ ማማ እየተባልን የቆየነው ይህ ስላለን ነው። ያለነው ደግሞ ተራራ ላይ እንደመሆናችን ተራራው ሁሉ የሚዳርገን ለዝናብ ነው። ደረቅ የሆኑ ቦታዎች ሁሉ በዓመት ዝናብ ሳያገኙ አይቀሩም፤ ነገር ግን ፈስሰው ስለሚሔዱና ለማምረት በቂ ባለመሆናቸው ይህን ያህል ውሃ ኢትዮጵያ አላት እየተባለ እንደ ሀብት እየተቆጠረ ነው። ይህ ግን ሀብት አይደለም፤ ምንጭ ነው፡። ይህን ሐሳብ (water resource እና water source) የሚሉት ቃላት ልዩነቱን በደንብ ይገልጹታል።

ውሃ ሀብት የሚሆነው ግን ተቆጣጥረነው ወደምንፈልገው ምርት ስንቀይረው ነው። ይህን ውሃ ተቆጣጥረን ለኃይልም ለምግብም ልማት ስናውለው ሀብት ሆነ ማለት ነው። አለበለዚያ ግን ዝናብ ስለዘነበ ብቻ ሀብት ሆነ ማለት አይቻልም። ወደ ሀብት እንቀይረው ከተባለ ግድብ መስራት አለብን። ይህን ነገር በጣም አጽንኦት ለመስጠት ማስረጃ ካስፈለገ አሁን ባለን ሁኔታና የሰበሰብነው የውሃ አናሳነት የተነሳ ኢትዮጵያ ውሃ አጠር ወደሆኑ አገራት ክለብ ልትቀላቀል ትንሽ ይቀራታል።

አዲስ ዘመን፡- አንድ አገር ውሃ አጠር ነው የሚያስብለው መለኪያ ምንድን ነው? ኢትዮጵያስ አሁን ያለችበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?

በለጠ (ዶ/ር)፡– እኔም እሱን ለማብራራት ነው የፈለኩት፤ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት አንድ አገር በዓመት በሰው አንድ ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ ሊኖረው ከቻለ ነው። ለምሳሌ እኛ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ነን። ይህን ያህል ሕዝብ በአንድ ሺ ብናበዛው ከውሃ እጥረት ውጭ ለመሆን የሚጠበቅብን የውሃ መጠን አለ፤ እኛ ይህን እያቀረብን ደግሞ አይደለም። አሁን ባሉን በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ግድቦቻችን የሰበሰብነው ውሃ የሚያሳየው ወደ 40 ሚሊዮን ነው። በእርግጥ የሕዳሴ ግድብ ወደሙሉ አቅሙ ሲገባ ይህ ቁጥር የሚቀየር ይሆናል።

የዓለም ባንክ በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ ፐር ካፒታል ያላት የውሃ ሁኔታ በዓመት በሰው ማለት ነው፤ አንድ ሺ 40 ነው። ይህ ማለት የውሃ አጠር ክለብ ውስጥ ልንገባ የቀረን 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ነው፤ የሕዝብ ቁጥራችን ደግሞ በየዓመቱ እያደገ በመሆኑና መረጃው ከወጣ ወደ ሁሉት ዓመት ያህል ያስቆጠረ በመሆኑ ያለነው ጥያቄ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል። የውሃ እጥረታችን መቀየር የሚችለው የሚፈሰውን የዝናብ ውሃ በሚቻለው ቴክኖሎጂ ሁሉ አጠራቅሞ ወደምርት መቀየር ሲቻል ነው። ስለዚህ ትልልቅ ግድቦች እና አነስተኛ ግድቦችንም መጠቀም ወሳኝ ነው።

ለአብነት ለማንሳት ያህል ባለፈው የድርቅ ጊዜ ቦረና አካባቢ ተከስቶ የነበረው ችግር የሚታወስ ነው። ፊና ኦሮሚያ በሚለው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አንድ ጥሩ ማሳያ ናቸው። ትንንሽም ቢሆኑ የሚዘንበውን ውሃ መቆጣጠር ስለቻሉ በጋው መጥቶ ወደሚቀጥለው ክረምት ለመሻገር የሚያስችሉ ናቸው። ከዚህ የተነሳ በተደጋጋሚ ከሚመጣው ድርቅ መውጣት እየቻሉ ነው። ውሃ በየትኛውም ስልት ካልተያዘ በስተቀር ውጤታማ መሆን አይቻልም፡። ስለዚህ የውሃ ሀብታችንን በትክክል ለመጠቀም የውሃ መሰብሰቢያዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን።

ኢትዮጵያ የመስኖ ልማትን የትኩረት ማዕከሏ ማድረግ አለባት የሚል እምነት አለኝ። በአጠቃላይ የውሃ ልማቶቻችን ማዕከል ሆኖ ከተንቀሳቀሰ አብሮ ኢንዱስትሪ፣ የዓሳ ልማት፣ አግሮ ኢንዱስትሪ ይመጣል፡። የሰው ኃይል ይመጣል፤ የማኅበረሰብ ግንኙነት ይዳብራል። ባለሙያዎችም ሆንን የመንግስት አካላት ጥሩ የውይይት መድረክ ፈጥረን ተወያይተን የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ውሃን ማዕከል ያደረገ ሆኖ እንዲቀየስ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን፡- ለሁልጊዜ ትብብርዎ ከልብ አመሰግናለሁ።

በለጠ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2016 ዓ.ም

Recommended For You